ዘዳግም 34:1-12

  • ይሖዋ ለሙሴ ምድሪቱን አሳየው (1-4)

  • ሙሴ ሞተ (5-12)

34  ከዚያም ሙሴ ከሞዓብ በረሃማ ሜዳ ተነስቶ ወደ ነቦ ተራራ+ ይኸውም በኢያሪኮ+ ትይዩ ወደሚገኘው ወደ ጲስጋ አናት+ ወጣ። ይሖዋም ምድሪቱን በሙሉ አሳየው፤ ይኸውም ከጊልያድ እስከ ዳን፣+  ንፍታሌምን በሙሉ፣ የኤፍሬምንና የምናሴን ምድር፣ በስተ ምዕራብ በኩል እስካለው ባሕር* ድረስ ያለውን የይሁዳን ምድር በሙሉ፣+  ኔጌብን፣+ የዮርዳኖስን አውራጃ+ እንዲሁም የዘንባባ ዛፍ ከተማ በሆነችው በኢያሪኮ ካለው ሸለቋማ ሜዳ አንስቶ እስከ ዞአር+ ድረስ አሳየው።  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ‘ለዘርህ እሰጣታለሁ’+ በማለት የማልኩላቸው ምድር ይህች ናት። በዓይንህ እንድታያት አድርጌሃለሁ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትሻገርም።”+  የይሖዋ አገልጋይ ሙሴም ልክ ይሖዋ እንደተናገረው በዚያው በሞዓብ ምድር ሞተ።+  እሱም ከቤትጰኦር ትይዩ በሞዓብ ምድር በሚገኘው ሸለቆ ቀበረው፤ እስከ ዛሬም ድረስ መቃብሩ የት እንደሚገኝ የሚያውቅ የለም።+  ሙሴ በሞተ ጊዜ ዕድሜው 120 ዓመት ነበር።+ ዓይኖቹ አልፈዘዙም፤ ጉልበቱም አልደከመም ነበር።  እስራኤላውያንም በሞዓብ በረሃማ ሜዳ ለሙሴ 30 ቀን አለቀሱለት።+ በመጨረሻም ለሙሴ የሚለቀስበትና የሚታዘንበት ጊዜ አበቃ።  የነዌ ልጅ ኢያሱ ሙሴ እጁን ስለጫነበት+ የጥበብ መንፈስ ተሞልቶ ነበር፤ እስራኤላውያንም እሱን ይሰሙት ጀመር፤ እንዲሁም ልክ ይሖዋ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።+ 10  ሆኖም ይሖዋ ፊት ለፊት እንዳወቀው+ እንደ ሙሴ ያለ ሌላ ነቢይ እስካሁን በእስራኤል ተነስቶ አያውቅም።+ 11  ይሖዋ በግብፅ ምድር በፈርዖን፣ በአገልጋዮቹ ሁሉና በምድሩ ሁሉ ፊት እንዲፈጽም የላከውን ምልክቶችና ተአምራት በሙሉ ፈጸመ፤+ 12  ከዚህም በተጨማሪ ሙሴ በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት በኃያል ክንድ ታላቅና አስፈሪ ድርጊት ፈጸመ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ታላቁን ባሕር፣ ሜድትራንያንን ያመለክታል።