ዘካርያስ 4:1-14

  • ራእይ 5፦ መቅረዝና ሁለት የወይራ ዛፎች (1-14)

    • ‘በመንፈሴ እንጂ፣ በጉልበት አይደለም’ (6)

    • ሥራው በትንሹ የተጀመረበትን ቀን አትናቁ (10)

4  ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ተመልሶ መጥቶ አንድን ሰው ከእንቅልፉ እንደሚቀሰቅስ ቀሰቀሰኝ።  ከዚያም “የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም እንዲህ አልኩት፦ “እነሆ፣ ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተሠራና ላዩ ላይ ሳህን ያለበት መቅረዝ+ ይታየኛል። በላዩ ላይ ሰባት መብራቶች፣ አዎ ሰባት መብራቶች አሉበት፤+ አናቱ ላይ ያሉት ሰባት መብራቶችም ሰባት ቱቦዎች አሏቸው።  ከጎኑም አንዱ ከሳህኑ በስተ ቀኝ፣ አንዱ ደግሞ በስተ ግራ የቆሙ ሁለት የወይራ ዛፎች አሉ።”+  ከዚያም ሲያነጋግረኝ የነበረውን መልአክ “ጌታዬ ሆይ፣ የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምንድን ነው?” በማለት ጠየቅኩት።  ከእኔ ጋር ሲነጋገር የነበረውም መልአክ “የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምን እንደሆነ አታውቅም?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም “ጌታዬ ሆይ፣ አላውቅም” ብዬ መለስኩለት።  በዚህ ጊዜ እንዲህ አለኝ፦ “ይሖዋ ለዘሩባቤል የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ ‘“በመንፈሴ እንጂ፣+ በወታደራዊ ኃይል ወይም በጉልበት አይደለም”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።  ታላቅ ተራራ ሆይ፣ አንተ ማን ነህ? በዘሩባቤል+ ፊት ደልዳላ መሬት* ትሆናለህ።+ “እንዴት ያምራል! እንዴት ያምራል!” እያሉ በሚጮኹበት ጊዜ እሱ የመደምደሚያውን ድንጋይ* ያወጣል።’”  የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦  “የዘሩባቤል እጆች የዚህን ቤት መሠረት ጥለዋል፤+ የገዛ እጆቹም ያጠናቅቁታል።+ እኔንም ወደ እናንተ የላከኝ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንደሆነ ታውቃላችሁ። 10  ሥራው በትንሹ የተጀመረበትን ቀን* የናቀ ማን ነው?+ እነሱ ሐሴት ያደርጋሉና፤ በዘሩባቤልም እጅ ላይ ቱምቢውን* ያያሉ። እነዚህ ሰባቱ በመላው ምድር የሚዘዋወሩ የይሖዋ ዓይኖች ናቸው።”+ 11  ከዚያም “ከመቅረዙ በስተ ቀኝና በስተ ግራ ያሉት የእነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ትርጉም ምንድን ነው?” በማለት ጠየቅኩት።+ 12  ለሁለተኛም ጊዜ እንዲህ ስል ጠየቅኩት፦ “በሁለቱ የወርቅ ቱቦዎች አማካኝነት ወርቃማ ፈሳሽ የሚያፈሱት የሁለቱ የወይራ ዛፎች ቅርንጫፎች* ትርጉም ምንድን ነው?” 13  እሱም “የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምን እንደሆነ አታውቅም?” አለኝ። እኔም “ጌታዬ ሆይ፣ አላውቅም” ብዬ መለስኩለት። 14  እሱም “እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት ሁለቱ ቅቡዓን ናቸው” አለ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ከላይ የሚቀመጠውን ድንጋይ።”
ወይም “ሜዳ።”
ወይም “የጥቂቱን ነገር ቀን።”
ቃል በቃል “ድንጋዩን፣ ቆርቆሮውን።”
ብዙ ፍሬ የያዙትን የዛፉን ቅርንጫፎች ያመለክታል።