ዘፀአት 11:1-10

  • አሥረኛው መቅሰፍት እንደሚመጣ ተነገረ (1-10)

    • እስራኤላውያን ከግብፃውያን ላይ ስጦታ እንዲጠይቁ ተነገራቸው (2)

11  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በፈርዖንና በግብፅ ላይ አንድ ተጨማሪ መቅሰፍት አመጣለሁ። ከዚያ በኋላ ከዚህ እንድትሄዱ ይለቃችኋል።+ ደግሞም በሚለቃችሁ ጊዜ አንዳችሁንም ሳያስቀር ከዚህ ያባርራችኋል።+  እንግዲህ አሁን ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ ሁሉ ከየጎረቤቶቻቸው የብርና የወርቅ ዕቃዎችን እንዲጠይቁ ለሕዝቡ ንገር።”+  ይሖዋም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት ሞገስ ሰጣቸው። ሙሴ ራሱም ቢሆን በፈርዖን አገልጋዮችና በሕዝቡ ፊት በግብፅ ምድር እጅግ የተከበረ ሰው ሆኖ ነበር።  ሙሴም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኩለ ሌሊት ገደማ በግብፅ መሃል እወጣለሁ፤+  በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኩር ልጅ አንስቶ የወፍጮ መጅ እስከምትገፋው ባሪያ የበኩር ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር ያለ በኩር ሁሉ ይሞታል፤+ የእንስሳም በኩር ሁሉ ይሞታል።+  በመላው የግብፅ ምድርም ከዚያ በፊት በጭራሽ ሆኖ የማያውቅ ከዚያ በኋላም ፈጽሞ ዳግመኛ የማይከሰት ታላቅ ዋይታ ይሆናል።+  ሆኖም ይሖዋ በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት ማድረግ እንደሚችል እንድታውቁ በእስራኤላውያን ላይ፣ በሰዎቹም ሆነ በእንስሶቻቸው ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽም።’*+  አገልጋዮችህም ሁሉ ወደ እኔ ወርደው ‘አንተም ሆንክ አንተን የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ ከዚህ ሂዱልን’ በማለት ይሰግዱልኛል።+ ከዚያ በኋላም እወጣለሁ።” ሙሴም ይህን ተናግሮ በታላቅ ቁጣ ከፈርዖን ፊት ወጣ።  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ተአምራቶቼ በግብፅ ምድር ላይ እንዲበዙ+ ፈርዖን እናንተን አይሰማችሁም” አለው።+ 10  ሙሴና አሮንም እነዚህን ሁሉ ተአምራት በፈርዖን ፊት ፈጸሙ፤+ ሆኖም ይሖዋ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ስለፈቀደ ፈርዖን እስራኤላውያን ከምድሩ እንዲሄዱ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ምላሱን አያሾልም።”