ዘኁልቁ 35:1-34
35 ይሖዋ ሙሴን በኢያሪኮ በሚገኘው በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ+ ላይ እንዲህ አለው፦
2 “እስራኤላውያንን ከሚወርሱት ርስት ላይ ለሌዋውያኑ መኖሪያ የሚሆኑ ከተሞችን እንዲሰጧቸው እዘዛቸው፤+ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን የግጦሽ መሬት ለሌዋውያኑ መስጠት አለባቸው።+
3 ከተሞቹ ለእነሱ መኖሪያ፣ የግጦሽ ቦታዎቹ ደግሞ ለከብቶቻቸውና ለዕቃዎቻቸው እንዲሁም ለሌሎች እንስሶቻቸው ይሆናሉ።
4 ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው የከተሞቹ የግጦሽ ቦታዎች ከከተማው ቅጥር በሁሉም አቅጣጫ 1,000 ክንድ* ይሆናል።
5 ከተማውን መካከል ላይ በማድረግ ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል 2,000 ክንድ፣ በደቡብ በኩል 2,000 ክንድ፣ በምዕራብ በኩል 2,000 ክንድ እንዲሁም በሰሜን በኩል 2,000 ክንድ ለኩ። እነዚህም የከተሞቻቸው የግጦሽ መሬት ይሆናሉ።
6 “ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ከተሞች ነፍስ ያጠፋ ሰው ሸሽቶ የሚሸሸግባቸውን+ 6 የመማጸኛ ከተሞችና+ ሌሎች 42 ከተሞችን ነው።
7 በጠቅላላ 48 ከተሞችን ከነግጦሽ መሬታቸው ለሌዋውያኑ ትሰጧቸዋላችሁ።+
8 ከተሞቹን የምትሰጧቸው ከእስራኤላውያን ርስት ላይ ወስዳችሁ ነው።+ ተለቅ ካለው ቡድን ላይ ብዙ ትወስዳላችሁ፤ አነስ ካለው ቡድን ላይ ደግሞ ጥቂት ትወስዳላችሁ።+ እያንዳንዱ ቡድን በወረሰው ርስት መጠን ካሉት ከተሞች ላይ የተወሰኑትን ለሌዋውያኑ መስጠት ይኖርበታል።”
9 ይሖዋ በመቀጠል ሙሴን እንዲህ አለው፦
10 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘እንግዲህ ወደ ከነአን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን ልትሻገሩ ነው።+
11 ሳያስበው ሰው የገደለ* ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው አመቺ የሆኑ የመማጸኛ ከተሞችን ለራሳችሁ ምረጡ።+
12 እነዚህ ከተሞች ነፍስ ያጠፋው ሰው በማኅበረሰቡ ፊት ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት+ እንዳይሞት ከደም ተበቃዩ+ የሚሸሸግባቸው ከተሞች ይሆኑላችኋል።
13 እናንተ የምትሰጧቸው ስድስቱ የመማጸኛ ከተሞች ለዚህ ዓላማ ያገለግላሉ።
14 የመማጸኛ ከተሞች ሆነው እንዲያገለግሉ ከዮርዳኖስ ወዲህ ሦስት ከተሞችን፣+ በከነአን ምድር ደግሞ ሦስት ከተሞችን+ ትሰጣላችሁ።
15 እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤላውያንም ሆነ ለባዕድ አገር ሰው+ አሊያም በመካከላቸው ለሚኖር ሰፋሪ ሳያስበው ሰው የገደለ* ማንኛውም ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው ከተሞች ሆነው ያገለግላሉ።+
16 “‘ሆኖም ሰውየው ግለሰቡን በብረት መሣሪያ ቢመታውና ቢገድለው ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳዩ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።+
17 ሰውየው ግለሰቡን ሊገድለው በሚችል ድንጋይ ቢመታውና ቢገድለው ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳዩ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።
18 ሰውየው ግለሰቡን ሊገድለው በሚችል ከእንጨት የተሠራ መሣሪያ ቢመታውና ቢገድለው ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳዩ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።
19 “‘ነፍሰ ገዳዩን መግደል ያለበት ደም ተበቃዩ ይሆናል። ባገኘው ጊዜ እሱ ራሱ ይግደለው።
20 አንድ ሰው ሌላውን በጥላቻ ተገፋፍቶ ቢገፈትረው ወይም ተንኮል አስቦ* የሆነ ነገር ቢወረውርበትና ግለሰቡ ቢሞት+
21 አሊያም በጥላቻ ተነሳስቶ በእጁ ቢመታውና ቢሞት መቺው ያለምንም ጥርጥር ይገደላል። እሱ ነፍሰ ገዳይ ነው። ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ባገኘው ጊዜ ይገድለዋል።
22 “‘ይሁን እንጂ ሰውየው ግለሰቡን የገፈተረው በጥላቻ ተነሳስቶ ሳይሆን ሳያስበው ከሆነ ወይም ዕቃ የወረወረበት ተንኮል አስቦ* ካልሆነ+
23 አሊያም ግለሰቡ ሳያየው ድንጋይ ቢጥልበትና ቢሞት ሆኖም ሰውየው ከግለሰቡ ጋር ጠላትነት ባይኖረውና ይህን ያደረገው እሱን ለመጉዳት አስቦ ባይሆን
24 ማኅበረሰቡ እነዚህን ደንቦች መሠረት በማድረግ በገዳዩና በደም ተበቃዩ መካከል ፍርድ ይስጥ።+
25 ማኅበረሰቡም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ታድጎ ሸሽቶበት ወደነበረው የመማጸኛ ከተማ ይመልሰው፤ እሱም በቅዱስ ዘይት የተቀባው+ ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቆይ።
26 “‘ይሁንና ገዳዩ ሸሽቶ ከገባበት የመማጸኛ ከተማ ወሰን ቢወጣና
27 ደም ተበቃዩም ገዳዩን ከመማጸኛ ከተማው ወሰን ውጭ አግኝቶ ቢገድለው በደም ዕዳ አይጠየቅም።
28 ምክንያቱም ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማው ውስጥ መቆየት ይገባዋል። ሊቀ ካህናቱ ከሞተ በኋላ ግን ገዳዩ ወደ ርስቱ መመለስ ይችላል።+
29 እነዚህም በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ፍርድ ለመስጠት እንደሚያገለግል ደንብ ይሁኗችሁ።
30 “‘ሰው* የገደለ ማንኛውም ሰው ምሥክሮች ከመሠከሩበት*+ እንደ ነፍሰ ገዳይ ተቆጥሮ ይገደል፤+ ይሁን እንጂ ማንም ሰው* አንድ ግለሰብ በሚሰጠው ምሥክርነት ብቻ በሞት መቀጣት የለበትም።
31 ሞት ለሚገባው ነፍሰ ገዳይ ሕይወት* ቤዛ አትቀበሉ፤ ምክንያቱም ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።+
32 እንዲሁም ሸሽቶ ወደ መማጸኛ ከተማው ለገባ ሰው* ሊቀ ካህናቱ ከመሞቱ በፊት ወደ ምድሩ ተመልሶ እንዲኖር ለማድረግ ቤዛ አትቀበሉ።
33 “‘ደም ምድሪቱን ስለሚበክል ያላችሁባትን ምድር አትበክሉ፤+ ደም ባፈሰሰው ሰው ደም ካልሆነ በስተቀር በምድሪቱ ላይ ለፈሰሰው ደም ስርየት ሊኖር አይችልም።+
34 የምትኖሩባትን፣ እኔም የምኖርባትን ምድር አታርክሱ፤ እኔ ይሖዋ በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁና።’”+