ዘካርያስ 5:1-11

  • ራእይ 6፦ የሚበር ጥቅልል (1-4)

  • ራእይ 7፦ የኢፍ መስፈሪያ (5-11)

    • ክፋትን የምታመለክት ሴት (8)

    • መስፈሪያዋ ወደ ሰናኦር ምድር ተወሰደች (9-11)

5  ዳግመኛ ቀና ብዬ ስመለከት የሚበር ጥቅልል አየሁ።  እሱም “የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም “ርዝመቱ 20 ክንድ፣* ወርዱ ደግሞ 10 ክንድ የሆነ የሚበር ጥቅልል አያለሁ” ስል መለስኩለት።  ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ በመላው ምድር ላይ የሚወጣው እርግማን ነው፤ ምክንያቱም የሚሰርቁ ሁሉ+ በአንደኛው በኩል በተጻፈው መሠረት አልተቀጡም፤ ደግሞም በሐሰት የሚምሉ ሁሉ+ በሌላኛው በኩል በተጻፈው መሠረት አልተቀጡም።  ‘እኔ ልኬዋለሁ’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ ‘ወደ ሌባውም ቤት ይገባል፤ በስሜ በሐሰት ወደሚምለውም ሰው ቤት ይገባል፤ በዚያም ቤት ውስጥ ይቀመጣል፤ እንጨቱንና ድንጋዩን ጨምሮ ቤቱን ይበላዋል።’”  ከዚያም ሲያነጋግረኝ የነበረው መልአክ ወደ እኔ ቀርቦ “እባክህ ቀና ብለህ የምትወጣውን ነገር ተመልከት” አለኝ።  እኔም “ምንድን ነች?” አልኩ። እሱም መልሶ “ይህች የምትወጣው የኢፍ መስፈሪያ* ናት” አለ። አክሎም “በምድሪቱ ሁሉ የሰዎቹ መልክ ይህ ነው” አለ።  እኔም ከእርሳስ የተሠራው ክቡ መክደኛ ሲነሳ አየሁ፤ በመስፈሪያዋም ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር።  እሱም “ይህች ሴት ክፋትን ታመለክታለች” አለኝ። ከዚያም የኢፍ መስፈሪያዋ ውስጥ መልሶ ጣላት፤ ቀጥሎም ከእርሳስ የተሠራውን ከባዱን መክደኛ መስፈሪያዋ አፍ ላይ ገጠመው።  ከዚያም ቀና ብዬ ስመለከት ሁለት ሴቶች ወደ ፊት ሲመጡ አየሁ፤ በነፋስም መካከል ወደ ላይ ተወነጨፉ። ክንፎቻቸው የራዛ* ዓይነት ክንፎች ነበሩ። እነሱም መስፈሪያዋን በምድርና በሰማይ መካከል አነሷት። 10  እኔም ያነጋግረኝ የነበረውን መልአክ “የኢፍ መስፈሪያዋን ወዴት እየወሰዷት ነው?” ስል ጠየቅኩት። 11  እሱም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ቤት ሊሠሩላት ወደ ሰናኦር*+ ምድር እየወሰዷት ነው፤ ቤቱም በተዘጋጀ ጊዜ በዚያ በተገቢው ቦታዋ ላይ ያስቀምጧታል።”

የግርጌ ማስታወሻ

አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ኢፍ።” ይህም አንድ ኢፍ ለመለካት የሚያገለግልን መስፈሪያ ወይም ቅርጫት ያመለክታል። አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ባለ ረጃጅም እግር ትልቅ አሞራ።
ባቢሎንን ያመለክታል።