ዘሌዋውያን 18:1-30

  • ተገቢ ያልሆነ የፆታ ግንኙነት (1-30)

    • እንደ ከነአናውያን አታድርጉ (3)

    • በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነት (6-18)

    • በወር አበባ ጊዜ (19)

    • ግብረ ሰዶማዊነት (22)

    • ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም (23)

    • ምድሪቱ እንዳትተፋችሁ ራሳችሁን አታርክሱ (24-30)

18  ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦  “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+  ትኖሩበት በነበረው በግብፅ ምድር ያሉ ሰዎች እንደሚያደርጉት አታድርጉ፤ እኔ በማስገባችሁ በከነአን ምድር ያሉ ሰዎች እንደሚያደርጉትም አታድርጉ።+ እንዲሁም እነሱ የሚከተሏቸውን ደንቦች አትከተሉ።  ድንጋጌዎቼን ተግባር ላይ አውሉ፤ ደንቦቼንም በመጠበቅ በእነሱ ሂዱ።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።  ደንቦቼንና ድንጋጌዎቼን ጠብቁ፤ እንዲህ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው በእነሱ አማካኝነት በሕይወት ይኖራል።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።  “‘ከመካከላችሁ ማንም ሰው የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ወደ ማንኛውም የቅርብ ዘመዱ አይቅረብ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።  ከአባትህ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ከእናትህም ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም። እሷ እናትህ ናት፤ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።  “‘ከአባትህ ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።+ ይህ አባትህን ለኀፍረት መዳረግ ነው።*  “‘የአባትህ ልጅም ሆነች የእናትህ ልጅ ወይም በቤት የተወለደችም ሆነች በውጭ፣ ከእህትህ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።+ 10  “‘ከወንድ ልጅህ ሴት ልጅ ወይም ከሴት ልጅህ ሴት ልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ምክንያቱም እነሱ የአንተው እርቃን ናቸው። 11  “‘የአባትህ ልጅ ከሆነችው ከአባትህ ሚስት ሴት ልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ምክንያቱም እሷ እህትህ ናት። 12  “‘ከአባትህ እህት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም። እሷ የአባትህ የሥጋ ዘመድ ናት።+ 13  “‘ከእናትህ እህት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ምክንያቱም እሷ የእናትህ የሥጋ ዘመድ ናት። 14  “‘ከአባትህ ወንድም ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት በመፈጸም እሱን ለኀፍረት አትዳርገው።* እሷ ዘመድህ ናት።+ 15  “‘ከልጅህ ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።+ እሷ የልጅህ ሚስት ናት፤ ከእሷ ጋር ግንኙነት መፈጸም የለብህም። 16  “‘ከወንድምህ ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤+ ምክንያቱም ይህ ወንድምህን ለኀፍረት መዳረግ ነው።* 17  “‘ከአንዲት ሴትና ከሴት ልጇ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።+ ከወንድ ልጇ ሴት ልጅም ሆነ ከሴት ልጇ ሴት ልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም እነሱን አትውሰድ። እነሱ የእሷ የቅርብ ዘመዶች ናቸው፤ ይህ ጸያፍ ድርጊት* ነው። 18  “‘እህቷ ጣውንቷ እንዳትሆን+ ሚስትህ በሕይወት እያለች ከእህቷ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም። 19  “‘አንዲት ሴት በወር አበባዋ ረክሳ እያለች ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ወደ እሷ አትቅረብ።+ 20  “‘ከጓደኛህ* ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ራስህን አታርክስ።+ 21  “‘ከልጆችህ መካከል የትኛውንም ለሞሎክ እንዲሰጥ* አታድርግ።+ በዚህ መንገድ የአምላክህን ስም አታርክስ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ። 22  “‘ከሴት ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ።+ ይህ አስጸያፊ ድርጊት ነው። 23  “‘አንድ ወንድ ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ራሱን አያርክስ፤ ሴትም ብትሆን ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ራሷን ለእንስሳ አታቅርብ።+ ይህ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ነገር ነው። 24  “‘ከእነዚህ ነገሮች በየትኛውም ራሳችሁን አታርክሱ፤ ምክንያቱም ከእናንተ ፊት አባርሬ የማስወጣቸው ብሔራት ራሳቸውን በእነዚህ ነገሮች አርክሰዋል።+ 25  ስለሆነም ምድሪቱ ረክሳለች፤ እኔም ለሠራችው ስህተት ቅጣት አመጣባታለሁ፤ ምድሪቱም ነዋሪዎቿን ትተፋቸዋለች።+ 26  እናንተ ግን ደንቦቼንና ድንጋጌዎቼን ጠብቁ፤+ ከእነዚህ አስጸያፊ ነገሮች መካከል የትኛውንም ማድረግ የለባችሁም፤ የአገራችሁ ሰውም ሆነ በመካከላችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው እንዲህ ማድረግ የለበትም።+ 27  ምክንያቱም ከእናንተ በፊት በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ ፈጽመዋል፤+ በዚህም የተነሳ አሁን ምድሪቱ ረክሳለች። 28  እናንተ ግን ምድሪቱን ስለማታረክሷት ከእናንተ በፊት የነበሩትን ብሔራት እንደተፋቻቸው እናንተን አትተፋችሁም። 29  ማንኛውም ሰው ከእነዚህ አስጸያፊ ነገሮች መካከል የትኛውንም ቢፈጽም ይህን የፈጸመው ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ። 30  ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች ይከተሏቸው ከነበሩት አስጸያፊ ልማዶች በመራቅ ለእኔ የገባችሁትን ግዴታ ፈጽሙ፤+ አለዚያ በእነሱ ምክንያት ራሳችሁን ታረክሳላችሁ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ይህ የአባትህ እርቃን ነው።”
ቃል በቃል “የአባትህን ወንድም እርቃን አትግለጥ።”
ቃል በቃል “ይህ የወንድምህ እርቃን ነው።”
ወይም “አሳፋሪ ምግባር፤ ሴሰኝነት።”
ወይም “ከጎረቤትህ።”
ወይም “መሥዋዕት እንዲሆን።”
ወይም “ነፍስ።”