ዘፀአት 15:1-27

  • የሙሴና የእስራኤላውያን የድል መዝሙር (1-19)

  • ሚርያም ከወንዶቹ ጋር እየተቀባበለች ዘመረች (20, 21)

  • መራራው ውኃ ጣፋጭ ሆነ (22-27)

15  በዚያን ጊዜ ሙሴና እስራኤላውያን የሚከተለውን መዝሙር ለይሖዋ ዘመሩ፦+ “በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ እዘምራለሁ።+ ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው።+  አዳኜ ስለሆነልኝ ያህ* ብርታቴና ኃይሌ ነው።+ እሱ አምላኬ ነው፤ አወድሰዋለሁ፤+ የአባቴ አምላክ ነው፤+ እኔም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።+  ይሖዋ ኃያል ተዋጊ ነው።+ ስሙ ይሖዋ ነው።+  የፈርዖንን ሠረገሎችና ሠራዊቱን ባሕር ውስጥ ወረወራቸው፣+ ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎቹም ቀይ ባሕር ውስጥ ሰመጡ።+  ማዕበሉም ከደናቸው፤ እነሱም እንደ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ሰመጡ።+  ይሖዋ ሆይ፣ ቀኝ እጅህ እጅግ ኃያል ነው፤+ ይሖዋ ሆይ፣ ቀኝ እጅህ ጠላትን ያደቃል።  እጅግ ታላቅ በሆነው ግርማህ በአንተ ላይ የሚነሱትን ሁሉ ቁልቁል ታሽቀነጥራቸዋለህ፤+ የሚነደውን ቁጣህን ትልካለህ፤ እነሱንም እንደ ገለባ* ይበላቸዋል።  በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኃዎች ተቆለሉ፤ ወራጁንም ውኃ ገድበው ቀጥ ብለው ቆሙ፤ ማዕበሉም በባሕሩ ልብ ውስጥ ረጋ።  ጠላትም ‘አሳድዳቸዋለሁ! አሳድጄ እደርስባቸዋለሁ! እስክጠግብም* ድረስ ምርኮን እከፋፈላለሁ! ሰይፌን እመዛለሁ! እጄም ታንበረክካቸዋለች!’ አለ።+ 10  አንተም እስትንፋስህን እፍ አልክ፤ ባሕሩም ከደናቸው፤+ እነሱም ኃያል በሆኑ ውኃዎች ውስጥ እንደ አረር ሰመጡ። 11  ይሖዋ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው?+ በቅድስናው ኃያል መሆኑን የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?+ በመዝሙር ልትወደስ የሚገባህ የምትፈራ አምላክ ነህ፤ ድንቅ ነገሮችን ታደርጋለህ።+ 12  ቀኝ እጅህን ዘረጋህ፤ ምድርም ዋጠቻቸው።+ 13  የታደግካቸውን+ ሕዝቦች በታማኝ ፍቅርህ መራሃቸው፤ በብርታትህም ወደ ቅዱስ መኖሪያህ ትመራቸዋለህ። 14  ሕዝቦችም ይሰማሉ፤+ ይንቀጠቀጣሉ፤ የፍልስጤም ነዋሪዎችም ምጥ ይይዛቸዋል። 15  በዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ይሸበራሉ፤ የሞዓብ ኃያላን ገዢዎች ብርክ ይይዛቸዋል።+ የከነአን ነዋሪዎችም ሁሉ ልባቸው ይከዳቸዋል።+ 16  ፍርሃትና ድንጋጤ ይወድቅባቸዋል።+ ይሖዋ ሆይ፣ ሕዝቦችህ አልፈው እስኪሄዱ ድረስ፣ አንተ የፈጠርካቸው ሕዝቦች+ አልፈው እስኪሄዱ ድረስ፣+ ከክንድህ ታላቅነት የተነሳ እንደ ድንጋይ ደርቀው ይቀራሉ። 17  አምጥተህ በርስትህ ተራራ ላይ ትተክላቸዋለህ፤+ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ራስህ ልትኖርበት ባዘጋጀኸው ጸንቶ የተመሠረተ ቦታ፣ ይሖዋ ሆይ፣ እጆችህ በመሠረቱት መቅደስ ትተክላቸዋለህ። 18  ይሖዋ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል።+ 19  የፈርዖን ፈረሶች፣ የጦር ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹ ወደ ባሕሩ በገቡ ጊዜ፣+ ይሖዋ የባሕሩን ውኃ ላያቸው ላይ መለሰባቸው፤+ የእስራኤል ሕዝብ ግን በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት ተሻገረ።”+ 20  ከዚያም የአሮን እህት ነቢዪቱ ሚርያም አታሞ አነሳች፤ ሴቶቹም ሁሉ አታሞ እየመቱና እየጨፈሩ ተከተሏት። 21  ሚርያምም ከወንዶቹ ጋር እየተቀባበለች እንዲህ ስትል ዘመረች፦ “በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ ዘምሩ።+ ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው።”+ 22  ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን ከቀይ ባሕር እየመራ ይዟቸው ወጣ፤ እነሱም ወደ ሹር ምድረ በዳ ሄዱ፤ በምድረ በዳውም ለሦስት ቀን ያህል ተጓዙ፤ ሆኖም ውኃ አላገኙም ነበር። 23  በኋላም ወደ ማራ*+ መጡ፤ ያም ሆኖ በማራ ያለው ውኃ መራራ ስለነበር ሊጠጡት አልቻሉም። የቦታውን ስም ማራ ያለውም በዚህ የተነሳ ነው። 24  በመሆኑም ሕዝቡ “እንግዲህ ምን ልንጠጣ ነው?” እያለ በሙሴ ላይ ማጉረምረም ጀመረ።+ 25  እሱም ወደ ይሖዋ ጮኸ፤+ ይሖዋም ወደ አንዲት ዛፍ መራው። ሙሴም ዛፏን ውኃው ውስጥ ሲጥላት ውኃው ጣፋጭ ሆነ። እሱም በዚያ የሚመሩበት ሥርዓትና ለፍርድ መሠረት የሚሆን መመሪያ አወጣላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው።+ 26  እንዲህም አላቸው፦ “የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል በጥንቃቄ ብታዳምጡ፣ በእሱ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ብታደርጉ፣ ለትእዛዛቱ ጆሯችሁን ብትሰጡና ሥርዓቶቹን በሙሉ ብታከብሩ+ በግብፃውያን ላይ ካመጣሁባቸው በሽታዎች አንዱንም በእናንተ ላይ አላመጣም፤+ ምክንያቱም እኔ ይሖዋ እፈውሳችኋለሁ።”+ 27  ከዚያም 12 የውኃ ምንጮችና 70 የዘንባባ ዛፎች ወዳሉበት ወደ ኤሊም መጡ። በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።

የግርጌ ማስታወሻ

“ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ቃል በቃል “ቆረን።” ጤፍ ወይም ስንዴ ከታጨደ በኋላ ማሳው ላይ የሚቀረውን አገዳ ያመለክታል።
ወይም “ነፍሴ እስክትጠግብም።”
“መራራ” የሚል ትርጉም አለው።