ዘሌዋውያን 8:1-36
-
የአሮን የክህነት ሹመት ሥርዓት (1-36)
8 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
2 “አሮንን፣ ከእሱም ጋር ወንዶች ልጆቹን+ እንዲሁም ልብሶቹን፣+ የቅብዓት ዘይቱን፣+ ለኃጢአት መባ የሚሆነውን በሬ፣ ሁለቱን አውራ በጎችና ቂጣ ያለበትን ቅርጫት+ ውሰድ፤
3 መላው ማኅበረሰብም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ እንዲሰበሰብ አድርግ።”
4 ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበረሰቡም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ተሰበሰበ።
5 ሙሴም ለማኅበረሰቡ “ይሖዋ እንድናደርግ ያዘዘን ነገር ይህ ነው” አላቸው።
6 በመሆኑም ሙሴ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን አቀረባቸው፤ በውኃም አጠባቸው።+
7 ከዚያም ለአሮን ረጅሙን ቀሚስ+ አጠለቀለት፤ መቀነቱንም+ አሰረለት፤ እጅጌ የሌለውን ቀሚስም+ አለበሰው፤ ኤፉዱንም+ አደረገለት፤ ኤፉዱንም ተሸምኖ በተሠራው የኤፉዱ መቀነት+ ጠበቅ አድርጎ አሰረው።
8 በመቀጠልም የደረት ኪሱን+ አደረገለት፤ በደረት ኪሱም ውስጥ ኡሪሙንና ቱሚሙን+ አስቀመጠ።
9 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ጥምጥሙን+ በራሱ ላይ አደረገለት፤ በጥምጥሙም ከፊት በኩል፣ የሚያብረቀርቀውን ጠፍጣፋ ወርቅ ይኸውም ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየውን ቅዱስ ምልክት*+ አደረገለት።
10 ሙሴም የቅብዓት ዘይቱን ወስዶ የማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ቀባቸው፤+ እንዲሁም ቀደሳቸው።
11 ከዚያም ይቀድሳቸው ዘንድ ከዘይቱ የተወሰነውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ በመርጨት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን በሙሉ እንዲሁም የውኃ ገንዳውንና ማስቀመጫውን ቀባቸው።
12 በመጨረሻም ከቅብዓት ዘይቱ የተወሰነውን ወስዶ በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰው፤ የተቀደሰም ይሆን ዘንድ ቀባው።+
13 ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት የአሮንን ወንዶች ልጆች አቀረባቸው፤ ረጅሞቹን ቀሚሶችም አለበሳቸው፤+ መቀነቶቹንም አሰረላቸው፤ የራስ ቆቡንም ደፋላቸው።
14 ከዚያም ለኃጢአት መባ የሚሆነውን በሬ አመጣ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም እጆቻቸውን ለኃጢአት መባ በሚሆነው በሬ ራስ ላይ ጫኑ።+
15 ሙሴም በሬውን አረደው፤ ደሙንም+ በጣቱ ወስዶ በሁሉም የመሠዊያው ጎኖች ላይ ያሉትን ቀንዶች ቀባ፤ መሠዊያውንም ከኃጢአት አነጻው፤ የቀረውንም ደም መሠዊያው ማስተሰረያ ይቀርብበት ዘንድ መሠዊያውን ለመቀደስ በሥሩ አፈሰሰው።
16 ከዚያም ሙሴ አንጀቱን የሸፈነውን ስብ ሁሉ፣ በጉበቱ ላይ ያለውን ሞራ፣ ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ያለውን ስብ ወስዶ በመሠዊያው ላይ እንዲጨሱ አደረገ።+
17 ሙሴም ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ከበሬው የቀረውን፣ ቆዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለው።+
18 እሱም ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን አውራ በግ አመጣ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ጫኑ።+
19 ከዚያም ሙሴ አውራውን በግ አረደው፤ ደሙንም በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ረጨው።
20 አውራውንም በግ በየብልቱ ቆራረጠው፤ ቀጥሎም ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሞራውን* አጨሰው።
21 ሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠባቸው፤ ሙሴም አውራው በግ በሙሉ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ አደረገ። ይህም ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የሚቃጠል መባ ነበር። ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነበር።
22 ከዚያም ሁለተኛውን አውራ በግ ይኸውም ለክህነት ሹመት ሥርዓት+ የሚቀርበውን አውራ በግ አመጣ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ።+
23 ከዚያም ሙሴ አውራውን በግ አረደው፤ ከደሙም የተወሰነውን ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ቀባ።
24 በመቀጠልም ሙሴ የአሮንን ወንዶች ልጆች ወደ ፊት አቀረባቸው፤ ከደሙም የተወሰነውን ወስዶ የቀኝ ጆሯቸውን ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ቀባ፤ የቀረውን ደም ግን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ረጨው።+
25 ከዚያም ስቡን፣ ላቱን፣ አንጀቱን የሚሸፍነውን ስብ በሙሉ፣ የጉበቱን ሞራ፣ ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ያለውን ስብ እንዲሁም ቀኝ እግሩን ወሰደ።+
26 በይሖዋ ፊት ካለው ቂጣዎች ከተቀመጡበት ቅርጫት ውስጥም እርሾ ያልገባበት የቀለበት ቅርጽ ያለው አንድ ዳቦ፣+ ዘይት የተቀባ የቀለበት ቅርጽ ያለው አንድ ዳቦና+ አንድ ስስ ቂጣ ወሰደ። ከዚያም በስቦቹና በቀኝ እግሩ ላይ አደረጋቸው።
27 በመቀጠልም ሁሉንም በአሮን መዳፍና በወንዶች ልጆቹ መዳፍ ላይ አስቀመጣቸው፤ በይሖዋ ፊት እንደሚወዘወዝ መባም ወዲያና ወዲህ ወዘወዛቸው።
28 ከዚያም ሙሴ ከእጃቸው ላይ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ባለው በሚቃጠለው መባ ላይ እንዲጨሱ አደረገ። እነዚህም ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ የሚሰጡ የክህነት ሹመት መሥዋዕት ናቸው። ይህም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነበር።
29 ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በይሖዋ ፊት እንደሚወዘወዝ መባ ወዲያና ወዲህ ወዘወዘው።+ ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረትም ለክህነት ሹመት ሥርዓት ከሚቀርበው አውራ በግ ላይ ይህ የእሱ ድርሻ ሆነ።+
30 ሙሴም ከቅብዓት ዘይቱና+ በመሠዊያው ላይ ካለው ደም የተወሰነውን ወስዶ በአሮንና በልብሶቹ እንዲሁም ከእሱ ጋር በነበሩት ወንዶች ልጆቹና በወንዶች ልጆቹ ልብሶች ላይ ረጨው። በዚህ መንገድ አሮንንና ልብሶቹን እንዲሁም ወንዶች ልጆቹንና+ ልብሶቻቸውን ቀደሰ።+
31 ከዚያም ሙሴ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “ሥጋውን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ቀቅሉት፤+ ‘አሮንና ወንዶች ልጆቹ ይበሉታል’ ተብዬ በታዘዝኩት መሠረት ሥጋውንም ሆነ በክህነት ሹመት ሥርዓቱ ቅርጫት ውስጥ ያለውን ቂጣ እዚያ ትበሉታላችሁ።+
32 ከሥጋውም ሆነ ከቂጣው የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ።+
33 ለክህነት ሹመታችሁ ሥርዓት የተመደቡት ቀናት እስከሚያበቁ ድረስ ይኸውም ለሰባት ቀን ያህል በመገናኛ ድንኳኑ ደጃፍ ቆዩ፤ ምክንያቱም እናንተን ካህን አድርጎ መሾም* ሰባት ቀን ይፈጃል።+
34 ለእናንተ ለማስተሰረይ+ ዛሬ ያደረግነውን ነገር እንድናደርግ ይሖዋ አዟል።
35 በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ቀንና ሌሊት ለሰባት ቀን ያህል ትቆያላችሁ፤+ እንዳትሞቱም ለይሖዋ የገባችሁትን ግዴታ ፈጽሙ፤+ ምክንያቱም እንዲህ እንዳደርግ ታዝዣለሁ።”
36 አሮንና ወንዶች ልጆቹም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ያዘዛቸውን ነገሮች በሙሉ አደረጉ።