ዘዳግም 15:1-23

  • በየሰባት ዓመቱ ዕዳ ይሰረዛል (1-6)

  • ድሆችን መርዳት (7-11)

  • በየሰባት ዓመቱ ባሮች ነፃ ይወጣሉ (12-18)

    • የባሪያን ጆሮ በወስፌ መብሳት (16, 17)

  • የእንስሳትን በኩር መቀደስ (19-23)

15  “በየሰባት ዓመቱ መጨረሻ የሌሎችን ዕዳ መሰረዝ ይኖርብሃል።+  ዕዳ የሚሰረዘው በሚከተለው መንገድ ነው፦ እያንዳንዱ አበዳሪ ባልንጀራው ያለበትን ዕዳ ይሰርዝለታል። ከባልንጀራው ወይም ከወንድሙ ክፍያ መጠየቅ የለበትም፤ ምክንያቱም ለይሖዋ ሲባል ዕዳ እንዲሰረዝ ይታወጃል።+  ከባዕድ አገር ሰው ክፍያ መጠየቅ ትችላለህ፤+ ወንድምህ ለአንተ መመለስ ያለበትን ማንኛውንም ነገር ግን ተውለት።  ይሁንና አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርገህ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ላይ ይሖዋ ስለሚባርክህ+ ከእናንተ መካከል ማንም ድሃ አይሆንም፤  ይህ የሚሆነው ግን የአምላክህን የይሖዋን ቃል በትኩረት የምትሰማና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዛት በሙሉ በጥንቃቄ የምትፈጽም ከሆነ ነው።+  አምላክህ ይሖዋ በገባልህ ቃል መሠረት ይባርክሃልና፤ አንተም ለብዙ ብሔራት ታበድራለህ* እንጂ አትበደርም፤+ ብዙ ብሔራትን ትገዛለህ እንጂ አንተን አይገዙህም።+  “ከወንድሞችህ መካከል አንዱ አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ከሚገኙት ከተሞች በአንዱ ውስጥ ድሃ ቢሆን በድሃው ወንድምህ ላይ ልብህ አይጨክንበት ወይም እጅህን አትጠፍበት።+  ከዚህ ይልቅ በልግስና እጅህን ዘርጋለት፤+ በተቻለ መጠን፣ የሚያስፈልገውን ወይም የጎደለውን ማንኛውንም ነገር አበድረው።*  ‘ዕዳ የሚሰረዝበት ሰባተኛው ዓመት ቀርቧል’ የሚል ክፉ ሐሳብ በልብህ አድሮ ለድሃው ወንድምህ ከመለገስ ወደኋላ እንዳትልና ምንም ሳትሰጠው እንዳትቀር ተጠንቀቅ።+ እሱ በአንተ ላይ ቅር ተሰኝቶ ወደ ይሖዋ ቢጮኽ ኃጢአት ይሆንብሃል።+ 10  በልግስና ስጠው፤+ ስትሰጠው ልብህ ቅር እያለው መሆን የለበትም፤ ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ በሥራህ ሁሉና በምታከናውነው በማንኛውም ነገር የሚባርክህ በዚህ የተነሳ ነው።+ 11  መቼም ቢሆን ከምድሪቱ ላይ ድሆች አይጠፉምና።+ ‘በምድርህ ላይ ለሚኖር ጎስቋላና ድሃ ወንድምህ በልግስና እጅህን ዘርጋለት’ በማለት ያዘዝኩህ ለዚህ ነው።+ 12  “ከወንድሞችህ አንዱ ይኸውም አንድ ዕብራዊ ወይም አንዲት ዕብራዊ፣ ለአንተ ቢሸጥና ስድስት ዓመት ቢያገለግልህ በሰባተኛው ዓመት ነፃ አውጣው።+ 13  ነፃ የምታወጣው ከሆነ ባዶ እጁን አትስደደው። 14  ከመንጋህና ከአውድማህ እንዲሁም ከዘይትና ከወይን መጭመቂያህ በልግስና ስጠው። አምላክህ ይሖዋ በባረከህ መጠን ስጠው። 15  አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደነበርክና አምላክህ ይሖዋ እንደተቤዠህ አስታውስ። እኔ ዛሬ ይህን እንድታደርግ የማዝህ ለዚህ ነው። 16  “ሆኖም ይህ ሰው ከአንተ ጋር በነበረበት ጊዜ ደስተኛ ስለነበር አንተንና ቤተሰብህን በመውደድ ‘ፈጽሞ ከአንተ አልለይም!’ ቢልህ+ 17  ጆሮውን በር ላይ አስደግፈህ በወስፌ ብሳው፤ እሱም ዕድሜ ልኩን የአንተ ባሪያ ይሆናል። ሴት ባሪያህንም በተመለከተ እንደዚሁ አድርግ። 18  ባሪያህን ነፃ አድርጎ ማሰናበት ሊከብድህ አይገባም፤ ምክንያቱም እሱ በስድስት ዓመት ውስጥ የሰጠህ አገልግሎት በቅጥር ሠራተኛ ደሞዝ ቢሰላ እጥፍ ዋጋ ያስወጣህ ነበር፤ ደግሞም አምላክህ ይሖዋ በምትሠራው ነገር ሁሉ ባርኮሃል። 19  “ከከብትህና ከመንጋህ መካከል በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ ለአምላክህ ለይሖዋ ቀድሰው።+ በከብትህ* በኩር ምንም ሥራ አትሥራበት፤ የመንጋህንም በኩር አትሸልት። 20  አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ይሖዋ በሚመርጠው ስፍራ በየዓመቱ በአምላክህ በይሖዋ ፊት ብሉት።+ 21  ይሁንና እንስሳው እንከን ካለበት ይኸውም አንካሳ ወይም ዕውር ከሆነ አሊያም ሌላ ዓይነት ከባድ ጉድለት ካለበት ለአምላክህ ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገህ አታቅርበው።+ 22  በከተሞችህ* ውስጥ ብላው፤ እንደ ሜዳ ፍየል ወይም እንደ ርኤም* ሁሉ ንጹሕ ያልሆነውም ሆነ ንጹሕ የሆነው ሰው ሊበላው ይችላል።+ 23  ሆኖም ደሙን አትብላ፤+ እንደ ውኃ መሬት ላይ አፍስሰው።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በመያዣ ታበድራለህ።”
ወይም “በመያዣ አበድረው።”
ቃል በቃል “በበሬህ።”
ቃል በቃል “በደጆችህ።”
ቅርንጫፍ የሚመስሉ ቀንዶች ያሉት አጥቢ እንስሳ፤ ከአጋዘን ጋር ይመሳሰላል።