ዘዳግም 5:1-33

  • ይሖዋ በኮሬብ ከእስራኤላውያን ጋር የገባው ቃል ኪዳን (1-5)

  • አሥርቱ ትእዛዛት በድጋሚ ተዘረዘሩ (6-22)

  • በሲና ተራራ አጠገብ ሕዝቡ ፍርሃት አደረበት (23-33)

5  ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን በሙሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ እስራኤላውያን፣ በዛሬው ዕለት የምነግራችሁን ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች ስሙ፤ እወቋቸው፤ በጥንቃቄም ፈጽሟቸው።  አምላካችን ይሖዋ በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል።+  ይሖዋ ይህን ቃል ኪዳን የገባው ከአባቶቻችን ጋር ሳይሆን ዛሬ በሕይወት እዚህ ካለነው ከእኛ ከሁላችን ጋር ነው።  ይሖዋ በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ከእናንተ ጋር ፊት ለፊት ተነጋገረ።+  በዚያ ወቅት እኔ የይሖዋን ቃል ለእናንተ ለመንገር በይሖዋና በእናንተ መካከል ቆሜ ነበር፤+ ምክንያቱም እናንተ ከእሳቱ የተነሳ ፈርታችሁ ወደ ተራራው አልወጣችሁም።+ እሱም እንዲህ አለ፦  “‘ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ።+  ከእኔ በቀር* ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።+  “‘በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸ ቅርጽም+ ሆነ የተሠራ ምስል ለራስህ አታብጅ።  ለእነሱ አትስገድ፤ አታገልግላቸውም፤+ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግና+ በሚጠሉኝ ሁሉ ላይ በአባቶች ስህተት የተነሳ በልጆቻቸው እንዲሁም በሦስተኛና በአራተኛ ትውልዶቻቸው ላይ ቅጣት የማመጣ አምላክ ነኝ፤+ 10  ሆኖም ለሚወዱኝና ትእዛዛቴን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ታማኝ ፍቅር* የማሳይ አምላክ ነኝ። 11  “‘የአምላክህን የይሖዋን ስም በከንቱ አታንሳ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ስሙን በከንቱ የሚያነሳውን ሳይቀጣ አይተወውም።+ 12  “‘አምላክህ ይሖዋ ባዘዘህ መሠረት ቅዱስ አድርገህ ትጠብቀው ዘንድ የሰንበትን ቀን አክብር።+ 13  ሥራህን ሁሉ በስድስት ቀን ትሠራለህ፤+ 14  ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለይሖዋ ሰንበት ነው።+ በዚህ ቀን አንተም ሆንክ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህም ሆነ ሴት ባሪያህ፣ በሬህም ሆነ አህያህ ወይም ማንኛውም የቤት እንስሳህ አሊያም በከተሞችህ* ውስጥ ያለ የባዕድ አገር ሰው+ ምንም ሥራ አትሥሩ፤+ ይህም አንተ እንደምታርፈው ወንድ ባሪያህና ሴት ባሪያህ እንዲያርፉ ነው።+ 15  አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደነበርክና አምላክህ ይሖዋ በብርቱ እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ እንዳወጣህ አስታውስ።+ አምላክህ ይሖዋ የሰንበትን ቀን እንድታከብር ያዘዘህ ለዚህ ነው። 16  “‘አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ+ አምላክህ ይሖዋ ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር።+ 17  “‘አትግደል።+ 18  “‘አታመንዝር።+ 19  “‘አትስረቅ።+ 20  “‘በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመሥክር።+ 21  “‘የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ።+ የባልንጀራህን ቤት፣ እርሻውን፣ ወንድ ባሪያውን፣ ሴት ባሪያውን፣ በሬውን፣ አህያውን ወይም የባልንጀራህ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ።’+ 22  “ይሖዋ በተራራው ላይ በእሳቱ መካከል በደመናውና በድቅድቅ ጨለማው+ ውስጥ ሆኖ እነዚህን ትእዛዛት* ከፍ ባለ ድምፅ ለመላው ጉባኤያችሁ ተናገረ፤ ከእነዚህም ሌላ ምንም አልጨመረም፤ ከዚያም እነዚህን በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠኝ።+ 23  “ይሁን እንጂ ተራራው በእሳት እየነደደ ሳለ+ ከጨለማው ውስጥ ድምፅ ሲወጣ ስትሰሙ የነገድ መሪዎቻችሁና ሽማግሌዎቹ በሙሉ ወደ እኔ መጡ። 24  ከዚያም እንዲህ አላችሁ፦ ‘ይኸው አምላካችን ይሖዋ ክብሩንና ታላቅነቱን አሳይቶናል፤ ድምፁንም ከእሳቱ ውስጥ ሰምተናል።+ አምላክ ከሰው ጋር መነጋገር እንደሚችልና ያም ሰው በሕይወት ሊኖር እንደሚችል በዛሬው ቀን አይተናል።+ 25  ታዲያ አሁን ለምን እንሙት? ምክንያቱም ይህ ታላቅ እሳት ሊበላን ይችላል። የአምላካችንን የይሖዋን ድምፅ መስማት ከቀጠልን እንደምንሞት የተረጋገጠ ነው። 26  ለመሆኑ ከሥጋ* ሁሉ መካከል ልክ እኛ እንደሰማነው ሕያው የሆነው አምላክ በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር ሰምቶ በሕይወት የኖረ ማን አለ? 27  አንተው ራስህ ቀርበህ አምላካችን ይሖዋ የሚናገረውን ሁሉ ስማ፤ ከዚያም አምላካችን ይሖዋ የነገረህን ሁሉ ትነግረናለህ፤ እኛም እንሰማለን፤ ደግሞም የተባልነውን እናደርጋለን።’+ 28  “ከዚያም ይሖዋ ያላችሁኝን ነገር ሰማ፤ ይሖዋም እንዲህ አለኝ፦ ‘ይህ ሕዝብ ምን እንዳለህ ሰምቻለሁ። የተናገሩት ነገር ሁሉ መልካም ነው።+ 29  ምንጊዜም እኔን የሚፈራና+ ትእዛዛቴን ሁሉ የሚጠብቅ ልብ+ ቢኖራቸው ምናለ፤ እንዲህ ቢሆን ለእነሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም ይሆንላቸው ነበር!+ 30  ሂድና “ወደየድንኳናችሁ ተመለሱ” በላቸው። 31  አንተ ግን እዚሁ እኔ ጋ ቆይ፤ እኔም ርስት አድርገው እንዲወርሷት በምሰጣቸው ምድር ውስጥ ይጠብቋቸው ዘንድ የምታስተምራቸውን ትእዛዛት፣ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች በሙሉ እነግርሃለሁ።’ 32  እንግዲህ አምላካችሁ ይሖዋ ያዘዛችሁን በጥንቃቄ ፈጽሙ።+ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አትበሉ።+ 33  ርስት አድርጋችሁ በምትወርሷት ምድር በሕይወት እንድትኖሩ፣ እንድትበለጽጉና ዕድሜያችሁ እንዲረዝም+ አምላካችሁ ይሖዋ ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “እኔን የሚቀናቀኑ።”
ወይም “ፍቅራዊ ደግነት።”
ቃል በቃል “በደጅህ።”
ቃል በቃል “ቃላት።”
ወይም “ከሰው ዘር።”