ዘኁልቁ 13:1-33

  • አሥራ ሁለቱ ሰላዮች ወደ ከነአን ተላኩ (1-24)

  • አሥሩ ሰላዮች ያመጡት መጥፎ ወሬ (25-33)

13  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦  “ለእስራኤላውያን የምሰጠውን የከነአንን ምድር እንዲሰልሉ ሰዎችን ላክ። ከእያንዳንዱ የአባቶች ነገድ አንድ አንድ ሰው ይኸውም ከመካከላቸው አለቃ+ የሆነውን ሰው ትልካለህ።”+  በመሆኑም ሙሴ ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ከፋራን ምድረ በዳ+ ላካቸው። ሰዎቹ በሙሉ የእስራኤላውያን መሪዎች ነበሩ።  ስማቸውም የሚከተለው ነው፦ ከሮቤል ነገድ የዛኩር ልጅ ሻሙአ፣  ከስምዖን ነገድ የሆሪ ልጅ ሻፋጥ፣  ከይሁዳ ነገድ የየፎኒ ልጅ ካሌብ፣+  ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግዓል፣  ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ ሆሺአ፣+  ከቢንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፓልጢ፣ 10  ከዛብሎን ነገድ የሶዲ ልጅ ጋዲኤል፣ 11  ከዮሴፍ+ ነገድ መካከል ለምናሴ+ ነገድ የሱሲ ልጅ ጋዲ፣ 12  ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ አሚዔል፣ 13  ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፣ 14  ከንፍታሌም ነገድ የዎፍሲ ልጅ ናህቢ 15  እንዲሁም ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጌኡዔል። 16  ሙሴ ምድሪቱን እንዲሰልሉ የላካቸው ሰዎች ስም ይህ ነው። ሙሴም ለነዌ ልጅ ለሆሺአ፣ ኢያሱ*+ የሚል ስም አወጣለት። 17  ሙሴ የከነአንን ምድር እንዲሰልሉ ሰዎቹን ሲልካቸው እንዲህ አላቸው፦ “በዚህ አድርጋችሁ ወደ ኔጌብ አቅኑ፤ ከዚያም ወደ ተራራማው አካባቢ ሂዱ።+ 18  ምድሪቱ ምን እንደምትመስል፣+ ነዋሪዎቿም ብርቱ ወይም ደካማ፣ ጥቂት ወይም ብዙ መሆናቸውን እዩ፤ 19  እንዲሁም ምድሪቱ መልካም ወይም መጥፎ መሆኗን ከተሞቹም በግንብ የታጠሩ ወይም ያልታጠሩ መሆናቸውን ተመልከቱ። 20  ምድሪቱም ለም* ወይም ደረቅ* መሆኗን፣+ በዚያም ዛፎች መኖር አለመኖራቸውን አጣሩ። እንዲሁም በድፍረት+ ከምድሪቱ ፍሬ ጥቂት ይዛችሁ ኑ።” ደግሞም ጊዜው የመጀመሪያው የወይን ፍሬ የሚደርስበት ወቅት ነበር።+ 21  ስለዚህ ሰዎቹ ወጥተው ምድሪቱን ከጺን ምድረ በዳ+ አንስተው በሌቦሃማት*+ አቅራቢያ እስከምትገኘው እስከ ሬሆብ+ ድረስ ሰለሉ። 22  በኔጌብ በኩል ሽቅብ ሲወጡም ኤናቃውያኑ+ አሂማን፣ ሸሻይ እና ታልማይ+ ወደሚኖሩበት ወደ ኬብሮን+ ደረሱ። ኬብሮን የተቆረቆረችው በግብፅ ያለችው ጾዓን ከመቆርቆሯ ከሰባት ዓመት በፊት ነበር። 23  ወደ ኤሽኮል ሸለቆ*+ በደረሱ ጊዜ የወይን ዘለላዎችን ያንዠረገገ አንድ ቅርንጫፍ ከዚያ ቆረጡ፤ ከሰዎቹም መካከል ሁለቱ በዱላ ተሸከሙት፤ በተጨማሪም ጥቂት የሮማን ፍሬዎችንና የበለስ ፍሬዎችን ያዙ።+ 24  እስራኤላውያን ከዚያ በቆረጡት ዘለላ የተነሳ ያን ቦታ የኤሽኮል* ሸለቆ*+ ብለው ጠሩት። 25  ምድሪቱንም ሰልለው ከ40 ቀን+ በኋላ ተመለሱ። 26  በቃዴስ+ ባለው በፋራን ምድረ በዳ ወደሚገኙት ወደ ሙሴ፣ ወደ አሮንና ወደ መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ተመልሰው መጡ። ያዩትንም ሁሉ ለመላው ማኅበረሰብ ተናገሩ፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። 27  ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “ወደላክኸን ምድር ገብተን ነበር፤ በእርግጥም ምድሪቱ ወተትና ማር የምታፈስ ናት፤+ የምድሪቱም ፍሬ+ ይህን ይመስላል። 28  ይሁንና በምድሪቱ የሚኖሩት ሰዎች ብርቱዎች ናቸው፤ በግንብ የታጠሩት ከተሞችም ቢሆኑ በጣም ታላላቅ ናቸው። ደግሞም ኤናቃውያንን በዚያ አይተናል።+ 29  አማሌቃውያን+ በኔጌብ+ ምድር ይኖራሉ፤ ሂታውያን፣ ኢያቡሳውያንና+ አሞራውያን+ ደግሞ በተራራማው አካባቢ ይኖራሉ፤ በባሕሩ አካባቢና+ በዮርዳኖስ ዳርቻ ደግሞ ከነአናውያን+ ይኖራሉ።” 30  ከዚያም ካሌብ “በድፍረት እንውጣ፤ ድል እንደምናደርግ ምንም ጥርጥር ስለሌለው ምድሪቱን እንወርሳለን” በማለት በሙሴ ፊት የቆመውን ሕዝብ ሊያረጋጋ ሞከረ።+ 31  ከእሱ ጋር የወጡት ሰዎች ግን “ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎች ስለሆኑ ወጥተን ልንዋጋቸው አንችልም” አሉ።+ 32  እንዲሁም የሰለሏትን ምድር በተመለከተ ለእስራኤላውያን እንዲህ የሚል መጥፎ ወሬ+ አወሩ፦ “በውስጧ ተዘዋውረን የሰለልናት ምድር ነዋሪዎቿን የምትበላ ምድር ናት፤ እዚያ ያየናቸውም ሰዎች በሙሉ እጅግ ግዙፎች ናቸው።+ 33  በዚያም ኔፍሊምን ይኸውም የኔፍሊም ዝርያ የሆኑትን የኤናቅን ልጆች+ አይተናል፤ እኛ ከእነሱ ጋር ስንነጻጸር በእኛም ሆነ በእነሱ ዓይን ልክ እንደ ፌንጣ ነበርን።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የሆሹአ።” “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ያልሰባች።”
ቃል በቃል “የሰባች።”
ወይም “በሃማት መግቢያ።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
“የወይን ዘለላ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”