ዘሌዋውያን 17:1-16
17 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
2 “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲሁም እስራኤላውያንን በሙሉ እንዲህ በላቸው፦ ‘ይሖዋ ያዘዘው ይህ ነው፦
3 “‘“ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው በሬ ወይም የበግ ጠቦት አሊያም ፍየል በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርድና
4 በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ፊት ለይሖዋ መባ አድርጎ ለማቅረብ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ባያመጣ ያ ሰው በደም ዕዳ ይጠየቃል። ሰውየው ደም አፍስሷል፤ በመሆኑም ይህ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።
5 ይህም እስራኤላውያን በሜዳ ላይ እየሠዉ ያሉትን መሥዋዕት ወደ ይሖዋ፣ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያና ወደ ካህኑ እንዲያመጡ ነው። እነዚህንም ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕቶች አድርገው መሠዋት አለባቸው።+
6 ካህኑም ደሙን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ባለው የይሖዋ መሠዊያ ላይ ይረጨዋል፤ ስቡንም ለይሖዋ ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ አድርጎ ያጨሰዋል።+
7 ከእንግዲህ ወዲህ፣ አብረዋቸው ምንዝር ለሚፈጽሙት+ ፍየል የሚመስሉ አጋንንት*+ አይሠዉም። ይህም በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ ለእናንተ ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።”’
8 “እንዲህም በላቸው፦ ‘የሚቃጠል መባ ወይም መሥዋዕት የሚያቀርብ ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው
9 ይህን ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ባያመጣ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+
10 “‘ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው ወይም በመካከላችሁ የሚኖር የትኛውም የባዕድ አገር ሰው ምንም ዓይነት ደም ቢበላ፣+ ደም በሚበላው ሰው* ላይ በእርግጥ ፊቴን አጠቁርበታለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ።
11 ምክንያቱም የሥጋ ሕይወት* ያለው በደሙ ውስጥ ነው፤+ ለራሳችሁም* ማስተሰረያ እንዲሆን እኔ ራሴ ደሙን ለእናንተ ስል ለመሠዊያው ሰጥቼዋለሁ፤+ ምክንያቱም በውስጡ ባለው ሕይወት* አማካኝነት የሚያስተሰርየው ደሙ ነው።+
12 እስራኤላውያንን “ማንኛችሁም ደም መብላት የለባችሁም፤* እንዲሁም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው+ ደም አይብላ”+ ያልኳቸው ለዚህ ነው።
13 “‘አንድ እስራኤላዊ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር አንድ የባዕድ አገር ሰው ለመብልነት የተፈቀደ እንስሳ ወይም ወፍ አድኖ ቢይዝ ደሙን ያፍሰው፤+ አፈርም ያልብሰው።
14 የሥጋ ሁሉ ሕይወት* ደሙ ነውና፤ ምክንያቱም በውስጡ ሕይወት* አለ። በዚህም የተነሳ እስራኤላውያንን እንዲህ አልኳቸው፦ “የሥጋ ሁሉ ሕይወት* ደሙ ስለሆነ የማንኛውንም ሥጋ ደም አትብሉ። ደም የሚበላ ማንኛውም ሰው ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል።”+
15 የአገሬው ተወላጅም ይሁን የባዕድ አገር ሰው፣ ማንኛውም ሰው* ሞቶ የተገኘን ወይም አውሬ የቦጫጨቀውን እንስሳ+ ሥጋ ቢበላ ልብሶቹን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሁን፤+ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል።
16 ሆኖም ልብሶቹን ካላጠበና ሰውነቱን ካልታጠበ በሠራው ጥፋት ይጠየቅበታል።’”+