ዘዳግም 17:1-20

  • የሚቀርበው መሥዋዕት እንከን የለሽ መሆን አለበት (1)

  • ከሃዲዎችን በተመለከተ መደረግ ያለበት ነገር (2-7)

  • ለመዳኘት አስቸጋሪ የሆኑ የፍርድ ጉዳዮች (8-13)

  • ወደፊት ንጉሥ ቢያነግሡ መደረግ ያለበት ነገር (14-20)

    • ንጉሡ የሕጉን ቅጂ ለራሱ መገልበጥ ይኖርበታል (18)

17  “እንከን ወይም ማንኛውም ዓይነት ጉድለት ያለበትን በሬ ወይም በግ ለአምላክህ ለይሖዋ አትሠዋ፤ ምክንያቱም ይህ ለአምላክህ ለይሖዋ አስጸያፊ ነው።+  “አምላክህ ይሖዋ ከሚሰጥህ ከተሞች በአንዱ ውስጥ በአምላክህ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር የሚፈጽምና ቃል ኪዳኑን የሚያፈርስ ወንድ ወይም ሴት ቢገኝ+  እሱም ሄዶ ሌሎች አማልክትን በማምለክ እንዲሁም ለእነሱ ወይም ለፀሐይ አሊያም ለጨረቃ ወይም ደግሞ ለሰማይ ሠራዊት በሙሉ በመስገድ+ እኔ ያላዘዝኩትን ነገር ቢያደርግ+  አንተም ይህ ነገር ቢነገርህ ወይም ሁኔታውን ብትሰማ ጉዳዩን በጥንቃቄ አጣራ። ይህ አስጸያፊ ነገር በእስራኤል ውስጥ መፈጸሙ እውነት እንደሆነ ቢረጋገጥ+  እንዲህ ያለ መጥፎ ድርጊት የፈጸመውን ያንን ሰው ወይም ያቺን ሴት ወደ ከተማዋ በር አውጣቸው፤ ከዚያም ሰውየው ወይም ሴትየዋ እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ይወገሩ።+  ሞት የሚገባው ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በሚሰጡት ምሥክርነት*+ ይገደል። አንድ ምሥክር በሚሰጠው ቃል ብቻ መገደል የለበትም።+  እሱን ለመግደል መጀመሪያ እጃቸውን የሚያነሱት ምሥክሮቹ መሆን ይኖርባቸዋል፤ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እጁን ያንሳበት። ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ።+  “ከከተሞችህ በአንዱ ውስጥ ለመዳኘት አስቸጋሪ የሆነ ክርክር ቢነሳ ለምሳሌ፣ ጉዳዩ ደም ማፍሰስን+ የሚመለከትም ይሁን ለሕግ አቤቱታ ማቅረብን ወይም የዓመፅ ድርጊትን አሊያም ሌሎች አለመግባባቶችን የሚመለከት ቢሆን ተነስተህ አምላክህ ይሖዋ ወደሚመርጠው ስፍራ ውጣ።+  ወደ ሌዋውያን ካህናትና በዚያን ጊዜ ዳኛ ሆኖ ወደሚያገለግለው ሰው+ ሄደህ ጠይቅ፤ እነሱም ውሳኔውን ይነግሩሃል።+ 10  አንተም እነዚህ ሰዎች ይሖዋ በሚመርጠው ስፍራ ሆነው በነገሩህ ውሳኔ መሠረት እርምጃ ውሰድ። የሰጡህንም መመሪያ በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽም። 11  በሚሰጡህ ሕግና በሚነግሩህ ውሳኔ መሠረት እርምጃ ውሰድ።+ እነሱ ካሳለፉት ውሳኔ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አትበል።+ 12  አምላክህን ይሖዋን የሚያገለግለውን ካህን ወይም ዳኛውን ባለመስማት እብሪተኛ የሚሆን ሰው ካለ ይገደል።+ ክፉ የሆነውን ከእስራኤል መካከል አስወግድ።+ 13  ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲሰማ ይፈራል፤ ከእንግዲህም የእብሪት ድርጊት አይፈጽምም።+ 14  “አምላክህ ይሖዋ የሚሰጥህን ምድር ገብተህ ከወረስካት በኋላ በዚያ መኖር ስትጀምር ‘በዙሪያዬ እንዳሉት ብሔራት ሁሉ እኔም በላዬ ላይ ንጉሥ ላንግሥ’ ብትል+ 15  አምላክህ ይሖዋ የሚመርጠውን ንጉሥ ታነግሣለህ። የምታነግሠውም ንጉሥ ከወንድሞችህ መካከል መሆን ይኖርበታል።+ ወንድምህ ያልሆነን ባዕድ ሰው በላይህ ላይ ማንገሥ አይገባህም። 16  ይሁን እንጂ ንጉሡ ለራሱ ፈረሶች ማብዛት+ ወይም የፈረሶቹን ቁጥር ለመጨመር ሲል ሕዝቡ ወደ ግብፅ እንዲመለስ ማድረግ የለበትም፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ‘በዚህ መንገድ ፈጽሞ ዳግመኛ እንዳትመለሱ’ ብሏችኋል። 17  ልቡ ከትክክለኛው መንገድ ዞር እንዳይል ለራሱ ሚስቶች አያብዛ፤+ ለራሱም ብርና ወርቅ አያከማች።+ 18  በመንግሥቱ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበትም ጊዜ በሌዋውያን ካህናት እጅ ካለው ላይ ወስዶ የዚህን ሕግ ቅጂ ለራሱ በመጽሐፍ* ላይ ይጻፍ።+ 19  “አምላኩን ይሖዋን መፍራትን እንዲማር እንዲሁም በዚህ ሕግና በእነዚህ ሥርዓቶች ላይ የሰፈሩትን ቃላት በሙሉ በመፈጸም እንዲጠብቃቸው ይህ መጽሐፍ ከእሱ ጋር ይሁን፤+ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ያንብበው።+ 20  ይህን ካደረገ ልቡ በወንድሞቹ ላይ አይታበይም፤ ከትእዛዛቱም ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አይልም፤ ይህም እሱም ሆነ ልጆቹ በእስራኤል መካከል በመንግሥቱ ላይ ረጅም ዘመን እንዲቆዩ ያስችላቸዋል።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች አፍ።”
ወይም “በጥቅልል።”