ዘሌዋውያን 5:1-19
5 “‘አንድ ሰው* ሰዎች የምሥክርነት ቃል እንዲሰጡ ጥሪ+ እየቀረበ መሆኑን ቢሰማና* እሱ መመሥከር እየቻለ ወይም ደግሞ ጉዳዩን አይቶ አሊያም አውቆ ሳለ ሳይናገር ቢቀር በሠራው ጥፋት ይጠየቅበታል።
2 “‘ወይም አንድ ሰው* ርኩስ የሆነን ማንኛውንም ነገር ይኸውም ርኩስ የሆነን የዱር አውሬ ወይም ርኩስ የሆነን የቤት እንስሳ አሊያም ርኩስ የሆነን የሚርመሰመስ ፍጥረት በድን ቢነካ፣+ ይህን ያደረገው ባለማወቅ ቢሆንም እንኳ ይህ ሰው ርኩስ ነው፤ በደለኛም ይሆናል።
3 ወይም አንድ ሰው ባለማወቅ የሰውን ርኩሰት+ ይኸውም እንዲረክስ ሊያደርገው የሚችለውን ማንኛውንም ርኩስ ነገር ቢነካና በኋላም ይህን ቢያውቅ በደለኛ ይሆናል።
4 “‘አሊያም ደግሞ አንድ ሰው* ነገሩ ምንም ሆነ ምን ክፉ ወይም መልካም ለማድረግ በችኮላ ቢምልና ይህን ያደረገው ባለማወቅ ቢሆን ሆኖም የማለው በችኮላ መሆኑን በኋላ ላይ ቢገነዘብ በደለኛ ይሆናል።*+
5 “‘ከእነዚህ ነገሮች በአንዱ በደለኛ ሆኖ ቢገኝ በምን መንገድ ኃጢአት እንደሠራ መናዘዝ+ አለበት።
6 ለሠራው ኃጢአት የበደል መባ+ ማለትም ከመንጋው መካከል እንስት የበግ ጠቦት ወይም እንስት የፍየል ግልገል የኃጢአት መባ አድርጎ ለይሖዋ ያመጣል። ከዚያም ካህኑ ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል።
7 “‘በግ ለማምጣት አቅሙ የማይፈቅድለት ከሆነ ግን ለሠራው ኃጢአት የበደል መባ እንዲሆኑ ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ለይሖዋ ያምጣ፤+ አንዱ ለኃጢአት መባ ሌላኛው ደግሞ ለሚቃጠል መባ ይሆናል።+
8 ወደ ካህኑም ያመጣቸዋል፤ ካህኑም በቅድሚያ ለኃጢአት መባ የሚሆነውን ያቀርባል፤ አንገቱን ሙሉ በሙሉ ሳይቆርጥ ከፊት በኩል አንገቱን በመቦጨቅ ያቀርበዋል።
9 ከኃጢአት መባው ደም ላይ የተወሰነውን በመሠዊያው ጎን ላይ ይረጨዋል፤ የተረፈው ደም ግን በመሠዊያው ሥር ይንጠፈጠፋል።+ ይህ የኃጢአት መባ ነው።
10 ሌላኛውን ደግሞ በተለመደው አሠራር መሠረት የሚቃጠል መባ አድርጎ ያቀርበዋል፤+ ካህኑም ለሠራው ኃጢአት ማስተሰረያ ያቀርብለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።+
11 “‘ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ለማምጣት አቅሙ የማይፈቅድለት ከሆነ ደግሞ ለሠራው ኃጢአት፣ የኃጢአት መባ እንዲሆን አንድ አሥረኛ ኢፍ*+ የላመ ዱቄት መባ አድርጎ ያምጣ። የኃጢአት መባ ስለሆነ ዘይት አይጨምርበት ወይም ነጭ ዕጣን አያድርግበት።
12 ወደ ካህኑም ያመጣዋል፤ ካህኑም አምላክ መላውን መባ እንዲያስበው ለማድረግ ከላዩ ላይ አንድ እፍኝ አንስቶ በመሠዊያው ላይ ባሉት ለይሖዋ በእሳት በሚቀርቡት መባዎች ላይ እንዲጨስ ያደርጋል። ይህ የኃጢአት መባ ነው።
13 ካህኑም ሰውየው ከእነዚህ ኃጢአቶች ውስጥ ለሠራው ለየትኛውም ኃጢአት ማስተሰረያ ያቀርብለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።+ እንደ እህል መባው+ ሁሉ ከመባው የተረፈውም የካህኑ ይሆናል።’”+
14 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦
15 “አንድ ሰው* ለይሖዋ በተቀደሱት ነገሮች ላይ ባለማወቅ ኃጢአት በመሥራት ታማኝነቱን ቢያጎድል+ ከመንጋው መካከል እንከን የሌለበትን አውራ በግ የበደል መባ አድርጎ ለይሖዋ ያመጣል፤+ ዋጋው በብር ሰቅል* የሚተመነው እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* መሠረት ነው።+
16 በቅዱሱ ስፍራ ላይ ለፈጸመው ኃጢአት ካሳ ይከፍላል፤ የዋጋውንም አንድ አምስተኛ ይጨምርበታል።+ ካህኑ ለበደል መባ በቀረበው አውራ በግ አማካኝነት እንዲያስተሰርይለትም ለካህኑ ይሰጠዋል፤+ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።+
17 “አንድ ሰው* ይሖዋ እንዳይደረጉ ብሎ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል አንዱን በመፈጸም ኃጢአት ቢሠራ፣ እንዲህ ያደረገው ባለማወቅ ቢሆንም እንኳ በደለኛ ይሆናል፤ በሠራውም ጥፋት ይጠየቅበታል።+
18 የበደል መባ እንዲሆንም የተተመነለትን ዋጋ ያህል የሚያወጣ እንከን የሌለበት አውራ በግ ከመንጋው መካከል ወስዶ ለካህኑ ያምጣ።+ ከዚያም ካህኑ፣ ሰውየው ባለማወቅ ለፈጸመው ስህተት ያስተሰርይለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።
19 ይህ የበደል መባ ነው። በይሖዋ ላይ ኃጢአት ስለፈጸመ በእርግጥ በደለኛ ይሆናል።”
የግርጌ ማስታወሻ
^ ቃል በቃል “የእርግማን (የመሐላ) ድምፅ ቢሰማና።” መጥፎ ድርጊት በፈጸመ ሰው ወይም የምሥክርነት ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ በማይሆን ምሥክር ላይ የሚነገረውን እርግማን ጨምሮ አንድን መጥፎ ድርጊት በተመለከተ የሚታወጅን አዋጅ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ወይም “ነፍስ።”
^ አንድ ሰው የገባውን ቃል ሳይፈጽም መቅረቱን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”
^ ወይም “ነፍስ።”