ዘዳግም 9:1-29

  • እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር የገቡት በጽድቃቸው አይደለም (1-6)

  • እስራኤላውያን ይሖዋን አራት ጊዜ አስቆጡት (7-29)

    • የወርቅ ጥጃ (7-14)

    • ሙሴ ያቀረበው ምልጃ (15-21, 25-29)

    • ይሖዋን ሦስት ጊዜ አስቆጡት (22)

9  “እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ እንግዲህ ዛሬ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ኃያል የሆኑ ብሔራትን+ እንዲሁም ታላላቅና እስከ ሰማያት የሚደርስ ቅጥር ያላቸውን ከተሞች+ በማስለቀቅ ወደ ምድሪቱ ለመግባት ዮርዳኖስን ልትሻገር ነው፤+  ‘የኤናቅን ልጆች ማን ሊቋቋማቸው ይችላል?’ ሲባልላቸው የሰማኸውን፣ አንተ ራስህ የምታውቃቸውን ብርቱና ቁመተ ረጃጅም ሕዝብ የሆኑትን የኤናቅን ልጆችም+ ልታስለቅቅ ነው።  ስለሆነም አምላክህ ይሖዋ ዛሬ ከአንተ ቀድሞ እንደሚሻገር እወቅ።+ እሱ የሚባላ እሳት ነው፤+ ደግሞም ያጠፋቸዋል። ልክ ይሖዋ ቃል በገባልህ መሠረት በፍጥነት ታባርራቸውና* ታጠፋቸው ዘንድ ዓይንህ እያየ ድል ያደርጋቸዋል።+  “አምላክህ ይሖዋ እነሱን ከፊትህ በሚያባርራቸው ጊዜ በልብህ ‘ይሖዋ ይህችን ምድር እንድወርስ ወደዚህ ያመጣኝ እኮ በራሴ ጽድቅ ነው’ አትበል፤+ ይሖዋ እነዚህን ብሔራት ከፊትህ የሚያባርራቸው በራሳቸው ክፋት የተነሳ ነው።+  የእነሱን ምድር ገብተህ የምትወርሰው ከጽድቅህ ወይም ከልብህ ቅንነት የተነሳ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክህ ይሖዋ እነዚህን ብሔራት ከፊትህ የሚያባርራቸው ከራሳቸው ክፋት የተነሳ ነው፤+ እንዲሁም ይሖዋ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣+ ለይስሐቅና+ ለያዕቆብ+ የማለላቸውን ቃል ለመፈጸም ሲል ነው።  ስለዚህ አምላክህ ይሖዋ ይህችን መልካም ምድር እንድትወርሳት የሚሰጥህ ከጽድቅህ የተነሳ እንዳልሆነ እወቅ፤ ምክንያቱም አንተ ግትር* ሕዝብ ነህ።+  “በምድረ በዳ አምላክህን ይሖዋን እንዴት እንዳስቆጣኸው+ አስታውስ፤ ፈጽሞም አትርሳ። ከግብፅ ምድር ከወጣችሁበት ጊዜ አንስቶ እዚህ ቦታ እስክትደርሱ ድረስ በይሖዋ ላይ ዓምፃችኋል።+  በኮሬብም እንኳ ይሖዋን አስቆጥታችሁት ነበር፤ ይሖዋም በእናንተ ላይ እጅግ ከመቆጣቱ የተነሳ እናንተን ለማጥፋት አስቦ ነበር።+  እኔም የድንጋይ ጽላቶቹን+ ይኸውም ይሖዋ ከእናንተ ጋር የገባው ቃል ኪዳን የተጻፈባቸውን ጽላቶች+ ለመቀበል ወደ ተራራው በወጣሁ ጊዜ እህል ሳልበላና ውኃ ሳልጠጣ በተራራው ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆይቼ ነበር።+ 10  ከዚያም ይሖዋ በአምላክ ጣት የተጻፈባቸውን ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች ሰጠኝ፤ በእነሱም ላይ ይሖዋ እዚያ ተሰብስባችሁ በነበረበት ቀን በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የነገራችሁ ነገር ሁሉ ተጽፎባቸው ነበር።+ 11  ከ40 ቀንና ከ40 ሌሊት በኋላ ይሖዋ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች ይኸውም የቃል ኪዳኑን ጽላቶች ሰጠኝ፤ 12  ይሖዋም እንዲህ አለኝ፦ ‘ተነስ፤ ቶሎ ብለህ ውረድ፤ ምክንያቱም ከግብፅ ያወጣኸው ሕዝብህ የጥፋት ጎዳና እየተከተለ ነው።+ እንዲከተሉት ካዘዝኳቸው መንገድ ፈጥነው ዞር ብለዋል። ከብረት የተሠራ ምስልም* ለራሳቸው አበጅተዋል።’+ 13  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘ይህን ሕዝብ አይቼዋለሁ፤ በእርግጥም ግትር* ሕዝብ ነው።+ 14  አጠፋቸውና ስማቸውን ከሰማይ በታች እደመስሰው ዘንድ ተወኝ፤ አንተን ግን ከእነሱ ይልቅ ኃያልና ብዙ ሕዝብ ያቀፈ ብሔር አደርግሃለሁ።’+ 15  “እኔም ተራራው በእሳት እየተቀጣጠለ+ እያለ ተመልሼ ከተራራው ወረድኩ፤ ሁለቱን የቃል ኪዳን ጽላቶችም በእጆቼ ይዤ ነበር።+ 16  ከዚያም ስመለከት በአምላካችሁ በይሖዋ ላይ ኃጢአት እንደፈጸማችሁ አየሁ! ለራሳችሁም የብረት* ጥጃ ሠርታችሁ ነበር። ይሖዋ እንድትከተሉት ካዘዛችሁ መንገድ ፈጥናችሁ ዞር ብላችሁ ነበር።+ 17  ስለዚህ ሁለቱን ጽላቶች አሽቀንጥሬ በመወርወር ዓይናችሁ እያየ ሰባበርኳቸው።+ 18  ከዚያም እንደ መጀመሪያው ጊዜ ሁሉ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት በይሖዋ ፊት ተደፋሁ። በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር በማድረግና እሱን በማስቆጣት በፈጸማችሁት ኃጢአት ሁሉ የተነሳ እህል አልቀመስኩም፤ ውኃም አልጠጣሁም።+ 19  ምክንያቱም ይሖዋ በእናንተ ላይ እጅግ ከመቆጣቱ የተነሳ ሊያጠፋችሁ ስለተዘጋጀ+ ፈርቼ ነበር። ይሁንና ይሖዋ በዚያን ጊዜም ሰማኝ።+ 20  “ይሖዋ አሮንን ለማጥፋት እስኪያስብ ድረስ በእሱ ላይ ተቆጥቶ ነበር፤+ ሆኖም በዚያን ጊዜ ስለ አሮንም ምልጃ አቀረብኩ። 21  ከዚያም የኃጢአት ሥራችሁን ይኸውም ጥጃውን+ ወስጄ በእሳት አቃጠልኩት፤ ሰባበርኩት፤ እንደ አቧራ ብናኝ እስኪሆንም ድረስ ፈጨሁት፤ ብናኙንም ከተራራው በሚወርደው ጅረት ውስጥ በተንኩት።+ 22  “በተጨማሪም በታበራ፣+ በማሳህ+ እና በቂብሮትሃታባ+ ይሖዋን አስቆጣችሁት። 23  ይሖዋ ከቃዴስበርኔ+ በላካችሁና ‘ውጡ፤ የምሰጣችሁንም ምድር ውረሱ!’ ባላችሁ ጊዜ በአምላካችሁ በይሖዋ ትእዛዝ ላይ በድጋሚ ዓመፃችሁ፤+ በእሱ አልታመናችሁም፤+ እንዲሁም አልታዘዛችሁትም። 24  እኔ እናንተን ካወቅኩበት ጊዜ አንስቶ በይሖዋ ላይ እንዳመፃችሁ ነው። 25  “በመሆኑም 40 ቀንና 40 ሌሊት በይሖዋ ፊት ተደፋሁ፤+ እንዲህ በፊቱ የተደፋሁት፣ ይሖዋ እንደሚያጠፋችሁ ተናግሮ ስለነበር ነው። 26  ከዚያም እንዲህ በማለት ይሖዋን መማጸን ጀመርኩ፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ሕዝብህን አታጥፋ። እነሱ በታላቅነትህ የታደግካቸውና በኃያል ክንድህ ከግብፅ ያወጣሃቸው+ የግል ንብረቶችህ*+ ናቸው። 27  አገልጋዮችህን አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ።+ የዚህን ሕዝብ ግትርነት፣ ክፋትና ኃጢአት አትመልከት።+ 28  አለዚያ እኛን ባወጣህበት ምድር የሚገኙ ሰዎች “ይሖዋ ቃል ወደገባላቸው ምድር ሊያስገባቸው ስላልቻለና ስለጠላቸው በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው” ሊሉ ይችላሉ።+ 29  እነሱ በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋ ክንድህ ያወጣሃቸው+ ሕዝቦችህና የግል ንብረቶችህ*+ ናቸው።’

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ታስለቅቃቸውና።”
ቃል በቃል “አንገተ ደንዳና።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልትም።”
ቃል በቃል “አንገተ ደንዳና።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ።”
ወይም “ውርሻህ።”
ወይም “ውርሻህ።”