ዘዳግም 32:1-52

  • የሙሴ መዝሙር (1-47)

    • ይሖዋ ዓለት ነው (4)

    • እስራኤል ዓለት የሆነለትን አምላክ ረሳ (18)

    • ‘በቀል የእኔ ነው’ (35)

    • “እናንተ ብሔራት ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” (43)

  • ሙሴ በነቦ ተራራ ላይ እንደሚሞት ተነገረው (48-52)

32  “ሰማያት ሆይ፣ ጆሯችሁን ስጡኝ፤ እኔም እናገራለሁ፤ምድርም የአፌን ቃል ትስማ።   ትምህርቴ እንደ ዝናብ ይወርዳል፤ካፊያ ሣር ላይ እንደሚወርድ፣የሚያረሰርስ ዝናብም ተክልን እንደሚያጠጣ፣ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠባል።   የይሖዋን ስም አውጃለሁና።+ ስለ አምላካችን ታላቅነት ተናገሩ!+   እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤+መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና።+ እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል+ ታማኝ+ አምላክ ነው፤ጻድቅና ትክክለኛ ነው።+   ምግባረ ብልሹ የሆኑት እነሱ ናቸው።+ ልጆቹ አይደሉም፤ ጉድለቱ የራሳቸው ነው።+ ጠማማና ወልጋዳ ትውልድ ናቸው!+   እናንተ ሞኞችና ጥበብ የጎደላችሁ ሰዎች ሆይ፣+በይሖዋ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ?+ ወደ ሕልውና ያመጣህ አባትህ እሱ አይደለም?+የሠራህና አጽንቶ ያቆመህስ እሱ አይደለም?   የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤ያለፉት ትውልዶች የኖሩባቸውን ዓመታት መለስ ብለህ አስብ። አባትህን ጠይቅ፤ ሊነግርህ ይችላል፤+ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ይነግሩሃል።   ልዑሉ ለብሔራት ርስታቸውን ሲሰጥ፣+የአዳምን ልጆች* አንዱን ከሌላው ሲለያይ፣+በእስራኤል ልጆች ቁጥር ልክ+የሕዝቦችን ወሰን ደነገገ።+   የይሖዋ ሕዝብ ድርሻው ነው፤+ያዕቆብ ርስቱ ነው።+ 10  እሱን ምድረ በዳ በሆነ ምድር፣+ነፋስ በሚያፏጭበት ጭው ያለ በረሃ አገኘው።+ ሊጠብቀውም ዙሪያውን ከበበው፤ ተንከባከበው፤+እንደ ዓይኑም ብሌን ጠበቀው።+ 11  ንስር ጎጆዋን እንደምትነቀንቅናከጫጩቶቿ በላይ እንደምታንዣብብ፣ክንፎቿን ዘርግታ እንደምትይዛቸው፣በላባዎቿም እንደምትሸከማቸው ሁሉ+ 12  ይሖዋ ብቻውን መራው፤*+ከእሱም ጋር ምንም ባዕድ አምላክ አልነበረም።+ 13  በምድር ላይ በሚገኙ ከፍ ያሉ ቦታዎች እንዲሄድ አደረገው፤+ስለሆነም የእርሻውን ምርት በላ።+ ከዓለት ማር አበላው፤ከባልጩትም ዘይት መገበው፤ 14  የላሞቹን ቅቤና የመንጋውን ወተትምርጥ ከሆነው በግ* ጋር ሰጠው፤የባሳንን አውራ በጎችና አውራ ፍየሎችከምርጥ ስንዴ* ጋር ሰጠው፤+አንተም ከወይን ፍሬው ደም* የወይን ጠጅ ጠጣህ። 15  የሹሩን* ሲወፍር በዓመፀኝነት ተራገጠ። ሰባህ፤ ፈረጠምክ፤ ደለብክ።+ ስለሆነም የሠራውን አምላክ ተወ፤+አዳኝ የሆነለትን ዓለት ናቀ። 16  በባዕዳን አማልክት አስቆጡት፤+በአስጸያፊ ነገሮችም አሳዘኑት።+ 17  ለአምላክ ሳይሆን ለአጋንንት፣+ለማያውቋቸው አማልክት፣በቅርቡ ለተነሱ ለአዲሶች፣አባቶቻችሁ ለማያውቋቸው አማልክት ይሠዉ ነበር። 18  አባት የሆነህን ዓለት ረሳኸው፤+የወለደህንም አምላክ አላስታወስክም።+ 19  ይሖዋ ይህን ሲያይ ተዋቸው፤+ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ አሳዝነውት ነበርና። 20  ስለዚህ እንዲህ አለ፦ ‘ፊቴን ከእነሱ እሰውራለሁ፤+ምን እንደሚሆኑም አያለሁ። ምክንያቱም እነሱ ጠማማ ትውልድ ናቸው፤+ታማኝነት የሚባል ነገር የማያውቁ ልጆች ናቸው።+ 21  እነሱ አምላክ ባልሆነው አስቆጡኝ፤+ከንቱ በሆኑ ጣዖቶቻቸው አሳዘኑኝ።+ በመሆኑም እኔ ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤+ሞኝ በሆነ ብሔር አበሳጫቸዋለሁ።+ 22  ምክንያቱም ቁጣዬ እሳት አቀጣጥሏል፤+እሱም እስከ መቃብር* ጥልቀት ድረስ ዘልቆ ይነድዳል፤+ምድርንና ምርቷን ይበላል፤የተራሮችንም መሠረት ያቃጥላል። 23  መከራቸውን አበዛዋለሁ፤ቀስቶቼን በእነሱ ላይ እጨርሳለሁ። 24  በረሃብ ይዳከማሉ፤+በሚያቃጥል ትኩሳትና በመራራ ጥፋት ይበላሉ።+ የአራዊትን ጥርስ፣በምድር ላይ የሚሳቡ እንስሳትንም መርዝ እልክባቸዋለሁ።+ 25  ወጣቱንም ሆነ ልጃገረዲቱን፣ጨቅላውንም ሆነ ሽማግሌውን፣+በውጭ፣ ሰይፍ ለሐዘን ይዳርጋቸዋል፤+በቤት ውስጥ ደግሞ ሽብር አለ።+ 26  እኔም “እበትናቸዋለሁ፤መታሰቢያቸውም ከሰዎች ዘንድ እንዲጠፋ አደርጋለሁ” ባልኩ ነበር፤ 27  ነገር ግን የጠላትን ምላሽ ፈራሁ፤+ምክንያቱም ባላጋራዎቼ በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ።+ “ክንዳችን የበላይ ሆነ፤+ይህን ሁሉ ያደረገው ይሖዋ አይደለም” ሊሉ ይችላሉ። 28  እነሱ ማመዛዘን የጎደለው* ብሔር ናቸው፤በመካከላቸውም ማስተዋል የሚባል ነገር የለም።+ 29  ምነው ጥበበኛ በሆኑ ኖሮ!+ ይህን ሁሉ ያሰላስሉ ነበር።+ የሚደርስባቸውንም ያስቡ ነበር።+ 30  ዓለታቸው ካልሸጣቸውና+ይሖዋ ለምርኮ ካልዳረጋቸው በስተቀር አንድ ሰው 1,000 ሊያሳድድ፣ሁለት ሰው ደግሞ 10,000 ሊያባርር እንዴት ይችላል?+ 31  የእነሱ ዓለት እንደ እኛ ዓለት አይደለም፤+ጠላቶቻችንም እንኳ ይህን ተረድተዋል።+ 32  ወይናቸው ከሰዶም የወይን ተክልናከገሞራ የእርሻ ቦታ የተገኘ ነው።+ የወይን ፍሬያቸው መርዛማ የወይን ፍሬ ነው፤ዘለላቸው መራራ ነው።+ 33  የወይን ጠጃቸው የእባቦች መርዝ፣የጉበናም* ምሕረት የለሽ መርዝ ነው። 34  ይህ እኔ ጋ ያለ፣በግምጃ ቤቴ ውስጥ ማኅተም ታትሞበት የተቀመጠ አይደለም?+ 35  በቀልም ሆነ ቅጣት የእኔ ነው፤+አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ እግራቸው ይከዳቸዋል፤+የሚጠፉበት ቀን ቀርቧልና፤የሚጠብቃቸውም ነገር በፍጥነት ይመጣል።’ 36  ይሖዋ ሕዝቡን ይዳኛል፤+አገልጋዮቹ አቅም እንዳነሳቸው፣ረዳት የለሽና ደካማ የሆኑት ብቻ እንደቀሩ ሲያይለእነሱ ያዝንላቸዋል።*+ 37  ከዚያም እንዲህ ይላል፦ ‘አማልክታቸው የት አሉ?+መሸሸጊያ እንዲሆናቸው የተጠጉት ዓለትስ የት አለ? 38  የመሥዋዕቶቻቸውን ስብ* ይበላ፣የመጠጥ መባዎቻቸውንም የወይን ጠጅ ይጠጣ የነበረው የት አለ?+ እስቲ ተነስተው ይርዷችሁ። እስቲ መሸሸጊያ ስፍራ ይሁኑላችሁ። 39  እንግዲህ እኔ እሱ እንደሆንኩ እዩ፤+ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት የሉም።+ እኔ እገድላለሁ፤ እኔ ሕያው አደርጋለሁ።+ እኔ አቆስላለሁ፤+ እኔው እፈውሳለሁ፤+ከእጄም ማዳን የሚችል የለም።+ 40  እጄን ወደ ሰማይ አንስቼ፣“በዘላለማዊ ሕያውነቴ” ብዬ እምላለሁ፤+ 41  የሚያብረቀርቅ ሰይፌን ከሳልኩናእጄን ለፍርድ ካዘጋጀሁ፣+ተቃዋሚዎቼን እበቀላለሁ፤+የሚጠሉኝንም እቀጣለሁ። 42  በታረዱና በተማረኩ ሰዎች ደም፣በጠላት መሪዎች ራስ፣ቀስቶቼን በደም አሰክራለሁ፤ሰይፌም ሥጋ ይበላል።’ 43  እናንተ ብሔራት ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ፤+እሱ የአገልጋዮቹን ደም ይመልሳልና፤+ተቃዋሚዎቹንም ይበቀላል፤+ለሕዝቡም ምድር ያስተሰርይለታል።”* 44  ሙሴም ከነዌ ልጅ ከሆሺአ*+ ጋር መጥቶ የዚህን መዝሙር ቃላት በሙሉ ሕዝቡ እየሰማ ተናገረ።+ 45  ሙሴ እነዚህን ቃላት በሙሉ ለመላው እስራኤል ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ 46  እንዲህ አላቸው፦ “የዚህን ሕግ ቃላት በሙሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዟቸው+ እኔ በዛሬው ዕለት እናንተን ለማስጠንቀቅ የምነግራችሁን ቃል ሁሉ ልብ በሉ።+ 47  ይህ ቃል ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃል አይደለም፤+ ይህ ቃል ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ላይ ዕድሜያችሁን ሊያረዝምላችሁ ይችላል።” 48  ይሖዋ በዚያው ዕለት ሙሴን እንዲህ አለው፦ 49  “በኢያሪኮ ትይዩ በሞዓብ ምድር ወደሚገኘው ወደዚህ የአባሪም ተራራ+ ይኸውም ወደ ነቦ ተራራ+ ወጥተህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርጌ የምሰጣትን የከነአንን ምድር ተመልከት።+ 50  ወንድምህ አሮን በሆር ተራራ ላይ ሞቶ+ ወደ ወገኖቹ እንደተሰበሰበ* ሁሉ አንተም በምትወጣበት በዚህ ተራራ ላይ ትሞታለህ፤ ወደ ወገኖችህም ትሰበሰባለህ፤ 51  ምክንያቱም ሁለታችሁም በጺን ምድረ በዳ በሚገኘው በቃዴስ፣ በመሪባ ውኃዎች+ አጠገብ በእስራኤላውያን መካከል ለእኔ ታማኝ ሆናችሁ አልተገኛችሁም፤ እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት እኔን አልቀደሳችሁኝም።+ 52  ምድሪቱን ከሩቅ ታያታለህ፤ ሆኖም ለእስራኤል ሕዝብ ወደምሰጣት ምድር አትገባም።”+

የግርጌ ማስታወሻ

“የሰው ዘርን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ያዕቆብን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ከበጉ ስብ።”
ቃል በቃል “ከስንዴው ኩላሊት ስብ።”
ወይም “ጭማቂ።”
“ቅን የሆነው” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ለእስራኤል የተሰጠ የማዕረግ ስም ነው።
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“ምክር የማይሰማ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
በእስያና በአፍሪካ የሚገኝ እጅግ መርዘኛ የሆነ እባብ፤ ኮብራ።
ወይም “በእነሱ ይጸጸታል።”
ወይም “ምርጥ የሆኑ መሥዋዕቶቻቸውን።”
ወይም “የሕዝቡንም ምድር ያነጻል።”
የኢያሱ ዋነኛው ስም ነው። ሆሺአ የሆሻያህ አጭር አጠራር ሲሆን “ያህ ያዳነው፤ ያህ አድኗል” የሚል ትርጉም አለው።
ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።