ዘዳግም 23:1-25

  • ወደ አምላክ ጉባኤ መግባት የሌለባቸው (1-8)

  • የሰፈሩን ንጽሕና መጠበቅ (9-14)

  • ከጌታው የኮበለለ ባሪያ (15, 16)

  • ዝሙት አዳሪነት የተከለከለ ነው (17, 18)

  • ወለድና ስእለት (19-23)

  • እሸት ቀጥፎ ስለመብላት (24, 25)

23  “የዘር ፍሬው ተቀጥቅጦ የተኮላሸ ወይም ብልቱ የተቆረጠ ማንኛውም ሰው ወደ ይሖዋ ጉባኤ አይግባ።+  “ዲቃላ ወደ ይሖዋ ጉባኤ አይግባ።+ ሌላው ቀርቶ እስከ አሥረኛ ትውልድ ድረስ ዘሮቹ ወደ ይሖዋ ጉባኤ አይግቡ።  “አሞናውያንም ሆኑ ሞዓባውያን ወደ ይሖዋ ጉባኤ አይግቡ።+ ሌላው ቀርቶ እስከ አሥረኛ ትውልድ ድረስ ዘሮቻቸው ፈጽሞ ወደ ይሖዋ ጉባኤ አይግቡ፤  ምክንያቱም እነሱ ከግብፅ ወጥታችሁ እየተጓዛችሁ በነበረበት ጊዜ ምግብና ውኃ በመስጠት አልረዷችሁም፤+ ደግሞም በሜሶጶጣሚያ በምትገኘው በጰቶር የሚኖረው የቢዖር ልጅ በለዓም አንተን እንዲረግም በገንዘብ ቀጥረውት ነበር።+  አምላክህ ይሖዋ ግን በለዓምን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም።+ ከዚህ ይልቅ አምላክህ ይሖዋ ለአንተ ሲል እርግማኑን ወደ በረከት ለወጠው፤+ ይህን ያደረገው አምላክህ ይሖዋ ስለወደደህ ነው።+  በዘመንህ ሁሉ መቼም ቢሆን ለእነሱ ሰላምን ወይም ብልጽግናን አትመኝ።+  “ወንድምህ ስለሆነ ኤዶማዊውን አትጥላው።+ “የባዕድ አገር ሰው ሆነህ በአገሩ ትኖር ስለነበር ግብፃዊውን አትጥላው።+  ለእነሱ የሚወለዱላቸው የሦስተኛው ትውልድ ልጆች ወደ ይሖዋ ጉባኤ መግባት ይችላሉ።  “ጠላትህን ለመውጋት ወጥተህ በምትሰፍርበት ጊዜ ከማንኛውም መጥፎ* ነገር መራቅ ይኖርብሃል።+ 10  አንድ ሰው ዘሩ በመፍሰሱ ምክንያት ቢረክስ+ ከሰፈሩ ውጭ ይውጣ፤ ወደ ሰፈሩም ተመልሶ አይግባ። 11  አመሻሹ ላይ በውኃ ይታጠብ፤ ከዚያም ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ወደ ሰፈሩ ተመልሶ መግባት ይችላል።+ 12  ለመጸዳጃ የሚሆን ቦታ ከሰፈሩ ውጭ አዘጋጅ፤ አንተም መሄድ ያለብህ ወደዚያ ነው። 13  ከመሣሪያዎችህም ጋር መቆፈሪያ ያዝ። ውጭ በምትጸዳዳበትም ጊዜ በመቆፈሪያው ጉድጓድ ቆፍር፤ ከዚያም በዓይነ ምድርህ ላይ አፈሩን መልስበት። 14  ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ ሊታደግህና ጠላቶችህን በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈሩ ውስጥ ይዘዋወራል፤+ በመሆኑም ነውር የሆነ ምንም ነገር እንዳያይብህና ከአንተ ጋር መሄዱን እንዳይተው ሰፈርህ ቅዱስ መሆን አለበት።+ 15  “አንድ ባሪያ ከጌታው አምልጦ ወደ አንተ ቢመጣ መልሰህ ለጌታው አትስጠው። 16  ከከተሞችህ መካከል በመረጠውና ደስ ባለው ቦታ አብሮህ ሊኖር ይችላል። በደል አትፈጽምበት።+ 17  “ከእስራኤል ሴቶች ልጆች መካከል የትኛዋም የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪ አትሁን፤+ ከእስራኤል ወንዶች ልጆችም መካከል የትኛውም የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪ አይሁን።+ 18  ለሴት ዝሙት አዳሪ የተከፈለን ዋጋም ሆነ ለወንድ ዝሙት አዳሪ* የተከፈለን ዋጋ* አንድን ስእለት ለመፈጸም ስትል ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ቤት አታምጣ፤ ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ ሁለቱንም ይጸየፋቸዋል። 19  “ወንድምህን ወለድ አታስከፍለው፤+ ከገንዘብም ሆነ ከእህል ወይም ወለድ ሊያስከፍል ከሚችል ከማንኛውም ነገር ወለድ አታስከፍለው። 20  ከባዕድ አገር ሰው ወለድ መጠየቅ ትችላለህ፤+ ሆኖም አምላክህ ይሖዋ ገብተህ በምትወርሳት ምድር በሥራህ ሁሉ እንዲባርክህ+ ወንድምህን ወለድ አታስከፍለው።+ 21  “ለአምላክህ ለይሖዋ ስእለት ከተሳልክ+ ለመፈጸም አትዘግይ።+ ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ በእርግጥ ከአንተ ይፈልገዋል፤ አለዚያ ኃጢአት ይሆንብሃል።+ 22  ሳትሳል ከቀረህ ግን ኃጢአት አይሆንብህም።+ 23  ከአፍህ የወጣውን ቃል ጠብቅ፤+ ለአምላክህ ለይሖዋ የፈቃደኝነት መባ አድርገህ ለማቅረብ በገዛ አንደበትህ የተሳልከውን ፈጽም።+ 24  “ወደ ባልንጀራህ የወይን እርሻ ከገባህ እስክትጠግብ* ድረስ ወይን መብላት ትችላለህ፤ በዕቃህ ግን ምንም ይዘህ አትሂድ።+ 25  “ወደ ባልንጀራህ የእህል ማሳ ከገባህ እሸት ቀጥፈህ መብላት ትችላለህ፤ ሆኖም የባልንጀራህን እህል በማጭድ ማጨድ የለብህም።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የሚያረክስ።”
ቃል በቃል “ለውሻ።”
ወይም “ወንድ ዝሙት አዳሪ የሚያገኘውን ገቢ።”
ወይም “ነፍስህ እስክትረካ።”