ዘካርያስ 7:1-14

  • ይሖዋ ልባዊ ያልሆነን ጾም ያወግዛል (1-14)

    • “ትጾሙ የነበረው በእርግጥ ለእኔ ነበር?” (5)

    • ‘አንዳችሁ ለሌላው ፍትሕ፣ ታማኝ ፍቅርና ምሕረት አሳዩ’ (9)

7  ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ኪስሌው* በተባለው በዘጠነኛው ወር፣ ከወሩም በአራተኛው ቀን የይሖዋ ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ።+  የቤቴል ሰዎች ይሖዋ ሞገስ እንዲያሳያቸው ለመለመን ሳሬጸርንና ረጌምሜሌክን ከሰዎቹ ጋር ላኩ፤  እነሱም የሠራዊት ጌታን የይሖዋን ቤት* ካህናትና ነቢያቱን “ለብዙ ዓመታት እንዳደረግኩት በአምስተኛው ወር ማልቀስና+ መጾም ይኖርብኛል?” ብለው ጠየቁ።  የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦  “ለምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉና ለካህናቱ እንዲህ በላቸው፦ ‘ለ70 ዓመታት+ በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር ስትጾሙና ዋይ ዋይ ስትሉ፣+ ትጾሙ የነበረው በእርግጥ ለእኔ ነበር?  ትበሉና ትጠጡ በነበረበት ጊዜስ ትበሉና ትጠጡ የነበረው ለራሳችሁ አልነበረም?  ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉት ከተሞቿ በሰዎች ተሞልተውና ሰላም ሰፍኖባቸው በነበረበት ጊዜ እንዲሁም ሰዎች በኔጌብና በሸፌላ ይኖሩ በነበረበት ወቅት ይሖዋ በቀድሞዎቹ ነቢያት አማካኝነት ያወጀውን ቃል መታዘዝ አልነበረባችሁም?’”+  የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ ዘካርያስ መጣ፦  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በእውነተኛ ፍትሕ ላይ ተመሥርታችሁ ፍረዱ፤+ አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅርና+ ምሕረት አሳዩ። 10  መበለቲቱንም ሆነ አባት የሌለውን ልጅ፣*+ ከባዕድ አገር የመጣውን ሰውም+ ሆነ ድሃውን አታታሉ፤+ ደግሞም አንዳችሁ በሌላው ላይ ክፉ ለማድረግ በልባችሁ አታሲሩ።’+ 11  እነሱ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም፤+ በግትርነትም ጀርባቸውን ሰጡ፤+ ላለመስማትም ሲሉ ጆሯቸውን ደፈኑ።+ 12  ልባቸውን እንደ አልማዝ* አጠነከሩ፤+ እንዲሁም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት፣ በቀድሞዎቹ ነቢያት በኩል የላከውን ሕግና* ቃል አልታዘዙም።+ ከዚህም የተነሳ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እጅግ ተቆጣ።”+ 13  “‘እኔ ስጠራቸው እንዳልሰሙኝ ሁሉ+ እነሱ ሲጣሩም አልሰማቸውም’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 14  ‘ደግሞም ወደማያውቋቸው ብሔራት ሁሉ በአውሎ ነፋስ በተንኳቸው፤+ ምድሪቱም ትተዋት ከሄዱ በኋላ ባድማ ሆነች፤ በእሷ የሚያልፍ ወይም ወደ እሷ የሚመለስ ማንም የለም፤+ የተወደደችውን ምድር አስፈሪ ቦታ አድርገዋታልና።’”

የግርጌ ማስታወሻ

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅ።”
“እንደ ጠንካራ ድንጋይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “መመሪያና፤ ትምህርትና።”