ዘሌዋውያን 9:1-24

  • አሮን መባዎችን አቀረበ (1-24)

9  በስምንተኛውም ቀን+ ሙሴ አሮንን፣ ወንዶች ልጆቹንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠራ።  አሮንንም እንዲህ አለው፦ “ለኃጢአት መባ+ አንድ ጥጃ፣ ለሚቃጠል መባ ደግሞ አንድ አውራ በግ ለራስህ ውሰድ፤ እንከን የሌለባቸው ይሁኑ፤ በይሖዋም ፊት አቅርባቸው።  እስራኤላውያንን ግን እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ‘ለኃጢአት መባ አንድ ተባዕት ፍየል፣ ለሚቃጠል መባ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸውና እንከን የሌለባቸው አንድ ጥጃና አንድ የበግ ጠቦት ውሰዱ፤  የኅብረት መሥዋዕት+ ሆነው በይሖዋ ፊት እንዲሠዉም አንድ በሬና አንድ አውራ በግ ውሰዱ፤ እንዲሁም በዘይት የተለወሰ የእህል መባ+ አቅርቡ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ዛሬ ለእናንተ ይገለጣል።’”+  ስለዚህ ሙሴ ያዘዛቸውን ነገሮች በሙሉ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ፊት አመጡ። ከዚያም መላው ማኅበረሰብ መጥቶ በይሖዋ ፊት ቆመ።  ሙሴም “የይሖዋ ክብር ይገለጥላችሁ+ ዘንድ ይሖዋ እንድታደርጉት ያዘዛችሁ ነገር ይህ ነው” አለ።  ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኃጢአት መባህንና+ የሚቃጠል መባህን አቅርብ፤ ለራስህና ለቤትህም አስተሰርይ፤+ ይሖዋ ባዘዘውም መሠረት የሕዝቡን መባ አቅርብ፤+ እንዲሁም ለእነሱ አስተሰርይ።”+  አሮንም ወዲያው ወደ መሠዊያው ቀርቦ ስለ ራሱ የኃጢአት መባ ሆኖ የሚቀርበውን ጥጃ አረደ።+  ከዚያም ወንዶች ልጆቹ ደሙን አቀረቡለት፤+ እሱም ጣቱን ደሙ ውስጥ በመንከር የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ሥር አፈሰሰው።+ 10  ይሖዋ ሙሴን ባዘዘውም መሠረት ከኃጢአት መባው ላይ ስቡን፣ ኩላሊቶቹንና በጉበቱ ላይ ያለውን ሞራ ወስዶ በመሠዊያው ላይ እንዲጨሱ አደረገ።+ 11  ሥጋውንና ቆዳውንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለው።+ 12  ከዚያም የሚቃጠል መባ ሆኖ የሚቀርበውን እንስሳ አረደው፤ ወንዶች ልጆቹም ደሙን ሰጡት፤ እሱም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ረጨው።+ 13  እነሱም የሚቃጠለውን መባ ብልቶች ከነጭንቅላቱ ሰጡት፤ እሱም በመሠዊያው ላይ እንዲጨሱ አደረገ። 14  በተጨማሪም ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን አጠባቸው፤ በመሠዊያው ላይ ባለው በሚቃጠለው መባ ላይም እንዲጨሱ አደረገ። 15  በመቀጠልም የሕዝቡን መባ አቀረበ፤ ለሕዝቡ የኃጢአት መባ ሆኖ የሚቀርበውን ፍየል ወስዶ አረደው፤ እንደ መጀመሪያው ሁሉ በዚህኛውም የኃጢአት መባ አቀረበ። 16  ከዚያም የሚቃጠለውን መባ አቀረበ፤ በተለመደውም አሠራር መሠረት አቀረበው።+ 17  በመቀጠልም የእህል መባውን+ አቀረበ፤ ከላዩ ላይም እፍኝ ሙሉ አንስቶ ጠዋት ላይ ከሚቀርበው የሚቃጠል መባ በተጨማሪ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ አደረገ።+ 18  በኋላም ለሕዝቡ የኅብረት መሥዋዕት የሚሆኑትን በሬውንና አውራውን በግ አረዳቸው። ወንዶች ልጆቹም ደሙን ሰጡት፤ እሱም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ረጨው።+ 19  ከዚያም የበሬውን ስቦች፣+ የአውራውን በግ ላት፣ ሆድ ዕቃውን የሸፈነውን ስብ፣ ኩላሊቶቹንና የጉበቱን ሞራ+ 20  ማለትም ስቡን ሁሉ በፍርምባዎቹ ላይ አደረጉ፤ ስቡም ሁሉ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ አደረገ።+ 21  ሆኖም አሮን ፍርምባዎቹንና ቀኝ እግሩን ልክ ሙሴ ባዘዘው መሠረት እንደሚወዘወዝ መባ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ወዘወዛቸው።+ 22  ከዚያም አሮን እጆቹን ወደ ሕዝቡ በማንሳት ባረካቸው፤+ የኃጢአት መባውን፣ የሚቃጠል መባውንና የኅብረት መሥዋዕቶቹን ካቀረበ በኋላ ወረደ። 23  በመጨረሻም ሙሴና አሮን ወደ መገናኛ ድንኳኑ ገቡ፤ ከዚያም ወጥተው ሕዝቡን ባረኩ።+ በዚህ ጊዜ የይሖዋ ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ፤+ 24  እሳትም ከይሖዋ ፊት ወጥቶ+ በመሠዊያው ላይ ያለውን የሚቃጠል መባና ስብ በላ። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያይ እልል አለ፤ በግንባሩም መሬት ላይ ተደፋ።+

የግርጌ ማስታወሻ