ዘዳግም 19:1-21

  • የደም ዕዳና የመማጸኛ ከተሞች (1-13)

  • ወሰን አትግፋ (14)

  • ዳኛ ፊት ቀርቦ መመሥከር (15-21)

    • ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች ያስፈልጋሉ (15)

19  “አምላክህ ይሖዋ ምድራቸውን ለአንተ የሚሰጥህን ብሔራት፣ ይሖዋ በሚያጠፋቸውና አንተም እነሱን አስለቅቀህ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው መኖር በምትጀምርበት ጊዜ+  አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ሦስት ከተሞችን ለይ።+  አምላክህ ይሖዋ እንድትወርሳት የሚሰጥህን ምድር ሦስት ቦታ ከፋፍላት፤ እንዲሁም ነፍስ ያጠፋ ማንኛውም ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ መሸሽ እንዲችል መንገድ አዘጋጅ።  “እዚያ ለመኖር ሸሽቶ የሄደን፣ ነፍስ ያጠፋ ሰው በተመለከተ መደረግ ያለበት ነገር ይህ ነው፦ ለባልንጀራው የቆየ ጥላቻ የሌለው አንድ ሰው ሳያስበው ባልንጀራውን መትቶ ቢገድለው፣+  ለምሳሌ ከባልንጀራው ጋር እንጨት ለመቁረጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፣ ዛፉንም ለመቁረጥ መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ላይ ወልቆ ባልንጀራውን ቢመታውና ቢገድለው ነፍሰ ገዳዩ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል።+  አለዚያ በንዴት የበገነው* ደም ተበቃይ+ ከተማዋ ሩቅ ከመሆኗ የተነሳ ነፍሰ ገዳዩን አሳዶ ሊደርስበትና ሊገድለው ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ሰው ለባልንጀራው የቆየ ጥላቻ ስለሌለው መሞት አይገባውም።+  ‘ሦስት ከተሞችን ለይ’ በማለት ያዘዝኩህ ለዚህ ነው።  “አምላክህ ይሖዋ ለአባቶችህ በማለላቸው መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህና+ ለእነሱ ለመስጠት ቃል የገባላቸውን ምድር በሙሉ ሲሰጥህ+  ይኸውም አምላክህን ይሖዋን እንድትወድና ዘወትር በመንገዶቹ እንድትሄድ እኔ ዛሬ የማዝህን ይህን ትእዛዝ ሁሉ በመጠበቅህ+ ግዛትህን ሲያሰፋልህ ከእነዚህ ሦስት ከተሞች በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትለያለህ።+ 10  ይህም አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ንጹሕ ደም እንዳይፈስና+ በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዳትሆን ነው።+ 11  “ይሁን እንጂ አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢጠላው፣+ አድብቶም ለሞት የሚያበቃ ጉዳት ቢያደርስበትና ሰውየው ቢሞት፣ ገዳዩም ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ ቢሸሽ 12  የሚኖርበት ከተማ ሽማግሌዎች ሰውየውን ከዚያ በማስመጣት ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይስጡት፤ ይህ ሰው ሞት ይገባዋል።+ 13  አትዘንለት፤* መልካም እንዲሆንልህ ንጹሕ ደም በማፍሰስ የሚመጣን በደል ከእስራኤል አስወግድ።+ 14  “አምላክህ ይሖዋ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ርስትህን በምትቀበልበት ጊዜ የቀድሞ አባቶችህ የከለሉትን ወሰን በማለፍ የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አትንካ።+ 15  “አንድ ሰው የትኛውንም ስህተት ወይም የትኛውንም ኃጢአት ቢፈጽም ግለሰቡን ጥፋተኛ ለማድረግ አንድ ምሥክር አይበቃም።+ ጉዳዩ የሚጸናው ሁለት ምሥክሮች ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል* ነው።+ 16  ተንኮል ያሰበ አንድ ምሥክር አንድን ግለሰብ የሆነ በደል ፈጽሟል በማለት ቢመሠክርበት+ 17  ክርክር የገጠሙት ሁለቱ ሰዎች በይሖዋ ፊት፣ በካህናቱና በዚያን ጊዜ ዳኛ ሆነው በሚያገለግሉት ሰዎች ፊት ይቆማሉ።+ 18  ዳኞቹም ጉዳዩን በጥንቃቄ ይመረምራሉ፤+ ምሥክሩ ሐሰተኛ ምሥክር ከሆነና ወንድሙን የወነጀለው በሐሰት ከሆነ 19  በወንድሙ ላይ ለማድረግ ያቀደውን ነገር በራሱ ላይ አድርጉበት፤+ ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ።+ 20  ሌሎችም ይህን ሲሰሙ ይፈራሉ፤ በመካከልህም እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ፈጽሞ ዳግመኛ አያደርጉም።+ 21  አዘኔታ አታሳይ፤+ ሕይወት* ስለ ሕይወት፣* ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ እንዲሁም እግር ስለ እግር ይሁን።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ልቡ የነደደው።”
ቃል በቃል “ዓይንህ አይዘንለት።”
ቃል በቃል “በሁለት ምሥክሮች ወይም በሦስት ምሥክሮች አፍ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”