ዘካርያስ 6:1-15

  • ራእይ 8፦ አራት ሠረገሎች (1-8)

  • ቀንበጡ ንጉሥና ካህን ይሆናል (9-15)

6  ዳግመኛም ቀና ብዬ ስመለከት አራት ሠረገሎች ከሁለት ተራሮች መካከል ሲመጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የመዳብ ተራሮች ነበሩ።  የመጀመሪያውን ሠረገላ የሚጎትቱት ቀይ ፈረሶች፣ ሁለተኛውን ሠረገላ የሚጎትቱት ደግሞ ጥቁር ፈረሶች ነበሩ።+  ሦስተኛውን ሠረገላ የሚጎትቱት ነጭ ፈረሶች፣ አራተኛውን ሠረገላ የሚጎትቱት ደግሞ ነጠብጣብ ያለባቸውና ዥጉርጉር ፈረሶች ነበሩ።+  ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ “ጌታዬ ሆይ፣ እነዚህ ምንድን ናቸው?” ብዬ ጠየቅኩት።  መልአኩ እንዲህ ሲል መለሰልኝ፦ “እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙ በኋላ፣+ ከዚያ የሚወጡት አራቱ የሰማያት መናፍስት ናቸው።+  በጥቁር ፈረሶች የሚጎተተው ሠረገላ ወደ ሰሜን ምድር ይወጣል፤+ ነጮቹ ፈረሶች ከባሕሩ ባሻገር ወዳለው ምድር ይወጣሉ፤ ነጠብጣብ ያለባቸው ፈረሶች ደግሞ ወደ ደቡብ ምድር ይወጣሉ።  ዥጉርጉሮቹ ፈረሶችም ወጥተው በምድር መካከል ለመመላለስ አቆብቁበው* ነበር።” እሱም “ሂዱ፤ በምድር መካከል ተመላለሱ” አለ። እነሱም በምድር መካከል ይመላለሱ ጀመር።  ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለኝ፦ “እነሆ፣ ወደ ሰሜን ምድር የሚወጡት፣ የይሖዋ መንፈስ በሰሜን ምድር እንዲያርፍ አድርገዋል።”  የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦ 10  “በግዞት ከተወሰደው ሕዝብ ያመጡትን ነገር ከሄልዳይ፣ ከጦቢያህና ከየዳያህ ውሰድ፤ በዚያም ቀን፣ ከባቢሎን ከመጡት ከእነዚህ ሰዎች ጋር ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ሂድ። 11  ብርና ወርቅ ወስደህ አክሊል* ሥራ፤ ከዚያም በየሆጼዴቅ ልጅ በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ+ ራስ ላይ አድርገው። 12  እንዲህም በለው፦ “‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ቀንበጥ ተብሎ የሚጠራው ሰው ይህ ነው።+ እሱ በገዛ ቦታው ላይ ያቆጠቁጣል፤ የይሖዋንም ቤተ መቅደስ ይሠራል።+ 13  የይሖዋን ቤተ መቅደስ የሚገነባው እሱ ነው፤ ግርማ የሚጎናጸፈውም እሱ ነው። በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ይገዛል፤ ደግሞም በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ካህን ሆኖ ያገለግላል፤+ በሁለቱም መካከል* ሰላማዊ ስምምነት ይኖራል። 14  አክሊሉም* ለሄሌም፣ ለጦቢያህ፣ ለየዳያህና+ ለሶፎንያስ ልጅ ለሄን በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ መታሰቢያ* ሆኖ ያገለግላል። 15  በሩቅ ያሉትም ይመጣሉ፤ በይሖዋ ቤተ መቅደስ የግንባታ ሥራም ይካፈላሉ።” እኔን ወደ እናንተ የላከኝ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንደሆነ ታውቃላችሁ። የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ብትሰሙ ይህ ይሆናል።’”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ተዘጋጅተው፤ ቸኩለው።”
ወይም “ታላቅ አክሊል።”
ገዢና ካህን ሆኖ በሚጫወተው ሚና መካከል ማለት ነው።
ወይም “ታላቁ አክሊልም።”
ወይም “ማስታወሻ።”