ዘዳግም 3:1-29

  • የባሳንን ንጉሥ ኦግን ድል አደረጉ (1-7)

  • ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ምድር ተከፋፈሉ (8-20)

  • ኢያሱ እንዳይፈራ ማበረታቻ ተሰጠው (21, 22)

  • ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደማይገባ ተነገረው (23-29)

3  “ከዚያም ተመልሰን በባሳን መንገድ ወጣን። የባሳን ንጉሥ ኦግም ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በመሆን ኤድራይ ላይ ጦርነት ሊገጥመን ወጣ።+  በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘እሱንም ሆነ ሕዝቡን ሁሉ እንዲሁም ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥህ አትፍራው፤ አንተም በሃሽቦን ይኖር በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሲሖን ላይ እንዳደረግከው ሁሉ በእሱም ላይ ታደርግበታለህ።’  ስለዚህ አምላካችን ይሖዋ የባሳንን ንጉሥ ኦግንና ሕዝቡን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጠን፤ እኛም ከሕዝቡ መካከል አንድም ሰው ሳናስቀር ሁሉንም ደመሰስን።  ከዚያም ከተሞቹን በሙሉ ያዝን። ከእነሱ ያልወሰድነው አንድም ከተማ አልነበረም፤ በባሳን ባለው በኦግ መንግሥት ሥር የሚገኘውን የአርጎብን ክልል በሙሉ ይኸውም 60 ከተሞችን ወሰድን።+  እነዚህ ከተሞች በሙሉ በረጃጅም ቅጥሮች የታጠሩ እንዲሁም በሮችና መቀርቀሪያዎች ያሏቸው ነበሩ፤ ከእነዚህም በተጨማሪ በጣም ብዙ የገጠር ከተሞች ነበሩ።  ሆኖም እያንዳንዱን ከተማ እንዲሁም ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን+ በማጥፋት በሃሽቦን ንጉሥ በሲሖን ላይ እንዳደረግነው ሁሉ እነዚህንም ሙሉ በሙሉ ደመሰስናቸው።+  ከብቶቹንና ከየከተማው የማረክናቸውን ነገሮች ሁሉ ለራሳችን ወሰድን።  “በዚያን ጊዜም ከአርኖን ሸለቆ* አንስቶ እስከ ሄርሞን ተራራ+ ድረስ ባለው በዮርዳኖስ ክልል ከነበሩት ከሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት እጅ ምድራቸውን ወሰድን፤+  (ሲዶናውያን የሄርሞንን ተራራ ሲሪዮን ብለው ሲጠሩት አሞራውያን ደግሞ ሰኒር ብለው ይጠሩት ነበር፤) 10  በባሳን ባለው በኦግ መንግሥት ሥር የሚገኙትን ከተሞች ይኸውም በአምባው ላይ የሚገኙትን ከተሞች በሙሉ፣ ጊልያድን በሙሉ፣ ባሳንን በሙሉ እስከ ሳልካ ድረስ እንዲሁም ኤድራይን+ ወሰድን። 11  ከረፋይም ወገን የተረፈው የባሳን ንጉሥ ኦግ ብቻ ነበር። ቃሬዛው እንኳ የብረት* ቃሬዛ* ነበር፤ አሁንም የአሞናውያን ከተማ በሆነችው በራባ ይገኛል። በሰው ክንድ* ሲለካ ርዝመቱ ዘጠኝ ክንድ ስፋቱ ደግሞ አራት ክንድ ነበር። 12  በዚያን ጊዜ ይህችን ምድር ወረስን፤ በአርኖን ሸለቆ* አጠገብ ከምትገኘው ከአሮዔር+ አንስቶ ያለውን ምድር እንዲሁም የጊልያድን ተራራማ አካባቢ እኩሌታ ከነከተሞቹ ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን ሰጠኋቸው።+ 13  የቀረውን የጊልያድን ክፍልና በኦግ ግዛት ሥር ያለውን ባሳንን በሙሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ።+ የባሳን ይዞታ የሆነው የአርጎብ አካባቢ በሙሉ የረፋይም ምድር ተብሎ ይጠራ ነበር። 14  “የምናሴ ልጅ ያኢር+ የአርጎብን ክልል+ በሙሉ እስከ ገሹራውያን እና እስከ ማአካታውያን+ ወሰን ድረስ ያለውን ወሰደ፤ በባሳን የሚገኙትን እነዚህን መንደሮች በራሱ ስም ሃዎትያኢር*+ ብሎ ሰየማቸው፤ እስከ ዛሬም ድረስ የሚጠሩት በዚህ ስም ነው። 15  ጊልያድን ደግሞ ለማኪር ሰጠሁት።+ 16  ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን+ የአርኖንን ሸለቆ* መሃል ወሰን በማድረግ ከጊልያድ አንስቶ እስከ አርኖን ሸለቆ ድረስ እንዲሁም የአሞናውያን ወሰን እስከሆነው ሸለቆ ማለትም እስከ ያቦቅ ድረስ ሰጠኋቸው፤ 17  እንዲሁም ከኪኔሬት አንስቶ በአረባ እስከሚገኘው ባሕር ይኸውም በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ በጲስጋ ሸንተረር ግርጌ እስከሚገኘው እስከ ጨው ባሕር* ድረስ ያለውን አረባን፣ ዮርዳኖስንና ወሰኑን ሰጠኋቸው።+ 18  “ከዚያም ይህን ትእዛዝ ሰጠኋችሁ፦ ‘አምላካችሁ ይሖዋ ይህችን ምድር ርስት አድርጋችሁ እንድትወርሷት ሰጥቷችኋል። ብርቱ የሆናችሁት ወንዶች ሁሉ የጦር መሣሪያችሁን ታጥቃችሁ በወንድሞቻችሁ በእስራኤላውያን ፊት ትሻገራላችሁ።+ 19  ሚስቶቻችሁ፣ ልጆቻችሁና ከብቶቻችሁ ብቻ (መቼም ብዙ ከብቶች እንዳሏችሁ አውቃለሁ) በሰጠኋችሁ ከተሞች ውስጥ ይቀራሉ፤ 20  ይህም ይሖዋ ልክ ለእናንተ እንዳደረገላችሁ ሁሉ ለወንድሞቻችሁም እረፍት እስኪሰጣቸው እንዲሁም አምላካችሁ ይሖዋ ከዮርዳኖስ ማዶ የሚሰጣቸውን ምድር ርስት አድርገው እስኪወርሱ ድረስ ነው። ከዚያ በኋላ እያንዳንዳችሁ ወደሰጠኋችሁ ወደየራሳችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።’+ 21  “በዚያን ጊዜ ለኢያሱ ይህን ትእዛዝ ሰጠሁት፦+ ‘አምላክህ ይሖዋ በእነዚህ ሁለት ነገሥታት ላይ ያደረገውን ሁሉ በገዛ ዓይንህ አይተሃል። ይሖዋ አልፈሃቸው በምትሄደው መንግሥታት ሁሉ ላይ እንዲሁ ያደርጋል።+ 22  ስለ እናንተ የሚዋጋው+ አምላካችሁ ይሖዋ ስለሆነ አትፍሯቸው።’ 23  “እኔም በዚያን ጊዜ ይሖዋን እንዲህ በማለት ተማጸንኩት፦ 24  ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህ ታላቅነትህንና ብርቱ ክንድህን እንዲያይ አድርገሃል፤+ አንተ እንደምታደርጋቸው ያሉ ታላላቅ ነገሮችን መፈጸም የሚችለው በሰማይም ሆነ በምድር ያለ የትኛው አምላክ ነው?+ 25  እባክህ ከዮርዳኖስ ማዶ ያለችውን መልካሚቱን ምድር፣ አዎ ውብ የሆነችውን ይህችን ተራራማ አካባቢና ሊባኖስን ተሻግሬ እንዳይ ፍቀድልኝ።’+ 26  ይሖዋ ግን በእናንተ የተነሳ በጣም ተቆጥቶኝ ስለነበር+ አልሰማኝም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘በቃ! ዳግመኛ ስለዚህ ጉዳይ እንዳታነሳብኝ። 27  ይህን ዮርዳኖስን ስለማትሻገር ወደ ጲስጋ አናት ውጣና+ ዓይንህን አቅንተህ ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅ ተመልከት።+ 28  በዚህ ሕዝብ ፊት የሚሻገረውም+ ሆነ አንተ ያየሃትን ምድር እንዲወርሱ የሚያደርገው ኢያሱ ስለሆነ እሱን መሪ አድርገህ ሹመው፤+ አደፋፍረው፤ አበረታታውም።’ 29  ይህ ሁሉ የሆነው በቤትጰኦር+ ፊት ለፊት በሚገኘው ሸለቆ ውስጥ በነበርንበት ጊዜ ነው።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
“የጥቁር ባልጩት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በድንጋይ የተሠራ የሬሳ ሣጥን፤ የሬሳ ሣጥን።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
“የያኢር የድንኳን መንደሮች” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ሙት ባሕርን ያመለክታል።