ዘዳግም 10:1-22

  • ሙሴ በድጋሚ ሁለት ጽላቶችን አዘጋጀ (1-11)

  • ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? (12-22)

    • ይሖዋን መፍራትና መውደድ (12)

10  “በዚያን ጊዜ ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ጠርበህ+ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፤ የእንጨት ታቦትም* ለራስህ ሥራ።  እኔም በጽላቶቹ ላይ አንተ በሰበርካቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት እጽፋለሁ፤ አንተም ጽላቶቹን በታቦቱ ውስጥ አስቀምጣቸው።’  ስለዚህ ከግራር እንጨት ታቦት ሠራሁ፤ ከዚያም እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ የድንጋይ ጽላቶችን ከቀረጽኩ በኋላ ሁለቱን ጽላቶች ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ።+  እሱም በጽላቶቹ ላይ ቀደም ሲል ጽፏቸው የነበሩትን ቃላት+ ይኸውም ተሰብስባችሁ በነበረበት ቀን+ ይሖዋ በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ+ ለእናንተ ነግሯችሁ የነበሩትን አሥርቱን ትእዛዛት*+ ጻፈባቸው፤ ይሖዋም ጽላቶቹን ለእኔ ሰጠኝ።  እኔም ተመልሼ ከተራራው ወረድኩ፤+ ይሖዋም ባዘዘኝ መሠረት ጽላቶቹን፣ በሠራሁት ታቦት ውስጥ አስቀመጥኳቸው። እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ይገኛሉ።  “ከዚያም እስራኤላውያን ከበኤሮት ብኔያዕቃን ተነስተው ወደ ሞሴራ ሄዱ። አሮንም በዚያ ቦታ ሞቶ ተቀበረ፤+ ልጁ አልዓዛርም በእሱ ምትክ ካህን ሆኖ ማገልገል ጀመረ።+  ከዚያም ተነስተው ወደ ጉድጎዳ ተጓዙ፤ ከጉድጎዳም ተነስተው ጅረቶች* ወደሚፈስሱባት ምድር ወደ ዮጥባታ+ ሄዱ።  “በዚያን ጊዜ ይሖዋ፣ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት እንዲሸከም፣+ ይሖዋን ለማገልገል በፊቱ እንዲቆምና እስከ ዛሬ እንደሚያደርገው በስሙ እንዲባርክ+ የሌዊን ነገድ ለየ።+  ሌዊ ከወንድሞቹ ጋር ድርሻ ወይም ርስት ያልተሰጠው ለዚህ ነው። አምላክህ ይሖዋ በነገረው መሠረት ይሖዋ ርስቱ ነው።+ 10  እኔም እንደ መጀመሪያው ጊዜ ሁሉ በተራራው ላይ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ቆየሁ፤+ በዚህ ጊዜም ደግሞ ይሖዋ ሰማኝ።+ ይሖዋ ሊያጠፋህ አልፈለገም። 11  ከዚያም ይሖዋ ‘ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማልኩላቸውን ምድር ገብተው እንዲወርሱ ተነስና ከሕዝቡ ፊት ፊት ሂድ’ አለኝ።+ 12  “እንግዲህ እስራኤል ሆይ፣ አምላክህ ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?+ አምላክህን ይሖዋን እንድትፈራው፣+ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣+ እንድትወደው፣ አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህና በሙሉ ነፍስህ* እንድታገለግለው+ 13  እንዲሁም ለገዛ ጥቅምህ ስትል እኔ ዛሬ የማዝህን የይሖዋን ትእዛዛትና ደንቦች እንድትጠብቅ ብቻ ነው።+ 14  እነሆ ሰማያት፣ ሌላው ቀርቶ ሰማየ ሰማያት* እንዲሁም ምድርና በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ የአምላክህ የይሖዋ ናቸው።+ 15  ይሁንና ይሖዋ የቀረበውና ፍቅሩን የገለጸው ለአባቶችህ ብቻ ነው፤ ስለሆነም ይኸው ዛሬ እንደሆነው የእነሱ ዘር የሆናችሁትን እናንተን ከሕዝቦች ሁሉ መካከል መረጠ።+ 16  ስለዚህ ልባችሁን አንጹ፤*+ ከእንግዲህም ወዲህ ግትር መሆናችሁን ተዉ።*+ 17  ምክንያቱም አምላካችሁ ይሖዋ የአማልክት አምላክና+ የጌቶች ጌታ እንዲሁም ታላቅ፣ ኃያል፣ የሚያስፈራ፣ ለማንም የማያዳላና+ ጉቦ የማይቀበል አምላክ ነው። 18  አባት ለሌለው* ልጅና ለመበለት ይፈርዳል፤+ እንዲሁም የባዕድ አገሩን ሰው ይወደዋል፤+ ምግብና ልብስም ይሰጠዋል። 19  እናንተም የባዕድ አገሩን ሰው ውደዱ፤ ምክንያቱም በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ነበራችሁ።+ 20  “አምላክህን ይሖዋን ፍራ፤ አገልግለው፤+ ከእሱም ጋር ተጣበቅ፤ በስሙም ማል። 21  ልታወድሰው የሚገባህ እሱን ነው።+ እሱ በዓይኖችህ ያየሃቸውን እነዚያን ታላላቅና አስፈሪ ነገሮች ሁሉ ያደረገልህ አምላክህ ነው።+ 22  አባቶችህ ወደ ግብፅ ሲወርዱ 70* ነበሩ፤+ አሁን ግን አምላክህ ይሖዋ በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት ቁጥርህን አብዝቶታል።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ሣጥንም።”
ቃል በቃል “አሥርቱን ቃላት።”
ወይም “ደረቅ ወንዞች።”
ወይም “እጅግ ከፍ ያሉት ሰማያት።”
ቃል በቃል “የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ።”
ቃል በቃል “አንገታችሁን አታደንድኑ።”
ወይም “ወላጅ አልባ ለሆነው።”
ወይም “70 ነፍስ።”