ዘዳግም 33:1-29
33 የእውነተኛው አምላክ ሰው ሙሴ ከመሞቱ በፊት እስራኤላውያንን የባረካቸው በረከት ይህ ነው።+
2 እንዲህ አለ፦
“ይሖዋ ከሲና መጣ፤+ከሴይርም ሆኖ አበራባቸው።
ከፋራን ተራራማ አካባቢዎችም በክብር አበራ፤+ከእሱም ጋር አእላፋት ቅዱሳን* ነበሩ፤+በቀኙም ተዋጊዎቹ አሉ።+
3 እሱ ሕዝቡን ይወዳል፤+ቅዱስ የሆነው ሕዝብ ሁሉ እጅህ ውስጥ ነው።+
እነሱም እግርህ ሥር ተቀምጠዋል፤+ቃልህንም ይሰማሉ።+
4 (ሙሴ ትእዛዝን ይኸውም ሕግን ሰጠን፤+ይህም ለያዕቆብ ጉባኤ እንደ ርስት ነው።)+
5 የሕዝቡ መሪዎች ከመላው የእስራኤል ነገድ ጋር+አንድ ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ፣+አምላክ በየሹሩን*+ ላይ ንጉሥ ሆነ።
6 ሮቤል በሕይወት ይኑር፣ አይሙት፤+የወገኖቹም ቁጥር አይቀንስ።”+
7 ይሁዳንም እንዲህ ሲል ባረከው፦+
“ይሖዋ ሆይ፣ የይሁዳን ድምፅ ስማ፤+ወደ ሕዝቦቹም መልሰህ አምጣው።
እጆቹ የእሱ ለሆነው ይከላከላሉ፤*አንተም ጠላቶቹን እንዲዋጋ እርዳው።”+
8 ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፦+
“የአንተ* ቱሚምና ኡሪም+ ለአንተ ታማኝ ለሆነ፣+በማሳህ ለፈተንከው ሰው ይሆናል፤+
በመሪባ ውኃዎች አጠገብ ተጣላኸው፤+
9 ሰውየው አባቱንና እናቱን በተመለከተ ‘ስለ እነሱ ግድ የለኝም’ አለ።
ሌላው ቀርቶ ወንድሞቹን እንኳ አልተቀበለም፤+የገዛ ልጆቹንም ችላ አለ።
ቃልህን ታዘዋልና፤ቃል ኪዳንህንም ጠብቀዋል።+
10 ለያዕቆብ ድንጋጌህን፣+ለእስራኤልም ሕግህን ያስተምሩ።+
ደስ የሚያሰኝ መዓዛ እንዲሸትህ ዕጣን ያቅርቡልህ፤+በመሠዊያህም ላይ ሙሉ በሙሉ የሚቀርብ መባ ይሠዉልህ።+
11 ይሖዋ ሆይ፣ ጉልበቱን ባርክለት፤በእጆቹም ሥራ ደስ ይበልህ።
እሱን የሚጠሉት ዳግመኛ እንዳያንሰራሩበእሱ ላይ የሚነሱትን እግራቸውን* አድቅቅ።”
12 ስለ ቢንያም እንዲህ አለ፦+
“ይሖዋ የወደደው ያለስጋት አብሮት ይኑር፤ቀኑን ሙሉ ይከልለዋልና፤በትከሻዎቹም መካከል ይኖራል።”
13 ስለ ዮሴፍ እንዲህ አለ፦+
“ይሖዋ ከሰማይ በሚወርዱ ምርጥ ነገሮች፣በጤዛና ከታች በሚመነጩ ውኃዎች+ምድሩን ይባርክ፤+
14 እንዲሁም ፀሐይ በምታስገኛቸው ምርጥ ነገሮች፣በየወሩ በሚገኝ ምርጥ ፍሬ፣+
15 ጥንታዊ ከሆኑ ተራሮች* በሚገኙ ምርጥ ነገሮች፣+ጸንተው ከሚኖሩት ኮረብቶች በሚገኙ ምርጥ ነገሮች፣
16 ከምድር በሚገኙ ምርጥ ነገሮችና ምድርን በሞሉ ምርጥ ነገሮች፣+በቁጥቋጦው ውስጥ በተገለጠው በእሱ ሞገስ ይባርክ።+
እነዚህ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ፣ከወንድሞቹ መካከል ተነጥሎ በወጣው አናት ላይ ይውረዱ።+
17 ግርማው እንደ በኩር በሬ ነው፤ቀንዶቹም የዱር በሬ ቀንድ ናቸው።
በእነሱም ሰዎችን፣ሕዝቦችን ሁሉ እስከ ምድር ዳርቻ ይገፋል።*
እነሱ የኤፍሬም አሥር ሺዎች ናቸው፤+የምናሴም ሺዎች ናቸው።”
18 ስለ ዛብሎን እንዲህ አለ፦+
“ዛብሎን ሆይ፣ በመውጣትህ ደስ ይበልህ፤አንተም ይሳኮር፣ በድንኳኖችህ ውስጥ ደስ ይበልህ።+
19 ሰዎችን ወደ ተራራው ይጠራሉ።
በዚያም የጽድቅ መሥዋዕቶችን ያቀርባሉ።
ምክንያቱም በባሕሮች ውስጥ ካለው የተትረፈረፈ ሀብት፣በአሸዋም ውስጥ ተሰውሮ ከተከማቸው ነገር* ዝቀው ያወጣሉ።”
20 ስለ ጋድ እንዲህ አለ፦+
“የጋድን ድንበሮች የሚያሰፋ የተባረከ ነው።+
በዚያ እንደ አንበሳ ይተኛል፤ክንድን፣ አዎ አናትን ለመዘነጣጠል ተዘጋጅቶ ይጠብቃል።
21 የመጀመሪያውን መርጦ ለራሱ ይወስዳል፤+በዚያ የሕግ ሰጪው ድርሻ ተለይቶ ተቀምጧልና።+
የሕዝቡ መሪዎች አንድ ላይ ይሰበሰባሉ።
የይሖዋን ጽድቅና ድንጋጌዎች፣በእስራኤል ያስፈጽማል።”
22 ስለ ዳን እንዲህ አለ፦+
“ዳን የአንበሳ ደቦል ነው።+
ከባሳን ዘሎ ይወጣል።”+
23 ስለ ንፍታሌም እንዲህ አለ፦+
“ንፍታሌም በይሖዋ ሞገስ ረክቷል፤በእሱም በረከት ተሞልቷል።
ምዕራቡንና ደቡቡን ውረስ።”
24 ስለ አሴር እንዲህ አለ፦+
“አሴር በልጆች የተባረከ ነው።
በወንድሞቹ ፊት ሞገስ ያግኝ፤እግሩንም ዘይት ውስጥ ይንከር።*
25 የበርህ መቀርቀሪያ ብረትና መዳብ ናቸው፤+በዘመንህ ሁሉ ያለስጋት ትኖራለህ።*
26 አንተን ለመርዳት በሰማይ ውስጥ የሚጋልብ፣በግርማው በደመና ላይ የሚገሰግስ፣+እንደ እውነተኛው የየሹሩን+ አምላክ ያለ ማንም የለም።+
27 አምላክ ከጥንት ጀምሮ መሸሸጊያ ነው፤+ዘላለማዊ ክንዶቹ ከበታችህ ናቸው።+
ጠላትን ከፊትህ ያባርራል፤+እንዲሁም ‘አጥፋቸው!’ ይላል።+
28 እህልና አዲስ የወይን ጠጅ ባለበት ምድር፣+ሰማያቱ ጠል በሚያንጠባጥቡበት+እስራኤል ያለስጋት ይቀመጣል፤የያዕቆብም ምንጭ የተገለለ ይሆናል።
29 እስራኤል ሆይ፣ ደስተኛ ነህ!+
የይሖዋን ማዳን ያየ፣+እንደ አንተ ያለ ሕዝብ ማን አለ?+እሱ የሚከልል ጋሻህና+ታላቅ ሰይፍህ ነው፤
ጠላቶችህ በፊትህ ይንቀጠቀጣሉ፤+አንተም በጀርባቸው* ላይ ትራመዳለህ።”
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ቅዱሳን።”
^ “ቅን የሆነው” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ለእስራኤል የተሰጠ የማዕረግ ስም ነው።
^ ወይም “ይታገላሉ።”
^ እዚህ ጥቅስ ላይ ያሉት “የአንተ” እና “ለአንተ” የሚሉት ቃላት አምላክን ያመለክታሉ።
^ ወይም “ወገባቸውን።”
^ “ከምሥራቅ ተራሮች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ይወጋል።”
^ ወይም “የከበረ ሀብት።”
^ ወይም “ይታጠብ።”
^ ቃል በቃል “ብርታትህም እንደ ዘመንህ ይሆናል።”
^ “በከፍታ ቦታዎቻቸው” ማለትም ሊሆን ይችላል።