ዘፀአት 20:1-26

  • አሥሩ ትእዛዛት (1-17)

  • እስራኤላውያን በተራራው ላይ ባዩት ትዕይንት የተነሳ ፈሩ (18-21)

  • አምልኮን በተመለከተ የተሰጠ መመሪያ (22-26)

20  ከዚያም አምላክ ይህን ቃል ሁሉ ተናገረ፦+  “ከግብፅ ምድር፣ ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ።+  ከእኔ በቀር* ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።+  “በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ።+  አትስገድላቸው፤ ተታለህም እነሱን አታገልግል፤+ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግና+ በሚጠሉኝ ሁሉ ላይ በአባቶች ስህተት የተነሳ በልጆቻቸው እንዲሁም በሦስተኛና በአራተኛ ትውልዶቻቸው ላይ ቅጣት የማመጣ አምላክ ነኝ፤  ሆኖም ለሚወዱኝና ትእዛዛቴን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ታማኝ ፍቅር የማሳይ አምላክ ነኝ።+  “የአምላክህን የይሖዋን ስም በከንቱ አታንሳ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ስሙን በከንቱ የሚያነሳውን ሳይቀጣ አይተወውም።+  “የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ መጠበቅ እንዳለብህ አትርሳ።+  ሥራህንና የምታከናውናቸውን ነገሮች በሙሉ በስድስት ቀን ሠርተህ አጠናቅ፤+ 10  ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለይሖዋ ሰንበት ነው። በዚህ ቀን አንተም ሆንክ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህም ሆነ ሴት ባሪያህ፣ የቤት እንስሳህም ሆነ በሰፈርህ* ውስጥ ያለ የባዕድ አገር ሰው ምንም ሥራ አትሥሩ።+ 11  ምክንያቱም ይሖዋ ሰማያትን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ ካጠናቀቀ በኋላ በሰባተኛው ቀን ማረፍ ጀምሯል።+ ይሖዋ የሰንበትን ቀን የባረከውና የቀደሰው ለዚህ ነው። 12  “አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም+ አባትህንና እናትህን አክብር።+ 13  “አትግደል።*+ 14  “አታመንዝር።+ 15  “አትስረቅ።+ 16  “በባልንጀራህ ላይ ምሥክር ሆነህ ስትቀርብ በሐሰት አትመሥክር።+ 17  “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ። የባልንጀራህን ሚስት፣+ ወንድ ባሪያውን፣ ሴት ባሪያውን፣ በሬውን ወይም አህያውን አሊያም የባልንጀራህ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ።”+ 18  ሕዝቡም ሁሉ የነጎድጓዱንና የቀንደ መለከቱን ድምፅ ሰሙ፤ እንዲሁም የመብረቁን ብልጭታና የተራራውን ጭስ ተመለከቱ፤ ይህም በፍርሃት እንዲንቀጠቀጡና ርቀው እንዲቆሙ አደረጋቸው።+ 19  በመሆኑም ሙሴን “አንተ አነጋግረን፤ እኛም እናዳምጥሃለን፤ ሆኖም እንዳንሞት ስለምንፈራ አምላክ አያነጋግረን” አሉት።+ 20  ሙሴም ሕዝቡን “አትፍሩ፤ ምክንያቱም እውነተኛው አምላክ የመጣው እናንተን ለመፈተን+ ይኸውም ዘወትር እሱን በመፍራት ኃጢአት ከመሥራት እንድትቆጠቡ ለማድረግ ነው”+ አላቸው። 21  ሕዝቡም እዚያው ርቆ ባለበት ቆመ፤ ሙሴ ግን እውነተኛው አምላክ ወዳለበት ጥቁር ደመና ቀረበ።+ 22  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘ከሰማይ ሆኜ እንዳነጋገርኳችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል።+ 23  እኔን የሚቀናቀኑ ከብር የተሠሩ አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከወርቅ የተሠሩ አማልክትም አይኑሯችሁ።+ 24  ከጭቃ መሠዊያ ሥራልኝ፤ በእሱም ላይ የሚቃጠሉ መባዎችህን፣ የኅብረት መሥዋዕቶችህን፣* መንጎችህንና ከብቶችህን ሠዋ። ስሜ እንዲታወስ በማደርግበት ቦታ ሁሉ+ ወደ አንተ እመጣለሁ፣ ደግሞም እባርክሃለሁ። 25  ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ በተጠረቡ ድንጋዮች አትሥራው።+ ምክንያቱም ድንጋዮቹን በመሮህ ከጠረብካቸው ታረክሳቸዋለህ። 26  ኀፍረተ ሥጋህ* በእሱ ላይ እንዳይጋለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።’

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “እኔን የሚቀናቀኑ።”
ቃል በቃል “በደጆችህ።”
እዚህ ላይ የሚገኘው “አትግደል” የሚለው ቃል ሆን ብሎ መግደልን ወይም ሕገ ወጥ ግድያን ያመለክታል።
ወይም “የሰላም መባዎችህን።”
ቃል በቃል “እርቃንህ።”