ዘኁልቁ 20:1-29
20 በመጀመሪያው ወር መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ወደ ጺን ምድረ በዳ መጣ፤ ሕዝቡም በቃዴስ+ ተቀመጠ። ሚርያም+ የሞተችውም ሆነ የተቀበረችው በዚያ ነበር።
2 በዚያ ለማኅበረሰቡ የሚሆን ውኃ አልነበረም፤+ ሕዝቡም ሙሴንና አሮንን በመቃወም በእነሱ ላይ ተሰበሰበ።
3 ሕዝቡም እንዲህ በማለት ከሙሴ ጋር ተጣላ፦+ “ምነው ወንድሞቻችን በይሖዋ ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ሞተን ባረፍነው ኖሮ!
4 እኛም ሆንን ከብቶቻችን እዚህ እንድናልቅ የይሖዋን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት ለምንድን ነው?+
5 ከግብፅ አውጥታችሁ ወደዚህ መጥፎ ቦታ እየመራችሁ ያመጣችሁን ለምንድን ነው?+ ይህ ቦታ እህልም ሆነ በለስ፣ የወይን ፍሬም ሆነ ሮማን የሌለበት ነው፤ የሚጠጣ ውኃም የለም።”+
6 ከዚያም ሙሴና አሮን ከጉባኤው ፊት ተነስተው ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በመሄድ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ፤ የይሖዋም ክብር ተገለጠላቸው።+
7 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
8 “በትሩን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮንም ማኅበረሰቡን ሰብስቡ፤ ዓለቱም ውኃውን እንዲሰጥ በእነሱ ፊት ተናገሩት፤ አንተም ከዓለቱ ውኃ ታፈልቅላቸዋለህ፤ ማኅበረሰቡም ሆነ ከብቶቻቸው እንዲጠጡም ትሰጣቸዋለህ።”+
9 ሙሴም ልክ እንደታዘዘው በትሩን ከይሖዋ ፊት ወሰደ።+
10 ከዚያም ሙሴና አሮን ጉባኤውን በዓለቱ ፊት ሰበሰቡ፤ እሱም “እናንተ ዓመፀኞች ስሙ! ከዚህ ዓለት ለእናንተ ውኃ ማፍለቅ አለብን?” አላቸው።+
11 ሙሴም ይህን ካለ በኋላ እጁን አንስቶ ዓለቱን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው፤ ውኃውም ይንዶለዶል ጀመር፤ ማኅበረሰቡና ከብቶቻቸውም ጠጡ።+
12 በኋላም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “በእስራኤል ሕዝብ ፊት በእኔ ስላልታመናችሁና እኔን ስላልቀደሳችሁ ይህን ጉባኤ እኔ ወደምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም።”+
13 ይሖዋ በመካከላቸው ይቀደስ ዘንድ እስራኤላውያን ከእሱ ጋር የተጣሉባቸው የመሪባ*+ ውኃዎች እነዚህ ናቸው።
14 ከዚያም ሙሴ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት ከቃዴስ መልእክተኞችን ላከ፦+ “ወንድምህ እስራኤል+ እንዲህ ይላል፦ ‘መቼም የደረሰብንን መከራ ሁሉ በሚገባ ታውቃለህ።
15 አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወርደው ነበር፤+ እኛም በግብፅ ለብዙ ዓመታት* ኖርን፤+ ግብፃውያኑም በእኛም ሆነ በአባቶቻችን ላይ በደል ይፈጽሙብን ነበር።+
16 በመጨረሻም ወደ ይሖዋ ጮኽን፤+ እሱም ጩኸታችንን ሰምቶ መልአክ በመላክ+ ከግብፅ አወጣን፤ ይኸው አሁን ድንበርህ ላይ ባለችው በቃዴስ ከተማ እንገኛለን።
17 እናም አሁን እባክህ በምድርህ እንለፍ። በየትኛውም እርሻ ወይም በየትኛውም የወይን ቦታ አቋርጠን አንሄድም፤ ከየትኛውም ጉድጓድ ውኃ አንጠጣም። ክልልህን አቋርጠን እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር ሳንል በንጉሡ መንገድ እንሄዳለን።’”+
18 ኤዶም ግን “ክልላችንን አቋርጠህ ማለፍ አትችልም። እንዲህ ካደረግክ ወጥቼ በሰይፍ እገጥምሃለሁ” አለው።
19 እስራኤላውያንም መልሰው እንዲህ አሉት፦ “አውራ ጎዳናውን ይዘን እናቀናለን፤ እኛም ሆን ከብቶቻችን ከውኃህ ከጠጣን ዋጋውን እንከፍልሃለን።+ በእግራችን አልፈን ከመሄድ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር አንፈልግም።”+
20 እሱ ግን አሁንም “በዚህ ማለፍ አትችልም”+ ሲል መልስ ሰጠ። ከዚያም ኤዶም ብዙ ሕዝብና ኃያል ሠራዊት* ይዞ ሊገጥመው ወጣ።
21 በዚህ መንገድ ኤዶም እስራኤል በክልሉ እንዳያልፍ ከለከለ፤ ስለዚህ እስራኤል ከእሱ ተመለሰ።+
22 የእስራኤል ሕዝብ ይኸውም መላው ማኅበረሰብ ከቃዴስ ተነስቶ ወደ ሆር ተራራ+ መጣ።
23 ከዚያም ይሖዋ በኤዶም ምድር ወሰን ላይ ባለው በሆር ተራራ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦
24 “አሮን ወደ ወገኖቹ ይሰበሰባል።*+ ሁለታችሁም ከመሪባ ውኃ ጋር በተያያዘ በሰጠሁት ትእዛዝ ላይ ስላመፃችሁ ለእስራኤላውያን ወደምሰጣት ምድር አይገባም።+
25 አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሆር ተራራ ውጣ።
26 የአሮንን ልብስ አውልቀህ+ ልጁን አልዓዛርን+ አልብሰው፤ አሮንም በዚያ ይሞታል።”*
27 በመሆኑም ሙሴ ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ እነሱም መላው ማኅበረሰብ እያየ ወደ ሆር ተራራ ወጡ።
28 ሙሴም የአሮንን ልብስ አውልቆ ልጁን አልዓዛርን አለበሰው። ከዚያም አሮን እዚያው ተራራው አናት ላይ ሞተ።+ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ወረዱ።
29 መላው ማኅበረሰብም አሮን መሞቱን አየ፤ በዚህ ጊዜ የእስራኤል ቤት በሙሉ ለአሮን 30 ቀን አለቀሰለት።+