ዘካርያስ 12:1-14

  • ይሖዋ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ይጠብቃል (1-9)

    • ኢየሩሳሌም፣ “ከባድ ድንጋይ” (3)

  • ለተወጋው ይለቀስለታል (10-14)

12  የፍርድ መልእክት፦ “ስለ እስራኤል የተነገረው የይሖዋ ቃል።”ሰማያትን የዘረጋው፣+የምድርን መሠረት የጣለውና+የሰውን መንፈስ* በውስጡ የሠራው ይሖዋ እንዲህ ይላል፦  “እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ የምታንገዳግድ ጽዋ* አደርጋታለሁ፤ ጠላት ይሁዳንም ሆነ ኢየሩሳሌምን ይከባል።+  በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን ለሕዝቦች ሁሉ ከባድ* ድንጋይ አደርጋታለሁ። ድንጋዩን የሚያነሱት ሁሉ ክፉኛ መጎዳታቸው የማይቀር ነው፤+ የምድር ብሔራትም ሁሉ በእሷ ላይ ይሰበሰባሉ።+  በዚያ ቀን” ይላል ይሖዋ፣ “እያንዳንዱን ፈረስ በድንጋጤ፣ ጋላቢውንም በእብደት እመታለሁ። ዓይኖቼን በይሁዳ ቤት ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቦቹን ፈረሶች ሁሉ ግን አሳውራለሁ።  የይሁዳም አለቆች* በልባቸው ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ አምላካቸው ስለሆነ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ብርታታችን ናቸው’ ይላሉ።+  በዚያን ቀን የይሁዳን አለቆች በእንጨት መካከል እንዳለ የሚነድ ምድጃና በታጨደ እህል መካከል እንዳለ የሚነድ ችቦ አደርጋቸዋለሁ፤+ እነሱም በስተ ቀኝም ሆነ በስተ ግራ፣ በዙሪያቸው ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ ይበላሉ፤+ ኢየሩሳሌምም በገዛ ስፍራዋ* ይኸውም በኢየሩሳሌም ዳግመኛ የሰዎች መኖሪያ ትሆናለች።+  “የዳዊት ቤት ውበትና* የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ውበት* ከይሁዳ እጅግ የበለጠ እንዳይሆን ይሖዋ በመጀመሪያ የይሁዳን ድንኳኖች ያድናል።  በዚያ ቀን ይሖዋ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ዙሪያ መከታ ይሆናል፤+ በዚያም ቀን ከእነሱ መካከል የሚሰናከለው* እንደ ዳዊት ይሆናል፤ የዳዊትም ቤት እንደ አምላክ፣ በፊታቸውም እንደሚሄደው የይሖዋ መልአክ ይሆናል።+  ደግሞም በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጡትን ብሔራት ሁሉ ለማጥፋት ቆርጬ እነሳለሁ።+ 10  “በዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የሞገስንና የምልጃን መንፈስ አፈሳለሁ፤ እነሱም የወጉትን ያዩታል፤+ ለአንድያ ልጅም እንደሚለቀስ ያለቅሱለታል፤ ለበኩር ልጅ እንደሚለቀሰው ያለ መራራ ለቅሶም ያለቅሱለታል። 11  በዚያን ቀን በኢየሩሳሌም የሚለቀሰው ለቅሶ በመጊዶ ሜዳ፣ በሃዳድሪሞን እንደተለቀሰው ለቅሶ ታላቅ ይሆናል።+ 12  ምድሪቱም ታለቅሳለች፤ እያንዳንዱም ቤተሰብ ለየብቻው ያለቅሳል፤ የዳዊት ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ የናታን+ ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ 13  የሌዊ+ ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ የሺምአይ+ ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ 14  የቀሩትም ቤተሰቦች በሙሉ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው ያለቅሳሉ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “እስትንፋስ።”
ወይም “ጎድጓዳ ሳህን።”
ወይም “ለመሸከም የሚያስቸግር።”
ቃል በቃል “ሺኮች።” የነገድ አለቃ የሆነ ሰው “ሺክ” ተብሎ ይጠራ ነበር።
ወይም “በተገቢው ቦታዋ።”
ወይም “የዳዊት ቤት ግርማና።”
ወይም “ግርማ።”
ወይም “እጅግ ደካማ የሆነው።”