ዘፀአት 19:1-25

  • ሙሴ ወደ ሲና ተራራ ወጣ (1-25)

    • እስራኤላውያን የካህናት መንግሥት ይሆናሉ (5, 6)

    • ሕዝቡ አምላክ ፊት ለመቅረብ ተቀደሰ (14, 15)

19  እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ በሦስተኛው ወር በዚያው ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ።  ከረፊዲም+ ተነስተው ወደ ሲና ምድረ በዳ በመምጣት በምድረ በዳው ሰፈሩ። እስራኤላውያን በዚያ ከተራራው ፊት ለፊት ሰፈሩ።+  ከዚያም ሙሴ ወደ እውነተኛው አምላክ ወጣ፤ ይሖዋም ከተራራው ጠርቶት እንዲህ አለው፦+ “ለያዕቆብ ቤት የምትለው፣ ለእስራኤላውያንም የምትነግረው ይህ ነው፦  ‘እናንተን በንስር ክንፎች ተሸክሜ+ ወደ እኔ ለማምጣት ስል በግብፃውያን ላይ ያደረግኩትን ሁሉ እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል።+  አሁንም ቃሌን በጥብቅ ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ መላው ምድር የእኔ ስለሆነ+ እናንተ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተመረጣችሁ ልዩ ንብረቶቼ* ትሆናላችሁ።+  እናንተ ለእኔ የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ብሔር ትሆናላችሁ።’+ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።”  በመሆኑም ሙሴ ሄዶ የሕዝቡን ሽማግሌዎች ጠራ፤ ይሖዋ ያዘዘውንም ይህን ቃል ነገራቸው።+  ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ በአንድ ድምፅ “ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች ነን”+ ብለው መለሱ። ሙሴም ወዲያውኑ የሕዝቡን ምላሽ ይዞ ወደ ይሖዋ ሄደ።  ይሖዋም ሙሴን “ሕዝቡ ከአንተ ጋር ስነጋገር እንዲሰማና ምንጊዜም በአንተ ላይ እምነት እንዲጥል በጥቁር ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” አለው። ከዚያም ሙሴ የሕዝቡን ቃል ለይሖዋ ተናገረ። 10  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ሕዝቡ ሄደህ ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፤ እነሱም ልብሳቸውን ይጠቡ። 11  ለሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ ምክንያቱም በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ሕዝቡ ሁሉ እያዩ በሲና ተራራ ላይ ይወርዳል። 12  በተራራው ዙሪያ ለሕዝቡ ወሰን አብጅ፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ወደ ተራራው እንዳትወጡ፣ ድንበሩንም እንኳ እንዳትነኩ ተጠንቀቁ። ተራራውን የሚነካ ማንኛውም ሰው ይገደላል። 13  ይህን ሰው ማንም እንዳይነካው፤ ከዚህ ይልቅ በድንጋይ ይወገር ወይም ደግሞ ይወጋ።* እንስሳም ሆነ ሰው በሕይወት እንዲኖር አይተውም።’+ ሆኖም የቀንደ መለከቱ ድምፅ+ በሚሰማበት ጊዜ ወደ ተራራው ሊወጡ ይችላሉ።” 14  ከዚያም ሙሴ ከተራራው ወርዶ ወደ ሕዝቡ ሄደ፤ ሕዝቡንም ይቀድስ ጀመር፤ እነሱም ልብሳቸውን አጠቡ።+ 15  ሕዝቡንም “ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ። የፆታ ግንኙነት ከመፈጸምም ተቆጠቡ”* አላቸው። 16  በሦስተኛውም ቀን ጠዋት ነጎድጓድ መሰማትና መብረቅ መታየት ጀመረ፤ በተራራውም ላይ ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበር፤+ ከፍተኛ የቀንደ መለከት ድምፅም ተሰማ፤ በሰፈሩም ውስጥ ያለው ሕዝብ በሙሉ በፍርሃት ተንቀጠቀጠ።+ 17  በዚህ ጊዜ ሙሴ ከእውነተኛው አምላክ ጋር እንዲገናኙ ሕዝቡን ከሰፈሩ ይዞ ወጣ፤ እነሱም በተራራው ግርጌ ቆሙ። 18  የሲና ተራራ ይሖዋ በእሳት ስለወረደበት ዙሪያውን ጨሰ፤+ ጭሱም እንደ እቶን ጭስ እየተትጎለጎለ ይወጣ ነበር፤ ተራራውም ሁሉ በኃይል ተናወጠ።+ 19  የቀንደ መለከቱም ድምፅ ይበልጥ እየጨመረ ሲመጣ ሙሴ ተናገረ፤ የእውነተኛውም አምላክ ድምፅ መለሰለት። 20  በመሆኑም ይሖዋ በሲና ተራራ አናት ላይ ወረደ። ከዚያም ይሖዋ ሙሴን ወደ ተራራው አናት ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።+ 21  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ሂድ ውረድ፤ ሕዝቡ ይሖዋን ለማየት ሲሉ አልፈው ለመምጣት እንዳይሞክሩ አስጠንቅቃቸው፤ ካልሆነ ግን ብዙዎቹ ለጥፋት ይዳረጋሉ። 22  ዘወትር ወደ ይሖዋ የሚቀርቡት ካህናትም ይሖዋ እንዳይቀስፋቸው ራሳቸውን ይቀድሱ።”+ 23  ከዚያም ሙሴ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “አንተ ‘በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፤ እሱንም ቀድሰው’ በማለት ስላስጠነቀቅከን ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ መቅረብ አይችልም።”+ 24  ሆኖም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ሂድ፣ ውረድና ከአሮን ጋር ተመልሰህ ወደዚህ ውጣ፤ ነገር ግን ካህናቱም ሆኑ ሕዝቡ አልፈው ወደ ይሖዋ ለመምጣት እንዳይሞክሩና እንዳይቀስፋቸው ከልክላቸው።”+ 25  ስለሆነም ሙሴ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ነገራቸው።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ውድ ሀብቴ።”
በቀስት መወጋትን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ወደ ሴት አትቅረቡ።”