ዘሌዋውያን 24:1-23
24 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
2 “መብራቱ ያለማቋረጥ እንዲበራ ለማድረግ ለመብራቱ የሚሆን ተጨቅጭቆ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው።+
3 ከምሽት አንስቶ እስከ ጠዋት ድረስ መብራቱ በይሖዋ ፊት ያለማቋረጥ እንዲበራ አሮን በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ካለው ከምሥክሩ መጋረጃ ውጭ ያስቀምጠው። በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ዘላለማዊ ደንብ ነው።
4 ዘወትር በይሖዋ ፊት እንዲሆኑ መብራቶቹን ከንጹሕ ወርቅ በተሠራው መቅረዝ+ ላይ በቦታ በቦታቸው ያስቀምጣቸው።
5 “አንተም የላመ ዱቄት ወስደህ የቀለበት ቅርጽ ያላቸው 12 ዳቦዎችን ጋግር። እያንዳንዱ ዳቦ ከሁለት አሥረኛ ኢፍ* ዱቄት የተዘጋጀ መሆን ይኖርበታል።
6 እነዚህንም በይሖዋ ፊት ባለው ከንጹሕ ወርቅ በተሠራው ጠረጴዛ+ ላይ ስድስት ስድስት አድርገህ በማነባበር በሁለት ረድፍ ታስቀምጣቸዋለህ።+
7 ተነባብሮ በተቀመጠው በእያንዳንዱ ረድፍ ላይም ንጹሕ ነጭ ዕጣን አድርግ፤ ይህም ለምግቡ መታሰቢያ እንዲሆን+ ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ይሆናል።
8 እሱም በየሰንበቱ ዘወትር በይሖዋ ፊት ይደርድረው።+ ይህ በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ያለ ዘላቂ ቃል ኪዳን ነው።
9 ይህም የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ይሆናል፤+ ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች መካከል ለእሱ እጅግ ቅዱስ ነገር ስለሆነ ቅዱስ በሆነ ቦታ ይበሉታል፤+ ይህ ዘላቂ ሥርዓት ነው።”
10 በእስራኤላውያን መካከል በእናቱ እስራኤላዊ በአባቱ ግን ግብፃዊ የሆነ አንድ ሰው ነበር፤+ በሰፈሩም ውስጥ በእሱና በአንድ እስራኤላዊ መካከል ጠብ ተነሳ።
11 የእስራኤላዊቷም ልጅ የአምላክን ስም* መሳደብና መራገም ጀመረ።+ በመሆኑም ወደ ሙሴ አመጡት።+ የእናትየውም ስም ሸሎሚት ነበር፤ እሷም ከዳን ነገድ የሆነው የዲብራይ ልጅ ነበረች።
12 እነሱም የይሖዋ ውሳኔ ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ በጥበቃ ሥር እንዲቆይ አደረጉት።+
13 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
14 “የተራገመውን ሰው ከሰፈሩ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሰዎች ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ መላው ጉባኤም በድንጋይ ይውገረው።+
15 ለእስራኤላውያንም እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ማንኛውም ሰው አምላኩን ቢራገም ለሠራው ኃጢአት ይጠየቅበታል።
16 ስለሆነም የይሖዋን ስም የተሳደበው ሰው ይገደል።+ መላው ጉባኤም በድንጋይ ይውገረው። የባዕድ አገሩም ሰው የአምላክን ስም ከተሳደበ ልክ እንደ አገሩ ተወላጅ ይገደል።
17 “‘አንድ ሰው የሰው ሕይወት ካጠፋ* ይገደል።+
18 የቤት እንስሳን የገደለ* ሰው፣ ሕይወት ስለ ሕይወት* ካሳ አድርጎ መክፈል ይኖርበታል።
19 አንድ ሰው በባልንጀራው ላይ ጉዳት ቢያደርስ ልክ እሱ ያደረሰው ዓይነት ጉዳት በራሱ ላይ እንዲደርስ ይደረግ።+
20 ስብራት ስለ ስብራት፣ ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ ይሁን፤ በሰውየው ላይ ያደረሰው ዓይነት ጉዳት በእሱ ላይ እንዲደርስ ይደረግ።+
21 እንስሳን መትቶ የገደለ ስለ እንስሳው ካሳ መክፈል ይኖርበታል፤+ ሰውን መትቶ የገደለ ግን መገደል አለበት።+
22 “‘ለባዕድ አገሩም ሰው ሆነ ለአገሬው ተወላጅ፣ ለሁላችሁም የሚሠራው አንድ ዓይነት ድንጋጌ ነው፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”
23 ከዚያም ሙሴ ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ እነሱም የተራገመውን ሰው ከሰፈሩ ውጭ አውጥተው በድንጋይ ወገሩት።+ በዚህ መንገድ እስራኤላውያን ልክ ይሖዋ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።