ዘኁልቁ 25:1-18

  • እስራኤላውያን ከሞዓብ ሴቶች ጋር የፆታ ብልግና ፈጸሙ (1-5)

  • ፊንሃስ እርምጃ ወሰደ (6-18)

25  እስራኤላውያን በሺቲም+ ይኖሩ በነበረበት ጊዜ ሕዝቡ ከሞዓብ ሴቶች ጋር የፆታ ብልግና መፈጸም ጀመረ።+  ሴቶቹም ለአማልክታቸው ወደተሠዉት መሥዋዕቶች ሕዝቡን ጠሩ፤+ ሕዝቡም ከመሥዋዕቱ መብላት እንዲሁም ለእነሱ አማልክት መስገድ ጀመረ።+  ስለዚህ እስራኤል የፌጎርን ባአል በማምለክ ተባበረ፤*+ ይሖዋም በእስራኤል ላይ እጅግ ተቆጣ።  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እየነደደ ያለው የይሖዋ ቁጣ ከእስራኤል ላይ እንዲመለስ የዚህን ሕዝብ መሪዎች* ሁሉ ወስደህ በጠራራ ፀሐይ* በይሖዋ ፊት ስቀላቸው።”  ከዚያም ሙሴ የእስራኤልን ዳኞች+ “እያንዳንዳችሁ በፌጎር ባአል አምልኮ የተባበረውን* የየራሳችሁን ሰው ግደሉ” አላቸው።+  ሆኖም ልክ በዚህ ጊዜ አንድ እስራኤላዊ፣ ሙሴና በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ እያለቀሰ ያለው የእስራኤል ማኅበረሰብ በሙሉ እያዩት አንዲት ምድያማዊት ሴት+ ይዞ ወደ ወንድሞቹ መጣ።  የካህኑ የአሮን ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስ+ ይህን ሲመለከት ከማኅበረሰቡ መሃል ወዲያው ብድግ ብሎ ጦር አነሳ።  ከዚያም እስራኤላዊውን ተከትሎ ወደ ድንኳኑ በመግባት ሁለቱንም ወጋቸው፤ እስራኤላዊውን ወጋው፤ እሷንም ሆዷ* ላይ ወጋት። በዚህ ጊዜ መቅሰፍቱ ከእስራኤል ልጆች ላይ ተወገደ።+  በመቅሰፍቱ የሞቱት ሰዎች 24,000 ነበሩ።+ 10  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 11  “የካህኑ የአሮን ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስ+ በመካከላቸው እኔን የሚቀናቀነኝን ማንኛውንም ነገር በቸልታ ባለማለፉ ቁጣዬ ከእስራኤል ሕዝብ ላይ እንዲመለስ አድርጓል።+ ስለዚህ እስራኤላውያንን እኔን ብቻ ለምን አላመለካችሁም ብዬ ጠራርጌ አላጠፋኋቸውም።+ 12  በዚህም የተነሳ ከእሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እንደምገባ ንገረው። 13  ይህም አምላኩን የሚቀናቀነውን ማንኛውንም ነገር በቸልታ ባለማለፉ+ እንዲሁም ለእስራኤል ሕዝብ በማስተሰረዩ ለእሱና ከእሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቹ+ ዘላቂ የክህነት ቃል ኪዳን ሆኖ ያገለግላል።” 14  ከምድያማዊቷ ሴት ጋር የተገደለው ሟቹ እስራኤላዊ የስምዖናውያን አባቶች ቤት አለቃ የሆነው የሳሉ ልጅ ዚምሪ ነበር። 15  የተገደለችውም ምድያማዊት ሴት የጹር+ ልጅ ኮዝቢ ነበረች፤ ጹር በምድያም ካሉት የአባቶች ቤት ጎሳዎች የአንዱ መሪ ነበር።+ 16  በኋላም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 17  “ምድያማውያንን አንገላቷቸው፤ እንዲሁም ፍጇቸው፤+ 18  ምክንያቱም እነሱ ከፌጎርና+ ከእህታቸው ከኮዝቢ ጋር በተያያዘ በፈጸሙባችሁ ተንኮል የተነሳ አንገላተዋችኋል፤ ኮዝቢ ከፌጎር ጋር በተያያዘ የተከሰተው መቅሰፍት በመጣበት ዕለት+ የተገደለች የምድያማዊው አለቃ ልጅ ነች።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ከፌጎር ባአል ጋር ተጣበቀ።”
ቃል በቃል “ራሶች።”
ቃል በቃል “በፀሐይ ፊት።”
ወይም “ከፌጎር ባአል ጋር የተጣበቀውን።”
“ብልቷ” ላቲን ቩልጌት። “ማህፀኗ” የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም።