ዘዳግም 30:1-20

  • ወደ ይሖዋ መመለስ (1-10)

  • የይሖዋ ትእዛዛት ከባድ አይደሉም (11-14)

  • ከሕይወትና ከሞት አንዱን መምረጥ (15-20)

30  “ይህ ቃል ሁሉ ይኸውም በፊትህ ያስቀመጥኩት በረከትና እርግማን+ በአንተ ላይ በሚመጣበትና አምላክህ ይሖዋ በመካከላቸው እንድትበተን ባደረገህ ብሔራት ምድር+ ሆነህ ይህን ቃል ሁሉ በምታስታውስበት* ጊዜ+  እንዲሁም አንተም ሆንክ ልጆችህ እኔ ዛሬ በማዝህ ትእዛዝ ሁሉ መሠረት በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ*+ ወደ አምላካችሁ ወደ ይሖዋ በምትመለሱበትና ቃሉን በምትሰሙበት ጊዜ+  አምላክህ ይሖዋ ተማርከው የተወሰዱብህን ይመልስልሃል፤+ ምሕረትም ያሳይሃል፤+ እንዲሁም አምላክህ ይሖዋ በመካከላቸው እንድትበተን ካደረገህ ሕዝቦች ምድር ሁሉ መልሶ ይሰበስብሃል።+  ሕዝብህ እስከ ሰማያት ዳርቻ ድረስ ቢበተን እንኳ አምላክህ ይሖዋ ከዚያ ይሰበስብሃል፤ ከዚያም መልሶ ያመጣሃል።+  አምላክህ ይሖዋ አባቶችህ ወርሰዋት ወደነበሩት ምድር ያስገባሃል፤ አንተም ትወርሳታለህ፤ እሱም ከአባቶችህ ይበልጥ ያበለጽግሃል፤ እንዲሁም ያበዛሃል።+  በሕይወትም ትኖር ዘንድ አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህና በሙሉ ነፍስህ* እንድትወደው+ አምላክህ ይሖዋ ልብህን እንዲሁም የልጆችህን ልብ ያነጻል።*+  ከዚያም አምላክህ ይሖዋ እነዚህን እርግማኖች ሁሉ በሚጠሉህና በሚያሳድዱህ ጠላቶችህ ላይ ያመጣል።+  “አንተም ተመልሰህ የይሖዋን ቃል ትሰማለህ፤ እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዛቱን ሁሉ ትፈጽማለህ።  አምላክህ ይሖዋ በአባቶችህ ደስ እንደተሰኘ+ ሁሉ ይሖዋ አንተንም በማበልጸግ ስለሚደሰት የሆድህን ፍሬ፣ እንስሶችህንና የምድርህን ፍሬ በማብዛት በእጅህ ሥራ ሁሉ እጅግ እንድትበለጽግ ያደርግሃል።+ 10  ይህም የሚሆነው የአምላክህን የይሖዋን ቃል ስለምትሰማ፣ በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዛቱንና ደንቦቹን ስለምትጠብቅ እንዲሁም በሙሉ ልብህና በሙሉ ነፍስህ* ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ስለምትመለስ ነው።+ 11  “እኔ ዛሬ የማዝህ ይህ ትእዛዝ ለአንተ ያን ያህል ከባድ አይደለም፤ ከአንተም የራቀ አይደለም።+ 12  ‘ሰምተን እንድንፈጽመው ወደ ሰማይ ወጥቶ ማን ያምጣልን?’ እንዳትል ትእዛዙ ያለው በሰማይ አይደለም።+ 13  ደግሞም ‘ሰምተን እንድንፈጽመው ባሕሩን ተሻግሮ ማን ያምጣልን?’ እንዳትል ትእዛዙ ያለው ከባሕሩ ማዶ አይደለም። 14  ቃሉ ትፈጽመው ዘንድ+ ለአንተ በጣም ቅርብ ነውና፤ ደግሞም በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው።+ 15  “እንግዲህ እኔ ዛሬ ሕይወትንና መልካም ነገርን እንዲሁም ሞትንና መጥፎ ነገርን በፊትህ አስቀምጫለሁ።+ 16  አምላክህን ይሖዋን በመውደድ፣+ በመንገዶቹ በመሄድ እንዲሁም ትእዛዛቱን፣ ደንቦቹንና ድንጋጌዎቹን በመጠበቅ እኔ ዛሬ የማዝህን የአምላክህን የይሖዋን ትእዛዛት ብትሰማ በሕይወት ትኖራለህ፤+ ደግሞም ትበዛለህ፤ አምላክህ ይሖዋም በምትወርሳት ምድር ውስጥ ይባርክሃል።+ 17  “ሆኖም ልብህ ቢሸፍትና+ ለመስማት ፈቃደኛ ባትሆን እንዲሁም ተታለህ ለሌሎች አማልክት ብትሰግድና ብታገለግላቸው+ 18  በእርግጥ እንደምትጠፉ+ በዛሬው ዕለት እነግራችኋለሁ። ደግሞም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ላይ ዕድሜያችሁ ያጥራል። 19  ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና እርግማንን በፊታችሁ እንዳስቀመጥኩ+ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምሥክሮች አድርጌ እጠራባችኋለሁ፤ እንግዲህ አንተም ሆንክ ዘሮችህ+ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤+ 20  ይህን የምታደርገው አምላክህን ይሖዋን በመውደድ፣+ ቃሉን በመስማትና ከእሱ ጋር በመጣበቅ ነው፤+ ምክንያቱም እሱ ሕይወትህ ነው፤ ይሖዋ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለመስጠት በማለላቸው ምድር ረጅም ዕድሜ የምትኖረውም በእሱ ነው።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ወደ ልብህ መልሰህ በምታመጣበት።”
ቃል በቃል “ይገርዛል።”