ዘዳግም 16:1-22

  • ፋሲካ፤ እርሾ ያልገባበት ቂጣ በዓል (1-8)

  • የሳምንታት በዓል (9-12)

  • የዳስ በዓል (13-17)

  • ዳኞች ተሾሙ (18-20)

  • የማምለኪያ ግንድና ዓምድ አታቁም (21, 22)

16  “አምላክህ ይሖዋ ከግብፅ በሌሊት ያወጣህ በአቢብ* ወር ስለሆነ የአቢብን ወር አስብ፤+ እንዲሁም ለአምላክህ ለይሖዋ ፋሲካን* አክብር።+  ይሖዋ ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በመረጠው ስፍራ+ ከመንጋህና ከከብትህ+ ለአምላክህ ለይሖዋ የፋሲካን መባ ሠዋ።+  ከእሱም ጋር እርሾ የገባበት ምንም ነገር አትብላ፤+ ከግብፅ ምድር የወጣኸው በጥድፊያ ስለነበር+ ለሰባት ቀን ቂጣ* ይኸውም የመከራ ቂጣ ብላ። ይህን የምታደርገው ከግብፅ ምድር የወጣህበትን ዕለት በሕይወት ዘመንህ ሁሉ እንድታስታውስ ነው።+  ለሰባት ቀን በግዛትህ ሁሉ እርሾ አይገኝ፤+ በመጀመሪያው ቀን ምሽት ላይ ከምታቀርበው መሥዋዕት ላይም ቢሆን ምንም ሥጋ ማደር የለበትም።+  የፋሲካውን መባ አምላክህ ይሖዋ ከሚሰጥህ ከተሞች አንተ በፈለግከው በአንዱ ውስጥ መሠዋት አይገባህም።  ከዚህ ይልቅ አምላክህ ይሖዋ ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ መቅረብ ይኖርበታል። የፋሲካውን መባ ምሽት ላይ ፀሐይ እንደጠለቀች፣+ ከግብፅ በወጣህበት በዚያው ጊዜ ሠዋው።  አምላክህ ይሖዋ በሚመርጠው ቦታ+ አብስለህ ብላው፤+ ሲነጋም ተመልሰህ ወደ ድንኳንህ መሄድ ትችላለህ።  ለስድስት ቀን ቂጣ ብላ፤ በሰባተኛውም ቀን ለአምላክህ ለይሖዋ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆናል። ምንም ሥራ አትሥራ።+  “ሰባት ሳምንት ቁጠር። ሰባቱን ሳምንት መቁጠር መጀመር ያለብህ በማሳህ ላይ ያለውን እህል ለማጨድ ማጭድህን ካነሳህበት ጊዜ አንስቶ ነው።+ 10  ከዚያም አምላክህ ይሖዋ በባረከህ መጠን+ በምታቀርበው የፈቃደኝነት መባ አማካኝነት ለአምላክህ ለይሖዋ የሳምንታት በዓልን ታከብራለህ።+ 11  በአምላክህ በይሖዋ ፊት ደስ ይበልህ፤ አንተም ሆንክ ወንድ ልጅህ፣ ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህ፣ ሴት ባሪያህ እንዲሁም በከተሞችህ ውስጥ* የሚኖር ሌዋዊ፣ በመካከልህ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው፣ አባት የሌለው* ልጅና መበለቲቱ አምላክህ ይሖዋ ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በመረጠው ስፍራ ደስ ይበላችሁ።+ 12  አንተም በግብፅ ባሪያ እንደነበርክ አስታውስ፤+ እነዚህንም ሥርዓቶች ጠብቅ እንዲሁም ፈጽም። 13  “እህልህን ከአውድማህ፣ ዘይትህንና የወይን ጠጅህን ከመጭመቂያህ በምታስገባበት ጊዜ የዳስ* በዓልን+ ለሰባት ቀን አክብር። 14  በዓልህን በምታከብርበት ወቅት ደስ ይበልህ፤+ አንተም ሆንክ ወንድ ልጅህ፣ ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህ፣ ሴት ባሪያህ እንዲሁም በከተሞችህ ውስጥ የሚኖር ሌዋዊ፣ የባዕድ አገር ሰው፣ አባት የሌለው ልጅና መበለቲቱ ደስ ይበላችሁ። 15  አምላክህ ይሖዋ ምርትህንና የእጅህን ሥራ ሁሉ ስለሚባርክልህ+ ይሖዋ በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለይሖዋ ሰባት ቀን በዓሉን ታከብራለህ፤+ አንተም እጅግ ትደሰታለህ።+ 16  “በመካከልህ ያሉ ወንዶች ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ ይኸውም በቂጣ በዓል+ ቀን፣ በሳምንታት በዓል+ ቀን እንዲሁም በዳስ* በዓል+ ቀን አምላክህ ይሖዋ በመረጠው ስፍራ ፊቱ ይቅረቡ፤ ማናቸውም ባዶ እጃቸውን ይሖዋ ፊት አይቅረቡ። 17  እያንዳንዱ ሰው የሚያመጣው ስጦታ አምላክህ ይሖዋ በባረከህ መጠን መሆን አለበት።+ 18  “አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ከተሞች ሁሉ ለእያንዳንዱ ነገድ ዳኞችንና አለቆችን ሹም፤+ እነሱም ለሕዝቡ የጽድቅ ፍርድ ይፍረዱ። 19  ፍርድን አታዛባ፤+ አድልዎ አትፈጽም+ ወይም ጉቦ አትቀበል፤ ምክንያቱም ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራል፤+ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማል። 20  በሕይወት እንድትኖርና አምላክህ ይሖዋ የሚሰጥህን ምድር እንድትወርስ ፍትሕን፣ አዎ ፍትሕን ተከታተል።+ 21  “ለአምላክህ ለይሖዋ በምትሠራው መሠዊያ አጠገብ የማምለኪያ ግንድ*+ እንዲሆን ማንኛውንም ዓይነት ዛፍ አትትከል። 22  “አምላክህ ይሖዋ አጥብቆ የሚጠላውን የማምለኪያ ዓምድ ለራስህ አታቁም።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የማለፍን በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ወላጅ አልባ የሆነው።”
ቃል በቃል “በደጆችህ ውስጥ።”
ወይም “የጊዜያዊ መጠለያ።”
ወይም “በጊዜያዊ መጠለያ።”