ዘሌዋውያን 2:1-16

  • የእህል መባ(1-16)

2  “‘አንድ ሰው* ለይሖዋ የእህል መባ+ የሚያቀርብ ከሆነ መባው የላመ ዱቄት መሆን አለበት፤ በላዩም ላይ ዘይት ያፍስበት፤ ነጭ ዕጣንም ያስቀምጥበት።+  ከዚያም ካህናት ወደሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆች ያመጣዋል፤ ካህኑም ከላዩ ላይ አንድ እፍኝ የላመ ዱቄትና ዘይት፣ ነጭ ዕጣኑንም በሙሉ ይወስዳል፤ ይህንም አምላክ መላውን መባ እንዲያስበው የሚያደርግ መባ+ ይኸውም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል።  ከእህል መባው የተረፈው ማንኛውም ነገር የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ነው፤+ ይህም ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች የተረፈ ስለሆነ እጅግ ቅዱስ ነው።+  “‘በመጋገሪያ ምድጃ የተጋገረ የእህል መባ የምታቀርብ ከሆነ ከላመ ዱቄት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ እርሾ ያልገባበት የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦ ወይም ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ* መሆን ይኖርበታል።+  “‘መባህ በምጣድ የተጋገረ የእህል መባ+ ከሆነ በዘይት ከተለወሰ እርሾ ያልገባበት የላመ ዱቄት የተጋገረ መሆን ይኖርበታል።  መቆራረስ አለበት፤ ዘይትም አፍስበት።+ ይህ የእህል መባ ነው።  “‘መባህ በድስት የተዘጋጀ የእህል መባ ከሆነ ከላመ ዱቄትና ከዘይት የተሠራ መሆን ይኖርበታል።  ከእነዚህ ነገሮች የተዘጋጀውን የእህል መባ ወደ ይሖዋ ማምጣት ይኖርብሃል፤ ወደ መሠዊያው ለሚያቀርበውም ካህን ይሰጠው።  ካህኑም አምላክ መላውን መባ እንዲያስበው የሚያደርግ መባ+ እንዲሆን ከእህል መባው ላይ የተወሰነውን በማንሳት ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል።+ 10  ከእህል መባው የተረፈው የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ነው፤ ይህም ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች የተረፈ ስለሆነ እጅግ ቅዱስ ነው።+ 11  “‘እርሾ ወይም ማር ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጋችሁ ማጨስ ስለሌለባችሁ ለይሖዋ ከምታቀርቡት የእህል መባ ውስጥ እርሾ የገባበት ምንም ነገር አይኑር።+ 12  “‘እነዚህንም የፍሬ በኩራት መባ+ አድርጋችሁ ለይሖዋ ልታቀርቧቸው ትችላላችሁ፤ ሆኖም ደስ እንደሚያሰኝ* መዓዛ ሆነው ወደ መሠዊያው መምጣት የለባቸውም። 13  “‘የምታቀርበው የእህል መባ በሙሉ በጨው መቀመም አለበት፤ የአምላክህ የቃል ኪዳን ጨውም ከእህል መባህ ላይ አይጥፋ። ከማንኛውም መባህ ጋር ጨው አብረህ ታቀርባለህ።+ 14  “‘መጀመሪያ የደረሰውን ፍሬ የእህል መባ አድርገህ ለይሖዋ የምታቀርብ ከሆነ የደረሰውን ሆኖም ገና እሸት የሆነውን በእሳት የተጠበሰና የተከካ እህል መጀመሪያ ላይ እንደደረሰው ፍሬህ የእህል መባ አድርገህ አቅርብ።+ 15  በላዩም ላይ ዘይት ትጨምርበታለህ፤ ነጭ ዕጣንም ታስቀምጥበታለህ። ይህ የእህል መባ ነው። 16  ካህኑም ከተከካው እህልና ከዘይቱ የተወሰነውን፣ ነጭ ዕጣኑንም በሙሉ ወስዶ አምላክ መላውን መባ እንዲያስበው የሚያደርግ መባ+ ይኸውም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ ያጨሰዋል።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነፍስ።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ወይም “እንደሚያረጋጋ፣ እንደሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት እንደሚሰጥ።”