ዘኁልቁ 32:1-42

  • ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያሉ የሰፈራ መንደሮች (1-42)

32  የሮቤል ልጆችና+ የጋድ ልጆች+ እጅግ በጣም ብዙ ከብት ነበራቸው። እነሱም የያዜር+ እና የጊልያድ ምድር ለከብቶች የሚስማማ ስፍራ እንደሆነ አዩ።  በመሆኑም የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች መጥተው ሙሴን፣ ካህኑን አልዓዛርንና የማኅበረሰቡን አለቆች እንዲህ አሏቸው፦  “የአጣሮት፣ የዲቦን፣ የያዜር፣ የኒምራ፣ የሃሽቦን፣+ የኤልዓሌ፣ የሰባም፣ የነቦ+ እና የቤኦን+ ምድር  ይሖዋ በእስራኤል ማኅበረሰብ ፊት ድል ያደረገው+ ሲሆን ለከብቶች ምቹ ነው፤ አገልጋዮችህ ደግሞ ብዙ ከብት አላቸው።”+  አክለውም እንዲህ አሉ፦ “እንግዲህ በፊትህ ሞገስ ካገኘን ይህ ምድር ለአገልጋዮችህ ርስት ተደርጎ ይሰጥ። ዮርዳኖስን እንድንሻገር አታድርገን።”  ከዚያም ሙሴ የጋድን ልጆችና የሮቤልን ልጆች እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት እንዲሄዱ ትፈልጋላችሁ?  የእስራኤል ልጆች ይሖዋ ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ ተስፋ የምታስቆርጧቸው ለምንድን ነው?  አባቶቻችሁ ምድሪቱን እንዲያዩ ከቃዴስበርኔ በላክኋቸው ጊዜ ያደረጉት ይህንኑ ነበር።+  ወደ ኤሽኮል ሸለቆ*+ አቅንተው ምድሪቱን ካዩ በኋላ የእስራኤልን ሕዝብ ይሖዋ ወደሚሰጠው ምድር እንዳይገባ ተስፋ አስቆረጡት።+ 10  በዚያ ቀን የይሖዋ ቁጣ ነደደ፤ እንዲህም ሲል ማለ፦+ 11  ‘ከግብፅ ምድር ከወጡት መካከል 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የማልኩላቸውን+ ምድር አያዩም፤+ ምክንያቱም በሙሉ ልባቸው አልተከተሉኝም፤ 12  ይሖዋን በሙሉ ልባቸው ከተከተሉት+ ከቀኒዛዊው ከየፎኒ ልጅ ከካሌብና+ ከነዌ ልጅ ከኢያሱ+ በስተቀር አንዳቸውም ምድሪቱን አያዩም።’ 13  በመሆኑም የይሖዋ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ በይሖዋ ፊት ክፉ ድርጊት የፈጸመው ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ+ ለ40 ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው።+ 14  እናንተ የኃጢአተኞች ልጆች ደግሞ ይኸው በአባቶቻችሁ እግር ተተክታችሁ ይሖዋ በእስራኤል ላይ ይበልጥ እንዲቆጣ ታደርጋላችሁ። 15  እንግዲህ እናንተ እሱን ከመከተል ዞር ካላችሁ እሱም እንደገና በምድረ በዳ ይተዋቸዋል፤ እናንተም በዚህ ሁሉ ሕዝብ ላይ ጥፋት ታመጣላችሁ።” 16  በኋላም ወደ እሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲያው እዚሁ ለከብቶቻችን በድንጋይ ካብ በረት እንሥራ፤ ለልጆቻችንም ከተሞች እንገንባ። 17  ይሁን እንጂ ወደ ስፍራቸው እስክናስገባቸው ድረስ ለጦርነት ታጥቀን+ በእስራኤላውያን ፊት እንሄዳለን፤ በዚህም ጊዜ ልጆቻችን ከምድሪቱ ነዋሪዎች ተጠብቀው በተመሸጉት ከተሞች ውስጥ ይኖራሉ። 18  እኛም እያንዳንዱ እስራኤላዊ የራሱን ርስት እስኪያገኝ ድረስ ወደ ቤታችን አንመለስም።+ 19  እኛ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው አካባቢ ርስት ካገኘን ከዮርዳኖስ ማዶና ከዚያ ባሻገር ባለው አካባቢ ከእነሱ ጋር ርስት አንካፈልም።”+ 20  ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ብታደርጉ ይኸውም በጦርነቱ ለመካፈል በይሖዋ ፊት ታጥቃችሁ ብትነሱ+ 21  እንዲሁም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያስወግድ ድረስ+ እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን ይዛችሁ በይሖዋ ፊት ዮርዳኖስን ብትሻገሩና 22  ምድሪቱ በይሖዋ ፊት እስክትገዛ ድረስ+ በዚያ ብትቆዩ፣ ከዚያ በኋላ መመለስ ትችላላችሁ፤+ በይሖዋም ሆነ በእስራኤላውያን ዘንድ ከበደል ነፃ ትሆናላችሁ። ከዚያም ይህች ምድር በይሖዋ ፊት የእናንተ ርስት ትሆናለች።+ 23  ይህን ባታደርጉ ግን በይሖዋ ላይ ኃጢአት ትሠራላችሁ። ለሠራችሁትም ኃጢአት ተጠያቂ እንደምትሆኑ እወቁ። 24  ስለዚህ ለልጆቻችሁ ከተሞችን መገንባትና ለመንጎቻችሁ በረት መሥራት የምትችሉ+ ቢሆንም የገባችሁትን ቃል መፈጸም ይኖርባችኋል።” 25  የጋድ ልጆችና የሮቤል ልጆችም ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እኛ አገልጋዮችህ ጌታችን እንዳዘዘን እናደርጋለን። 26  ልጆቻችን፣ ሚስቶቻችን፣ ከብቶቻችንና እንስሶቻችን በሙሉ በጊልያድ ከተሞች ውስጥ ይቆያሉ፤+ 27  ሆኖም እኛ አገልጋዮችህ ይኸውም በይሖዋ ፊት ጦርነት ለመግጠም የታጠቅን እያንዳንዳችን ልክ ጌታችን በተናገረው መሠረት እንሻገራለን።”+ 28  በመሆኑም ሙሴ ለካህኑ ለአልዓዛር፣ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ነገዶች የአባቶች ቤት መሪዎች እነሱን በተመለከተ ትእዛዝ ሰጠ። 29  ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “የጋድ ልጆችና የሮቤል ልጆች ይኸውም በይሖዋ ፊት ለጦርነት የታጠቀ እያንዳንዱ ሰው ከእናንተ ጋር ዮርዳኖስን ከተሻገረ፣ ምድሪቱም በፊታችሁ ከተገዛች የጊልያድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጧቸዋላችሁ።+ 30  ሆኖም የጦር መሣሪያ ታጥቀው ከእናንተ ጋር ካልተሻገሩ በከነአን ምድር በመካከላችሁ ይኖራሉ።” 31  በዚህ ጊዜ የጋድ ልጆችና የሮቤል ልጆች እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይሖዋ ለአገልጋዮችህ የተናገረውን እንፈጽማለን። 32  እኛ ራሳችን የጦር መሣሪያ ታጥቀን በይሖዋ ፊት ወደ ከነአን ምድር እንሻገራለን፤+ የምንወርሰው ርስት ግን ከዮርዳኖስ ወዲህ ያለውን ይሆናል።” 33  ስለዚህ ሙሴ ለጋድ ልጆችና ለሮቤል ልጆች+ እንዲሁም ለዮሴፍ ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ+ የአሞራውያንን ንጉሥ የሲሖንን ግዛትና+ የባሳንን ንጉሥ የኦግን ግዛት+ ይኸውም በክልሎቹ ውስጥ የሚገኙ ከተሞች ይዞታ የሆነውን ምድር እንዲሁም በዙሪያው ባለው ምድር ያሉትን ከተሞች ሰጣቸው። 34  የጋድ ልጆችም ዲቦን፣+ አጣሮት፣+ አሮዔር፣+ 35  አትሮትሾፋን፣ ያዜር፣+ ዮግበሃ፣+ 36  ቤትኒምራ+ እና ቤትሃራን+ የተባሉትን የተመሸጉ ከተሞች ገነቡ፤ ለመንጎቹም በድንጋይ ካብ በረት ሠሩ። 37  የሮቤል ልጆች ደግሞ ሃሽቦንን፣+ ኤልዓሌን፣+ ቂርያታይምን፣+ 38  ስማቸው የተለወጠውን ነቦን+ እና በዓልመዖንን+ እንዲሁም ሲብማን ገነቡ፤ እነሱም መልሰው ለገነቧቸው ከተሞች አዲስ ስም አወጡላቸው። 39  የምናሴ ልጅ የማኪር+ ልጆች በጊልያድ ላይ ዘምተው ምድሪቱን ያዙ፤ በዚያም ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያን አስወጧቸው። 40  በመሆኑም ሙሴ ጊልያድን ለምናሴ ልጅ ለማኪር ሰጠው፤ እሱም በዚያ መኖር ጀመረ።+ 41  የምናሴ ልጅ ያኢርም በእነሱ ላይ ዘምቶ የድንኳን ሰፈሮቻቸውን ያዘ፤ እነሱንም ሃዎትያኢር* ብሎ ጠራቸው።+ 42  ኖባህም ዘምቶ ቄናትንና በሥሯ* ያሉትን ከተሞች ያዘ፤ እነሱንም በራሱ ስም ኖባህ ብሎ ሰየማቸው።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
“የያኢር የድንኳን መንደሮች” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “በዙሪያዋ።”