ዘዳግም 21:1-23

  • ገዳዩ ስላልታወቀ ሰው የተሰጠ መመሪያ (1-9)

  • የተማረከችን ሴት ስለማግባት (10-14)

  • የበኩር ልጅ መብት (15-17)

  • እልኸኛና ዓመፀኛ ልጅ (18-21)

  • በእንጨት ላይ የሚሰቀል ሰው የተረገመ ነው (22, 23)

21  “አምላክህ ይሖዋ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር አንድ ሰው ሜዳ ላይ ተገድሎ ቢገኝና ማን እንደገደለው ባይታወቅ  ሽማግሌዎችህና ዳኞችህ+ ወጥተው የሞተው ሰው ከተገኘበት ስፍራ አንስቶ በዙሪያው እስከሚገኙት ከተሞች ድረስ ያለውን ርቀት ይለኩ።  ከዚያም የሞተው ሰው ለተገኘበት ስፍራ ቅርብ የሆነችው ከተማ ሽማግሌዎች ምንም ሥራ ያልተሠራባትንና ቀንበር ተጭኖባት የማያውቅን ጊደር ከከብቶች መካከል ይውሰዱ፤  የከተማዋም ሽማግሌዎች ጊደሯን ከዚህ ቀደም ታርሶ ወይም ዘር ተዘርቶበት ወደማያውቅ ወራጅ ውኃ ወዳለበት ሸለቆ* ይውሰዷት፤ በሸለቆውም ውስጥ የጊደሯን አንገት ይስበሩ።+  “ሌዋውያኑ ካህናት ይቅረቡ፤ ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ እሱን እንዲያገለግሉና በይሖዋ ስም እንዲባርኩ+ የመረጠው እነሱን ነው።+ ደግሞም የኃይል ጥቃትን በተመለከተ ለሚነሳ ለማንኛውም ክርክር እልባት የሚሰጡት እነሱ ናቸው።+  ከዚያም የሞተው ሰው ለተገኘበት ስፍራ ቅርብ የሆኑት የከተማዋ ሽማግሌዎች በሙሉ በሸለቆው ውስጥ አንገቷ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ይታጠቡ፤+  እንዲህ ብለውም ይናገሩ፦ ‘እጆቻችን ይህን ደም አላፈሰሱም፤ ዓይኖቻችንም ይህ ደም ሲፈስ አላዩም።  ይሖዋ ሆይ፣ የታደግከውን+ ሕዝብህን እስራኤልን በዚህ ድርጊት ተጠያቂ አታድርገው፤ ንጹሕ ደም በማፍሰስ የተፈጸመ በደልም በሕዝብህ በእስራኤል መካከል እንዲኖር አትፍቀድ።’+ እነሱም በደም ዕዳው ተጠያቂ አይሆኑም።  በዚህ መንገድ ንጹሕ ደም በማፍሰስ የተፈጸመን በደል ከመካከልህ በማስወገድ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርግ። 10  “ከጠላቶችህ ጋር ብትዋጋ፣ አምላክህ ይሖዋም እነሱን በእጅህ አሳልፎ ቢሰጥህ፣ አንተም ምርኮኛ አድርገህ ብትወስዳቸውና+ 11  ከምርኮኞቹ መካከል አንዲት የምታምር ሴት አይተህ ብትወዳት፣ ሚስትህም ልታደርጋት ብትፈልግ 12  ወደ ቤትህ ልትወስዳት ትችላለህ። እሷም ፀጉሯን ትላጭ፤ ጥፍሯንም ትቁረጥ፤ 13  የምርኮኛነት ልብሷን ታውልቅ፤ በቤትህም ትቀመጥ። ለአባቷና ለእናቷ አንድ ወር ሙሉ ታልቅስ፤+ ከዚህ በኋላ ከእሷ ጋር ግንኙነት መፈጸም ትችላለህ፤ አንተ ባሏ ትሆናለህ፤ እሷም ሚስትህ ትሆናለች። 14  በእሷ ካልተደሰትክ ግን ወደፈለገችበት* እንድትሄድ አሰናብታት።+ ሆኖም ለውርደት ስለዳረግካት በገንዘብ ልትሸጣት ወይም ግፍ ልትፈጽምባት አይገባም። 15  “አንድ ሰው ሁለት ሚስቶች ቢኖሩትና አንደኛዋን ከሌላኛዋ አስበልጦ የሚወዳት ቢሆን፣* ሁለቱም ወንዶች ልጆች ቢወልዱለትና በኩሩ የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ+ ቢሆን 16  ውርሱን ለወንዶች ልጆቹ በሚያስተላልፍበት ቀን ከማይወዳት ሚስቱ የተወለደውን በኩር የሆነውን ወንድ ልጅ ትቶ ከሚወዳት ሚስቱ የተወለደውን ወንድ ልጅ እንደ በኩር ልጁ አድርጎ መቁጠር የለበትም። 17  ከዚህ ይልቅ ከማይወዳት ሚስቱ ለተወለደው ወንድ ልጅ፣ ካለው ከማንኛውም ነገር ላይ ሁለት እጥፍ በመስጠት የልጁን ብኩርና መቀበል ይኖርበታል፤ ምክንያቱም የጎልማሳነቱ ብርታት መጀመሪያ ይህ ልጅ ነው። የብኩርና መብቱ የእሱ ነው።+ 18  “አንድ ሰው እልኸኛና ዓመፀኛ ልጅ ቢኖረው ልጁም አባቱንም ሆነ እናቱን ለመታዘዝ አሻፈረኝ ቢል፣+ እነሱም እርማት ሊሰጡት ቢሞክሩና እሱ ግን ሊሰማቸው ፈቃደኛ ባይሆን+ 19  አባትና እናቱ እሱ ባለበት ከተማ በር ላይ ወዳሉት ሽማግሌዎች ያምጡት፤ 20  ሽማግሌዎቹንም ‘ይህ ልጃችን እልኸኛና ዓመፀኛ ነው፤ ሊታዘዘንም ፈቃደኛ አይደለም። ሆዳምና+ ሰካራም+ ነው’ ይበሏቸው። 21  ከዚያም የከተማዋ ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት። በዚህ መንገድ ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ፤ እስራኤላውያንም ሁሉ ይህን ሰምተው ይፈራሉ።+ 22  “አንድ ሰው ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት ሠርቶ ቢገደልና+ በእንጨት ላይ ብትሰቅለው+ 23  በድኑ በእንጨቱ ላይ አይደር።+ ከዚህ ይልቅ በዚያው ዕለት ቅበረው፤ ምክንያቱም እንጨት ላይ የሚሰቀለው፣ አምላክ የረገመው ነው፤+ አንተም አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርጎ የሚሰጥህን ምድር አታርክስ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “ነፍሷ ወዳሻት።”
ቃል በቃል “አንደኛዋ የምትወደድ፣ ሌላኛዋ የምትጠላ ብትሆን።”