ዘዳግም 6:1-25

  • ይሖዋን በሙሉ ልብ ውደድ (1-9)

    • “እስራኤል ሆይ ስማ” (4)

    • ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል (6, 7)

  • አምላክህን ይሖዋን አትርሳ (10-15)

  • ይሖዋን አትፈታተን (16-19)

  • ለቀጣዩ ትውልድ ተናገር (20-25)

6  “አምላካችሁ ይሖዋ ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ውስጥ ትጠብቋቸው ዘንድ እንዳስተምራችሁ የሰጠኝ ትእዛዛት፣ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች እነዚህ ናቸው፤  ይህም አንተ፣ ልጅህና የልጅ ልጅህ+ ዕድሜያችሁ ይረዝም ዘንድ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ አምላካችሁን ይሖዋን እንድትፈሩ እንዲሁም እኔ የማዛችሁን የእሱን ደንቦችና ትእዛዛት ሁሉ እንድትጠብቁ ነው።+  እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ የአባቶችህ አምላክ ይሖዋ በገባልህ ቃል መሠረት ወተትና ማር በምታፈሰው ምድር እንድትበለጽግና እጅግ እንድትበዛ እነዚህን በጥንቃቄ ጠብቅ።  “እስራኤል ሆይ ስማ፣ አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው።+  አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና*+ በሙሉ ኃይልህ ውደድ።+  እኔ ዛሬ የማዝህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ፤  በልጆችህም ውስጥ ቅረጻቸው፤*+ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድ ላይ ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሳ ስለ እነሱ ተናገር።+  በእጅህም ላይ እንደ ማስታወሻ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ* እንደታሰረ ነገር ይሁኑ።+  በቤትህ መቃኖችና በግቢህ በሮች ላይ ጻፋቸው። 10  “አምላክህ ይሖዋ ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደማለላቸው ምድር+ ሲያስገባህና በዚያም አንተ ያልገነባሃቸውን ታላላቅና ያማሩ ከተሞች፣+ 11  አንተ ባልደከምክባቸው የተለያዩ መልካም ነገሮች የተሞሉ ቤቶችን፣ አንተ ያልቦረቦርካቸውን የውኃ ማጠራቀሚያዎች እንዲሁም አንተ ያልተከልካቸውን የወይን ተክሎችና የወይራ ዛፎች ስታገኝ፣ በልተህም ስትጠግብ+ 12  ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን ይሖዋን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ።+ 13  ይሖዋ አምላክህን ፍራ፤+ እሱን አገልግል፤+ በስሙም ማል።+ 14  ሌሎች አማልክትን ይኸውም በዙሪያችሁ ያሉ ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን የትኞቹንም አማልክት አትከተሉ፤+ 15  ምክንያቱም በመካከልህ ያለው አምላክህ ይሖዋ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው።+ አለዚያ የአምላክህ የይሖዋ ቁጣ በላይህ ይነድዳል፤+ ከምድርም ገጽ ጠራርጎ ያጠፋሃል።+ 16  “በማሳህ እንደተፈታተናችሁት+ አምላካችሁን ይሖዋን አትፈታተኑት።+ 17  አምላካችሁ ይሖዋ እንድትጠብቋቸው ያዘዛችሁን ትእዛዛት እንዲሁም ማሳሰቢያዎቹንና ሥርዓቶቹን በጥንቃቄ ጠብቁ። 18  እንድትበለጽግና ይሖዋ ለአባቶችህ የማለላቸውን መልካሚቱን ምድር ገብተህ እንድትወርስ በይሖዋ ፊት ትክክልና መልካም የሆነውን አድርግ፤+ 19  ይሖዋ በገባው ቃል መሠረት ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ አባረህ አስወጣ።+ 20  “ወደፊት ልጅህ ‘አምላካችን ይሖዋ የሰጣችሁ ማሳሰቢያዎች፣ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች ትርጉም ምንድን ነው?’ ብሎ ሲጠይቅህ 21  እንዲህ ትለዋለህ፦ ‘እኛ በግብፅ የፈርዖን ባሪያዎች ሆነን ነበር፤ ይሖዋ ግን በብርቱ ክንድ ከግብፅ አወጣን። 22  ይሖዋም በግብፅ፣ በፈርዖንና በቤተሰቡ ሁሉ ላይ+ ታላላቅና አጥፊ የሆኑ ድንቅ ምልክቶችንና ተአምራትን+ ዓይናችን እያየ ፈጸመ። 23  እኛንም ለአባቶቻችን የማለላቸውን ምድር ሊሰጠን ከዚያ አውጥቶ ወደዚህ አመጣን።+ 24  ከዚያም ይሖዋ ምንጊዜም መልካም ይሆንልን ዘንድ እነዚህን ሥርዓቶች ሁሉ እንድንፈጽምና አምላካችንን ይሖዋን እንድንፈራ አዘዘን፤+ ይህም ዛሬ እንደሆነው ሁሉ በሕይወት እንድንኖር ነው።+ 25  አምላካችንን ይሖዋን በመታዘዝ* ልክ እሱ በሰጠን መመሪያ መሠረት እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ በጥንቃቄ ብንፈጽም ለእኛ ጽድቅ ይሆንልናል።’+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ለልጆችህ ደጋግመህ ንገራቸው፤ በልጆችህ ላይ አትማቸው።”
ቃል በቃል “በዓይኖችህም መካከል።”
ቃል በቃል “በአምላካችን በይሖዋ ፊት።”