ዘሌዋውያን 25:1-55
25 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፦
2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ+ ምድሪቱ ለይሖዋ ሰንበትን ማክበር ይኖርባታል።+
3 ስድስት ዓመት በእርሻህ ላይ ዘር ዝራ፤ ስድስት ዓመት ወይንህን ግረዝ፤ እንዲሁም የምድሪቱን ምርት ሰብስብ።+
4 ሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ የምታርፍበት ሰንበት ይኸውም የይሖዋ ሰንበት ይሁን። በእርሻህ ላይ ዘር አትዝራ ወይም ወይንህን አትግረዝ።
5 በማሳህ ላይ የበቀለውን ገቦ* አትጨድ፤ ያልተገረዘውን ወይንህን ፍሬ አትልቀም። ምድሪቱ ለአንድ ዓመት ሙሉ በሙሉ ማረፍ ይኖርባታል።
6 ሆኖም ምድሪቱ በሰንበት እረፍቷ ጊዜ የምታበቅለውን እህል መብላት ትችላለህ፤ አንተ፣ ወንድ ባሪያህ፣ ሴት ባሪያህ፣ ቅጥር ሠራተኛህና አብረውህ የሚኖሩ ባዕዳን ሰፋሪዎች ልትበሉት ትችላላችሁ፤
7 እንዲሁም በምድርህ ለሚኖሩ የቤትና የዱር እንስሳት ምግብ ይሁን። ምድሪቱ የምትሰጠው ምርት ሁሉ ለምግብነት ሊውል ይችላል።
8 “‘ሰባት የሰንበት ዓመታትን ማለትም ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመታትን ትቆጥራለህ፤ ሰባቱ የሰንበት ዓመታትም 49 ዓመታት ይሆናሉ።
9 ከዚያም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን ቀንደ መለከቱን ድምፁን ከፍ አድርገህ ትነፋዋለህ፤ በስርየት ቀን+ የቀንደ መለከቱ ድምፅ በምድራችሁ ሁሉ እንዲሰማ ማድረግ አለባችሁ።
10 ሃምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱም ለሚኖሩ ሁሉ ነፃነት አውጁ።+ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆንላችኋል፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደየርስቱ ይመለሳል፤ ከእናንተም እያንዳንዱ ወደየቤተሰቡ ይመለስ።+
11 ሃምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆንላችኋል። ዘር አትዘሩም ወይም ማሳ ላይ የበቀለውን ገቦ አታጭዱም አሊያም ያልተገረዘውን የወይን ፍሬ አትሰበስቡም።+
12 ምክንያቱም ይህ ኢዮቤልዩ ነው። ለእናንተም ቅዱስ መሆን ይኖርበታል። ምድሪቱ በራሷ የምታበቅለውን ብቻ መብላት ትችላላችሁ።+
13 “‘በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት ከእናንተ እያንዳንዱ ወደየርስቱ ይመለስ።+
14 ለባልንጀራችሁ አንድ ነገር ብትሸጡ ወይም ከባልንጀራችሁ እጅ አንድ ነገር ብትገዙ አንዳችሁ ሌላውን መጠቀሚያ አታድርጉ።+
15 ከባልንጀራህ ላይ መሬት ስትገዛ ከኢዮቤልዩ በኋላ ያሉትን ዓመታት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል፤ እሱም ሲሸጥልህ እህል የሚሰበሰብባቸውን የቀሩትን ዓመታት ማስላት ይኖርበታል።+
16 ብዙ ዓመታት የሚቀሩ ከሆነ ዋጋውን መጨመር ይችላል፤ የሚቀሩት ዓመታት ጥቂት ከሆኑ ደግሞ ዋጋውን መቀነስ ይኖርበታል፤ ምክንያቱም የሚሸጥልህ አዝመራ የሚሰበሰብበትን ጊዜ አስልቶ ነው።
17 ከእናንተ መካከል ማንም ባልንጀራውን መጠቀሚያ ማድረግ የለበትም፤+ አምላክህን ፍራ፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+
18 ደንቦቼን ብትፈጽሙና ድንጋጌዎቼን ብትጠብቁ በምድሪቱ ላይ ያለስጋት ትኖራላችሁ።+
19 ምድሪቱ ፍሬዋን ትሰጣለች፤+ እናንተም እስክትጠግቡ ድረስ ትበላላችሁ፤ በዚያም ያለስጋት ትኖራላችሁ።+
20 “‘ሆኖም ‘ዘር ካልዘራን ወይም እህል ካልሰበሰብን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ+
21 እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እልክላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ እህል ታፈራለች።+
22 ከዚያም በስምንተኛው ዓመት ዘር ትዘራላችሁ፤ እስከ ዘጠነኛውም ዓመት ድረስ ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ትበላላችሁ። እህሉ እስኪደርስ ድረስ ቀድሞ የሰበሰባችሁትን ትበላላችሁ።
23 “‘ምድሪቱ የእኔ ስለሆነች+ መሬት ለዘለቄታው መሸጥ አይኖርበትም።+ ምክንያቱም እናንተ በእኔ አመለካከት የባዕድ አገር ሰዎችና ሰፋሪዎች ናችሁ።+
24 በርስትነት በያዛችሁት ምድር ሁሉ መሬትን መልሶ መግዛት የሚያስችል መብት እንዲኖር አድርጉ።
25 “‘ወንድምህ ቢደኸይና ከርስቱ የተወሰነውን ለመሸጥ ቢገደድ የሚዋጅ የቅርብ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን መልሶ ይግዛ።+
26 አንድ ሰው የሚዋጅለት ቢያጣ ሆኖም እሱ ራሱ ሀብት ቢያገኝና መሬቱን ለመዋጀት የሚያስችል አቅም ቢኖረው
27 መሬቱን ከሸጠበት ጊዜ አንስቶ ያሉትን ዓመታት በመቁጠር ዋጋውን ያስላ፤ የዋጋውንም ልዩነት ለሸጠለት ሰው ይመልስ። ከዚያም ወደ ርስቱ መመለስ ይችላል።+
28 “‘ሆኖም መሬቱን ከሰውየው ላይ ለማስመለስ የሚያስችል አቅም ባይኖረው የሸጠው መሬት እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ በገዢው እጅ ይቆያል፤+ መሬቱም በኢዮቤልዩ ይመለስለታል፤ እሱም ወደ ርስቱ ይመለሳል።+
29 “‘አንድ ሰው በቅጥር በታጠረ ከተማ ውስጥ የሚገኝን መኖሪያ ቤት ቢሸጥ ከሸጠበት ጊዜ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ድረስ የመዋጀት መብቱ እንደተጠበቀ ይቆያል፤ የመዋጀት መብቱ+ ለአንድ ዓመት ሙሉ እንደተጠበቀ ይቆያል።
30 ይሁንና ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት መልሶ ሊገዛው ካልቻለ በቅጥር በታጠረው ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቤት ለዘለቄታው የገዢው ንብረት ሆኖ በትውልዶቹ ሁሉ ይቀጥላል። በኢዮቤልዩ ነፃ አይለቀቅም።
31 ቅጥር በሌላቸው መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ግን በገጠራማ አካባቢ የሚገኝ የእርሻ መሬት ክፍል እንደሆኑ ይቆጠራሉ። የመዋጀት መብታቸው እንደተጠበቀ ይቆይ፤ በኢዮቤልዩም ነፃ ይለቀቁ።
32 “‘በሌዋውያን ከተሞች+ ውስጥ ያሉትን የሌዋውያን ቤቶች በተመለከተ ግን ሌዋውያኑ እነዚህን ቤቶች የመዋጀት መብታቸው ምንጊዜም የተጠበቀ ነው።
33 የሌዋውያን ንብረት ተመልሶ ካልተገዛ የእነሱ በሆነው ከተማ ውስጥ የሚገኘው የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ነፃ ይለቀቃል፤+ ምክንያቱም በሌዋውያኑ ከተሞች ውስጥ የሚገኙት ቤቶች በእስራኤላውያን መካከል ያሉ የሌዋውያኑ ንብረቶች ናቸው።+
34 ከዚህም በላይ በከተሞቻቸው ዙሪያ ያለው የግጦሽ መሬት+ ዘላለማዊ ርስታቸው ስለሆነ መሸጥ አይኖርበትም።
35 “‘በአቅራቢያህ ያለ ወንድምህ ቢደኸይና ራሱን ማስተዳደር ቢያቅተው አብሮህ በሕይወት ይኖር ዘንድ አንድን የባዕድ አገር ሰውና ሰፋሪ+ እንደምትረዳ ሁሉ ልትረዳው ይገባል።+
36 ከእሱ ወለድ ወይም ትርፍ* አትቀበል።+ ከዚህ ይልቅ አምላክህን ፍራ፤+ ወንድምህም አብሮህ በሕይወት ይኖራል።
37 ገንዘብህን በወለድ አታበድረው+ ወይም እህል ስታበድረው ትርፍ አትጠይቀው።
38 የከነአንን ምድር በመስጠት አምላካችሁ መሆኔን አስመሠክር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+
39 “‘በአቅራቢያህ የሚኖር ወንድምህ ቢደኸይና ራሱን ለአንተ ለመሸጥ ቢገደድ+ እንደ ባሪያ እንዲሠራ አታስገድደው።+
40 እንደ ቅጥር ሠራተኛና እንደ ሰፋሪ ሊታይ ይገባዋል።+ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያገልግልህ።
41 ከዚያም እሱም ሆነ አብረውት ያሉት ልጆቹ* ትተውህ ይሄዳሉ፤ ወደ ዘመዶቹም ይመለሳሉ። እሱም ወደ ቀድሞ አባቶቹ ርስት ይመለስ።+
42 ምክንያቱም እነሱ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸው።+ እንደ ባሪያ ራሳቸውን መሸጥ የለባቸውም።
43 የጭካኔ ድርጊት ልትፈጽምበት አይገባም፤+ አምላክህን መፍራት ይኖርብሃል።+
44 ወንድ ባሪያዎቻችሁና ሴት ባሪያዎቻችሁ በዙሪያችሁ ካሉት ብሔራት የመጡ ይሁኑ፤ ከእነሱ መካከል ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ መግዛት ትችላላችሁ።
45 በተጨማሪም ከእናንተ ጋር ከሚኖሩት ባዕዳን ሰፋሪዎች+ እንዲሁም እነሱ በምድራችሁ ከወለዷቸው ቤተሰቦቻቸው መካከል ባሪያዎችን መግዛት ትችላላችሁ፤ እነሱም የእናንተ ንብረት ይሆናሉ።
46 እነሱንም እንደ ቋሚ ንብረት አድርጋችሁ ከእናንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆቻችሁ ማውረስ ትችላላችሁ። ባሪያ አድርጋችሁ ልታሠሯቸው ትችላላችሁ፤ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን እስራኤላውያንን ግን በጭካኔ አትግዟቸው።+
47 “‘በመካከልህ ያለ የባዕድ አገር ሰው ወይም ሰፋሪ ሀብታም ቢሆንና ከእሱ ጋር ያለው ወንድምህ ደግሞ ደህይቶ ለባዕድ አገሩ ሰው ወይም ሰፋሪ አሊያም ከባዕድ አገሩ ሰው ቤተሰብ መካከል ለአንዱ ራሱን ለመሸጥ ቢገደድ
48 ይህ ሰው ራሱን ከሸጠም በኋላ የመዋጀት መብቱ የተጠበቀ ይሆናል። ከወንድሞቹ አንዱ መልሶ ሊገዛው ይችላል፤+
49 ወይም ደግሞ አጎቱ አሊያም የአጎቱ ልጅ መልሶ ሊገዛው ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ማንኛውም የቅርብ ዘመዱ* ማለትም ከቤተሰቦቹ አንዱ መልሶ ሊገዛው ይችላል።
“‘ወይም ደግሞ ሰውየው ራሱ ሀብት ካገኘ ራሱን መልሶ ሊገዛ ይችላል።+
50 እሱም ራሱን ከሸጠበት ዓመት አንስቶ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን+ ጊዜ ከገዛው ሰው ጋር በመሆን ያስላ፤ የተሸጠበትም ገንዘብ ከዓመታቱ ብዛት ጋር የሚመጣጠን ይሁን።+ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያሉት የሥራ ቀናት የሚሰሉት የአንድ ቅጥር ሠራተኛ የሥራ ቀናት በሚሰሉበት መንገድ ይሆናል።+
51 ገና ብዙ ዓመታት የሚቀሩ ከሆነ እሱን ለመግዛት ከተከፈለው ገንዘብ ላይ የቀሪዎቹን ዓመታት ብዛት ግምት ውስጥ በማስገባት ራሱን የሚዋጅበትን ዋጋ ይክፈል።
52 እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የሚቀሩት ዓመታት ጥቂት ከሆኑ ደግሞ ይህን ለራሱ ያስላ፤ በቀሩት ዓመታት ብዛት ልክም የሚዋጅበትን ዋጋ ይክፈል።
53 ከእሱም ጋር በሚቆይበት ጊዜ ከዓመት እስከ ዓመት እንደ ቅጥር ሠራተኛ ሆኖ ያገልግለው፤ አንተም የጭካኔ ድርጊት እንዳይፈጽምበት ተከታተል።+
54 ሆኖም ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ ራሱን መልሶ መግዛት ካልቻለ በኢዮቤልዩ ዓመት ነፃ ይለቀቃል፤+ እሱም ሆነ ልጆቹ* አብረውት ነፃ ይለቀቁ።
55 “‘እስራኤላውያን የእኔ ባሪያዎች ናቸው። እነሱ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸው።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።