ዘዳግም 25:1-19
25 “በሰዎች መካከል አለመግባባት ቢፈጠር ሰዎቹ ዳኞች ፊት መቅረብ ይችላሉ፤+ እነሱም ይዳኟቸዋል፤ ጻድቅ የሆነውን ንጹሕ፣ ጥፋተኛ የሆነውን ደግሞ በደለኛ ይሉታል።+
2 ጥፋተኛው መገረፍ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ+ ዳኛው መሬት ላይ እንዲያስተኙትና እሱ ባለበት እንዲገረፍ ያደርጋል። የግርፋቱም ቁጥር ከሠራው ጥፋት ጋር የሚመጣጠን ይሁን።
3 እስከ 40 ግርፋት ሊገርፈው ይችላል፤+ ከዚያ ማስበለጥ ግን የለበትም። ከዚህ የበለጠ ብዙ ግርፋት ከገረፈው ግን ወንድምህ በፊትህ ይዋረዳል።
4 “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር።+
5 “ወንድማማቾች አንድ ላይ ሲኖሩ ቆይተው ከመካከላቸው አንዱ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት የሟቹ ሚስት ከቤተሰቡ ውጭ የሆነ ሰው ማግባት የለባትም። የባሏ ወንድም ወደ እሷ በመሄድ ሚስቱ አድርጎ ይውሰዳት፤ የዋርሳነት ግዴታውንም ይፈጽምላት።+
6 መጀመሪያ የምትወልደው ልጅ በሟች ወንድሙ ስም ይጠራል፤+ ይህ የሚሆነው የሟቹ ስም ከእስራኤል መካከል እንዳይጠፋ ነው።+
7 “ሰውየው የሟች ወንድሙን ሚስት ለማግባት ፈቃደኛ ካልሆነ መበለት የሆነችው ሴት በከተማዋ በር ወደሚገኙት ሽማግሌዎች ሄዳ ‘የባሌ ወንድም የወንድሙ ስም ከእስራኤል መካከል እንዳይጠፋ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። የዋርሳነት ግዴታውን ሊፈጽምልኝ አልተስማማም’ ትበላቸው።
8 የከተማዋ ሽማግሌዎችም ጠርተው ያናግሩት። እሱም ‘እኔ እሷን ማግባት አልፈልግም’ ብሎ በሐሳቡ ከጸና
9 የወንድሙ ሚስት በሽማግሌዎቹ ፊት ወደ እሱ ቀርባ ጫማውን ከእግሩ ላይ ታውልቅ፤+ ከዚያም ፊቱ ላይ ትትፋበትና ‘የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ የሚደረግበት እንዲህ ነው’ ትበል።
10 ከዚያ በኋላ የዚያ ሰው ቤተሰብ ስም* በእስራኤል ውስጥ ‘ጫማው የወለቀበት ሰው ቤት’ ይባላል።
11 “ሁለት ሰዎች ቢደባደቡና የአንደኛው ሚስት ባሏን ከደብዳቢው እጅ ለማስጣል ስትል እጇን ዘርግታ ብልቱን ብትይዝ
12 እጇን ቁረጠው። ልታዝንላት አይገባም።*
13 “በከረጢትህ ውስጥ ትልቅና ትንሽ የሆኑ ሁለት ዓይነት የሚዛን ድንጋዮች አይኑሩህ።+
14 በቤትህም ውስጥ ትልቅና ትንሽ የሆኑ ሁለት ዓይነት መስፈሪያዎች* አይኑሩህ።+
15 አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም ትክክለኛና ሐቀኛ ሚዛን እንዲሁም ትክክለኛና ሐቀኛ መስፈሪያ ይኑርህ።+
16 ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ነገሮችን በማድረግ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት የሚፈጽም ሰው ሁሉ በአምላክህ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው።+
17 “ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ መንገድ ላይ ሳላችሁ አማሌቃውያን ያደረጉባችሁን ነገር አስታውሱ፤+
18 በጉዞ ላይ ሳለህ ደክመህና ዝለህ በነበረበት ጊዜ አግኝተውህ ከኋላ ከኋላህ እያዘገሙ በነበሩት ሁሉ ላይ እንዴት ጥቃት እንደሰነዘሩ አስታውስ። አምላክንም አልፈሩም።
19 አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርገህ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ላይ አምላክህ ይሖዋ በዙሪያህ ካሉት ጠላቶችህ ሁሉ በሚያሳርፍህ ጊዜ+ አማሌቃውያንን ከሰማይ በታች ጨርሶ እንዳይታወሱ አድርገህ ጠራርገህ አጥፋቸው።+ ይህን አትርሳ።