ዘፀአት 13:1-22

  • በኩር የሆነ ወንድ ሁሉ የይሖዋ ነው (1, 2)

  • እርሾ ያልገባበት ቂጣ በዓል (3-10)

  • በኩር የሆነ ወንድ ሁሉ ለአምላክ የተሰጠ ነው (11-16)

  • እስራኤላውያን ወደ ቀይ ባሕር እንዲያመሩ ታዘዙ (17-20)

  • የደመናና የእሳት ዓምድ (21, 22)

13  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦  “ከእስራኤል ሕዝብ መካከል በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ።* ከሰውም ሆነ ከእንስሳ መካከል በኩር የሆነው ወንድ ሁሉ* የእኔ ነው።”+  ከዚያም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ከግብፅ ከባርነት ቤት የወጣችሁበትን ይህን ቀን አስቡ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ በኃያል ክንድ ከዚህ አውጥቷችኋል።+ በመሆኑም እርሾ የገባበት ምንም ነገር መበላት የለበትም።  ይኸው በዛሬው ዕለት በአቢብ* ወር ከዚህ ለቃችሁ እየወጣችሁ ነው።+  ይሖዋ ለአንተ ይሰጥህ ዘንድ ለቀድሞ አባቶችህ ወደማለላቸው+ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር+ ይኸውም ወደ ከነአናውያን፣ ሂታውያን፣ አሞራውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን ምድር+ ሲያስገባህ አንተ ደግሞ በዚህ ወር ይህን በዓል ማክበር አለብህ።  ለሰባት ቀን ቂጣ ትበላለህ፤+ በሰባተኛውም ቀን ለይሖዋ በዓል ይከበራል።  በእነዚህ ሰባት ቀናት መበላት ያለበት እርሾ ያልገባበት ቂጣ ነው፤+ በአንተ ዘንድ እርሾ የገባበት ምንም ነገር መገኘት የለበትም፤+ በወሰንህም ውስጥ ሁሉ ምንም እርሾ መገኘት የለበትም።  በዚያ ቀን ለልጅህ ‘ይህን የማደርገው ከግብፅ በወጣሁበት ጊዜ ይሖዋ ባደረገልኝ ነገር የተነሳ ነው’ ብለህ ንገረው።+  የይሖዋ ሕግ በአፍህ ላይ እንዲሆን ይህ በዓል በእጅህ ላይ እንደታሰረ ምልክትና በግንባርህ* ላይ እንዳለ መታሰቢያ* ሆኖ ያገለግልሃል፤+ ምክንያቱም ይሖዋ በኃያል ክንድ ከግብፅ አውጥቶሃል። 10  አንተም ይህን ደንብ በየዓመቱ በተወሰነለት ጊዜ አክብረው።+ 11  “ይሖዋ ለአንተ ለመስጠት ለአንተም ሆነ ለቀድሞ አባቶችህ ወደማለላችሁ+ ወደ ከነአናውያን ምድር ሲያስገባህ 12  በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ* እንዲሁም የአንተ ከሆነው እንስሳ መካከል በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ ለይሖዋ መስጠት አለብህ። ወንዶቹ ሁሉ የይሖዋ ናቸው።+ 13  የእያንዳንዱን አህያ በኩር በበግ ዋጀው፤ የማትዋጀው ከሆነ ግን አንገቱን ስበረው። ከወንዶች ልጆችህ መካከል በኩር የሆነውን ሁሉ ልትዋጀው ይገባል።+ 14  “ምናልባት ወደፊት ልጅህ ‘ይህን የምታደርገው ለምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ በኃያል ክንድ ከግብፅ ከባርነት ቤት አወጣን።+ 15  ፈርዖን እኛን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆን ግትር አቋም በያዘ ጊዜ+ ይሖዋ ከሰው በኩር አንስቶ እስከ እንስሳ በኩር ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ ገደለ።+ በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ* ለይሖዋ የምሠዋው እንዲሁም ከወንዶች ልጆቼ መካከል በኩር የሆነውን ሁሉ የምዋጀው ለዚህ ነው።’ 16  ይሖዋ በኃያል ክንድ ከግብፅ ስላወጣን ይህ በዓል በእጅህ ላይ እንዳለ ምልክትና በግንባርህ* ላይ እንደታሰረ ነገር ሆኖ ያገልግል።”+ 17  ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ አምላክ ምንም እንኳ አቋራጭ ቢሆንም ወደ ፍልስጤማውያን ምድር በሚወስደው መንገድ አልመራቸውም። ምክንያቱም “ሕዝቡ ጦርነት ቢያጋጥመው ሐሳቡን ለውጦ ወደ ግብፅ ሊመለስ ይችላል” በማለት አስቦ ነበር። 18  በመሆኑም አምላክ ሕዝቡ በቀይ ባሕር አቅራቢያ ባለው ምድረ በዳ በኩል ዞሮ እንዲሄድ አደረገ።+ እስራኤላውያንም ከግብፅ ምድር የወጡት የጦርነት አሰላለፍ ተከትለው ነበር። 19  በተጨማሪም ሙሴ የዮሴፍን አፅም ይዞ ነበር፤ ምክንያቱም ዮሴፍ እስራኤላውያንን “አምላክ ፊቱን ወደ እናንተ መመለሱ አይቀርም፤ በመሆኑም አፅሜን ከዚህ ይዛችሁ ውጡ” በማለት በጥብቅ አስምሏቸው ነበር።+ 20  እነሱም ከሱኮት ተነስተው በምድረ በዳው ዳርቻ ላይ በሚገኘው በኤታም ሰፈሩ። 21  ይሖዋ የሚሄዱበትን መንገድ ይመራቸው ዘንድ ቀን ቀን በደመና ዓምድ ውስጥ ሆኖ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር፤+ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ብርሃን እንዲያገኙ ለማድረግ በእሳት ዓምድ ውስጥ ሆኖ ይመራቸው ነበር፤+ በመሆኑም ቀንም ሆነ ሌሊት ይጓዙ ነበር። 22  ቀን ቀን የደመናው ዓምድ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የእሳቱ ዓምድ ከሕዝቡ ፊት አይለይም ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ለይልኝ።”
ቃል በቃል “እያንዳንዱን ማህፀን የሚከፍተው በኩር ሁሉ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ማስታወሻ።”
ቃል በቃል “በዓይኖችህ መካከል።”
ቃል በቃል “ማህፀን የሚከፍተውን ሁሉ።”
ቃል በቃል “ማህፀን የሚከፍተውን ሁሉ።”
ቃል በቃል “በዓይኖችህ መካከል።”