ዘካርያስ 8:1-23

  • ይሖዋ ለጽዮን ሰላምንና እውነትን ይሰጣል (1-23)

    • ኢየሩሳሌም፣ “የእውነት ከተማ” (3)

    • “እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ” (16)

    • ከጾም ወደ ፍስሐ (18, 19)

    • ይሖዋን ከልብ እንፈልግ (21)

    • አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ይይዛሉ (23)

8  የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ መጣ፦  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለጽዮን በታላቅ ቅንዓት እቀናለሁ፤+ ደግሞም በታላቅ ቁጣ ለእሷ እቀናለሁ።’”  “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ ጽዮን እመለሳለሁ፤+ በኢየሩሳሌምም እኖራለሁ፤+ ኢየሩሳሌምም የእውነት* ከተማ ተብላ ትጠራለች፤+ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ተራራም ቅዱስ ተራራ ተብሎ ይጠራል።’”+  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሽማግሌዎችና አሮጊቶች በኢየሩሳሌም አደባባዮች እንደገና ይቀመጣሉ፤ እያንዳንዳቸውም ከዕድሜያቸው ርዝመት የተነሳ* በእጃቸው ምርኩዝ ይይዛሉ።+  የከተማዋም አደባባዮች በዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።’”+  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚያን ጊዜ ይህ ነገር ለዚህ ሕዝብ ቀሪዎች የማይቻል ነገር መስሎ ቢታይ እንኳ ለእኔ የማይቻል ነገር ሊመስል ይገባል?’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ ሕዝቤን ከምሥራቅና ከምዕራብ አገሮች* አድናለሁ።+  እኔም አመጣቸዋለሁ፤ እነሱም በኢየሩሳሌም ይኖራሉ፤+ ሕዝቤም ይሆናሉ፤ እኔም በእውነትና* በጽድቅ አምላካቸው እሆናለሁ።’”+  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በእነዚህ ቀናት በነቢያት አፍ የተነገሩትን+ እነዚህን ቃላት የምትሰሙ ሁሉ እጃችሁን አበርቱ፤*+ እነዚህ ቃላት፣ ቤተ መቅደሱን ለመገንባት፣ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቤት መሠረት በተጣለበት ጊዜ ነቢያት የተናገሯቸው ናቸው። 10  ከእነዚያ ቀናት በፊት ለሰውም ሆነ ለእንስሳ የሚከፈል ደሞዝ አልነበረምና፤+ ደግሞም ከጠላት የተነሳ በሰላም መግባትና መውጣት አይቻልም ነበር፤ ሰው ሁሉ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ አድርጌ ነበርና።’ 11  “‘አሁን ግን በዚህ ሕዝብ ቀሪዎች ላይ እንደቀድሞው ዘመን አላደርግም’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 12  ‘የሰላም ዘር ይዘራልና፤ የወይን ተክሉ ፍሬ ያፈራል፤ ምድርም ፍሬዋን ትሰጣለች፤+ ሰማያትም ጠል ያዘንባሉ፤ እኔም የዚህ ሕዝብ ቀሪዎች እነዚህን ነገሮች ሁሉ እንዲወርሱ አደርጋለሁ።+ 13  የይሁዳና የእስራኤል ቤት ሆይ፣ በብሔራት መካከል እርግማን ነበራችሁ፤+ አሁን ግን አድናችኋለሁ፤ እናንተም በረከት ትሆናላችሁ።+ አትፍሩ!+ እጃችሁን አበርቱ።’*+ 14  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘“አባቶቻችሁ ስላስቆጡኝ በእናንተ ላይ ጥፋት ላመጣባችሁ ቆርጬ እንደነበርና በዚያም እንዳልተጸጸትኩ ሁሉ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣+ 15  “አሁንም ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት መልካም ለማድረግ ቆርጫለሁ።+ አትፍሩ!”’+ 16  “‘እናንተ እነዚህን ነገሮች ልታደርጉ ይገባል፦ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤+ በከተማዋም በሮች የምትፈርዱት ፍርድ እውነትን የሚያጠናክርና ሰላምን የሚያሰፍን ይሁን።+ 17  አንዳችሁ በሌላው ላይ ክፉ ነገር ለማድረግ በልባችሁ አታሲሩ፤+ ማንኛውንም የሐሰት መሐላ አትውደዱ፤+ እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጠላለሁና’+ ይላል ይሖዋ።” 18  የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦ 19  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የአራተኛው ወር፣+ የአምስተኛው ወር፣+ የሰባተኛው ወርና+ የአሥረኛው ወር+ ጾም ለይሁዳ ቤት የፍስሐና የደስታ ይኸውም የሐሴት በዓል ይሆናል።+ በመሆኑም እውነትንና ሰላምን ውደዱ።’ 20  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሕዝቦችና የብዙ ከተማ ነዋሪዎች በእርግጥ ይመጣሉ፤ 21  በአንዲት ከተማ የሚኖሩ ሰዎችም በሌላ ከተማ ወደሚኖሩ ሰዎች ሄደው እንዲህ ይላሉ፦ “ይሖዋ ሞገሱን እንዲያሳየን ለመለመንና የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ለመፈለግ ተነሱ፤ እንሂድ። እኔም እሄዳለሁ።”+ 22  ደግሞም ብዙ ሕዝቦችና ኃያላን ብሔራት የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ለመፈለግና ይሖዋ ሞገሱን እንዲያሳያቸው ለመለመን ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ።’+ 23  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚያን ጊዜ ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ+ አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ* አጥብቀው በመያዝ “አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን”+ ይላሉ።’”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የታማኝነት።”
ቃል በቃል “ከቀናት ብዛት የተነሳ።”
ወይም “ፀሐይ ከምትወጣበት አገርና ፀሐይ ከምትጠልቅበት አገር።”
ወይም “በታማኝነትና።”
ወይም “አይዟችሁ።”
ወይም “አይዟችሁ።”
ወይም “የልብስ ዘርፍ።”