ዘዳግም 27:1-26

  • ሕጉ በድንጋዮች ላይ መጻፍ ይኖርበታል (1-10)

  • በኤባልና በገሪዛን ተራራ ላይ (11-14)

  • እርግማኑ ተነበበ (15-26)

27  ከዚያም ሙሴ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “እኔ ዛሬ የምሰጣችሁን ትእዛዛት በሙሉ ጠብቁ።  አምላካችሁ ይሖዋ ወደሚሰጣችሁ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በምትሻገሩበት ቀን ትላልቅ ድንጋዮችን አቁማችሁ ለስኗቸው።*+  ከዚያም የአባቶችህ አምላክ ይሖዋ ቃል በገባልህ መሠረት አምላክህ ይሖዋ ወደሚሰጥህ ምድር ይኸውም ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር+ ለመግባት በምትሻገርበት ጊዜ የዚህን ሕግ ቃላት በሙሉ ጻፍባቸው።  ዮርዳኖስን ስትሻገሩ ዛሬ በሰጠኋችሁ ትእዛዝ መሠረት እነዚህን ድንጋዮች በኤባል ተራራ+ ላይ አቁሟቸው፤ ደግሞም ለስኗቸው።*  በዚያም ለአምላክህ ለይሖዋ መሠዊያ ይኸውም የድንጋይ መሠዊያ ሥራ። ድንጋዮቹንም የብረት መሣሪያ አታስነካቸው።+  የአምላክህን የይሖዋን መሠዊያ ካልተጠረበ ድንጋይ ሥራ፤ በላዩም ላይ ለአምላክህ ለይሖዋ የሚቃጠሉ መባዎችን አቅርብ።  የኅብረት መሥዋዕቶችንም አቅርብ፤+ መሥዋዕቶቹንም እዚያው ብላቸው፤+ አንተም በአምላክህ በይሖዋ ፊት ደስ ይልሃል።+  በድንጋዮቹም ላይ የዚህን ሕግ ቃላት በሙሉ በግልጽ ጻፍባቸው።”+  ከዚያም ሙሴና ሌዋውያኑ ካህናት እስራኤላውያንን በሙሉ እንዲህ አሏቸው፦ “እስራኤል ሆይ፣ ጸጥ ብለህ አዳምጥ። በዛሬው ቀን አንተ የአምላክህ የይሖዋ ሕዝብ ሆነሃል።+ 10  የአምላክህን የይሖዋን ቃል ስማ፤ እኔ ዛሬ የማዝህን የእሱን ትእዛዛትና ሥርዓቶች ፈጽም።”+ 11  ሙሴም በዚያ ቀን ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፦ 12  “ዮርዳኖስን በምትሻገሩበት ጊዜ በገሪዛን ተራራ+ ላይ ቆመው ሕዝቡን የሚባርኩት ነገዶች ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዮሴፍ እና ቢንያም ናቸው። 13  እርግማኑን ለማሰማት በኤባል ተራራ+ ላይ የሚቆሙት ደግሞ ሮቤል፣ ጋድ፣ አሴር፣ ዛብሎን፣ ዳን እና ንፍታሌም ናቸው። 14  ሌዋውያኑም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ለእያንዳንዱ እስራኤላዊ እንዲህ ብለው ይናገራሉ፦+ 15  “‘ይሖዋ የሚጠላውን አስጸያፊ ነገር+ ይኸውም የአንድ የእጅ ጥበብ ባለሙያ* የእጅ ሥራ ውጤት የሆነውን የተቀረጸ ምስል+ ወይም ከብረት የተሠራ ሐውልት*+ የሚሠራና በስውር የሚያስቀምጥ ሰው የተረገመ ይሁን።’ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’* ብሎ ይመልሳል።) 16  “‘አባቱን ወይም እናቱን የሚንቅ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 17  “‘የጎረቤቱን የወሰን ምልክት የሚገፋ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 18  “‘ዓይነ ስውሩን መንገድ የሚያሳስት የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 19  “‘የባዕድ አገሩን ሰው፣ አባት የሌለውን* ልጅ ወይም የመበለቲቱን ፍርድ የሚያዛባ+ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 20  “‘ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ አባቱን ስላዋረደ* የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 21  “‘ከማንኛውም ዓይነት እንስሳ ጋር የሚተኛ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 22  “‘የአባቱ ልጅ ወይም የእናቱ ልጅ ከሆነችው ከእህቱ ጋር የሚተኛ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 23  “‘ከሚስቱ እናት ጋር የሚተኛ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 24  “‘ጎረቤቱን አድብቶ በመጠበቅ የሚገድል የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 25  “‘ንጹሑን ሰው* ለመግደል ሲል ጉቦ የሚቀበል የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።) 26  “‘የዚህን ሕግ ቃል ተግባራዊ በማድረግ የማይጠብቅ ሰው የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ኖራ ቀቧቸው።”
ወይም “ኖራ ቀቧቸው።”
ወይም “ይሁን!”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልት።”
ወይም “የእንጨትና የብረት ሠራተኛ።”
ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን።”
ቃል በቃል “የአባቱን ቀሚስ ስለገለጠ።”
ወይም “የንጹሑን ደም ነፍስ።”