ዘኁልቁ 30:1-16

  • አንድ ወንድ ስእለት ቢሳል (1, 2)

  • አንዲት ወጣት ወይም አንዲት ሴት ስእለት ብትሳል (3-16)

30  ከዚያም ሙሴ የእስራኤላውያን የነገድ መሪዎችን+ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ የሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፦  አንድ ሰው ለይሖዋ ስእለት ቢሳል+ ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ ራሱን* ግዴታ ውስጥ ቢያስገባ+ ቃሉን ማጠፍ የለበትም።+ አደርገዋለሁ ብሎ የማለውን ነገር ሁሉ መፈጸም አለበት።+  “በአባቷ ቤት የምትኖር አንዲት ወጣት ለይሖዋ ስእለት ብትሳል ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ ራሷን በመሐላ ግዴታ ውስጥ ብታስገባ  አባቷ ስእለት መሳሏን ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ ራሷን* በመሐላ ግዴታ ውስጥ ማስገባቷን ሰምቶ ካልተቃወማት ስእለቶቿ በሙሉ ይጸናሉ፤ እንዲሁም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባችው ማንኛውም ግዴታ ይጸናል።  ሆኖም አባቷ ስእለት መሳሏን ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ ራሷን በመሐላ ግዴታ ውስጥ ማስገባቷን ሲሰማ ቢከለክላት ስእለቱ አይጸናም። አባቷ ስለከለከላት ይሖዋ ይቅር ይላታል።+  “ይሁን እንጂ ይህች ሴት ስእለት ተስላ ወይም ሳታስብበት ራሷን ግዴታ ውስጥ የሚያስገባ ቃል ተናግራ እያለ ባል ብታገባ፣  ባሏም ይህን ቢሰማና በሰማበት ቀን ዝም ቢላት ስእለቶቿ ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባቻቸው ግዴታዎች ይጸናሉ።  ሆኖም ባሏ ይህን በሰማበት ቀን ቢከለክላት የተሳለችውን ስእለት ወይም ሳታስብበት ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችበትን ቃል ያፈርሰዋል፤+ ይሖዋም ይቅር ይላታል።  “ሆኖም አንዲት መበለት ወይም ከባሏ የተፋታች አንዲት ሴት ስእለት ብትሳል ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች በሙሉ ይጸኑባታል። 10  “ይሁን እንጂ አንዲት ሴት ስእለት የተሳለችው ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ ራሷን በመሐላ ግዴታ ውስጥ ያስገባችው በባሏ ቤት እያለች ከሆነና 11  ባሏም ሰምቶ ይህን ካልተቃወማት ወይም ካልከለከላት የተሳለቻቸው ስእለቶች በሙሉ ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባቻቸው ግዴታዎች ሁሉ ይጸናሉ። 12  ይሁንና ባሏ የተሳለችውን ማንኛውንም ስእለት ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባችውን የትኛውንም ግዴታ በሰማበት ቀን ሙሉ በሙሉ ቢያፈርስባት ስእለቶቹ አይጸኑም።+ ባሏ ስእለቶቿን አፍርሷቸዋል፤ ይሖዋም ይቅር ይላታል። 13  የትኛውንም ስእለት ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባችውን ግዴታ አሊያም ራሷን* ለማጎሳቆል የገባችውን ቃል ባሏ ሊያጸናው ወይም ሊያፈርሰው ይችላል። 14  ሆኖም ባሏ ቀናት እያለፉ ሲሄዱ ጨርሶ ካልተቃወማት ስእለቶቿን በሙሉ ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባችውን ግዴታ ሁሉ አጽንቶታል ማለት ነው። ስእለት መሳሏን በሰማበት ቀን ስላልተቃወማት እንዳጸናቸው ይቆጠራል። 15  ስእለቶቹን ሰምቶ የተወሰኑ ቀናት ካለፉ በኋላ ስእለቶቹን ካፈረሰ ግን የእሷ በደል የሚያስከትላቸውን መዘዞች እሱ ይሸከማል።+ 16  “ከባልና ከሚስት እንዲሁም ከአባትና በቤቱ ከምትኖር ወጣት ልጁ ጋር በተያያዘ ይሖዋ ለሙሴ የሰጣቸው ደንቦች እነዚህ ናቸው።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሷን።”
ወይም “ነፍሷን።”