ዘፀአት 24:1-18

  • ሕዝቡ ቃል ኪዳኑን ለማክበር ተስማማ (1-11)

  • ሙሴ በሲና ተራራ ላይ (12-18)

24  ሙሴንም እንዲህ አለው፦ “አንተ፣ አሮን፣ ናዳብ፣ አቢሁና+ 70ዎቹ የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ይሖዋ ውጡ፤ ከሩቅ ሆናችሁም ስገዱ።  ሙሴ ብቻውን ወደ ይሖዋ ይቅረብ፤ ሌሎቹ ግን መቅረብ የለባቸውም፤ ሕዝቡም ከእሱ ጋር መውጣት የለበትም።”+  ከዚያም ሙሴ መጥቶ የይሖዋን ቃል ሁሉ እንዲሁም ድንጋጌዎቹን በሙሉ ለሕዝቡ ነገራቸው፤+ ሕዝቡም ሁሉ “ይሖዋ የተናገረውን ቃል በሙሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች ነን”+ ሲሉ በአንድ ድምፅ መለሱ።  ስለሆነም ሙሴ የይሖዋን ቃል ሁሉ በጽሑፍ አሰፈረ።+ በማለዳም ተነስቶ በተራራው ግርጌ መሠዊያና 12ቱን የእስራኤል ነገዶች የሚወክሉ 12 ዓምዶች ሠራ።  ከዚያም ወጣት እስራኤላውያን ወንዶችን ላከ፤ እነሱም የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረቡ፤ እንዲሁም በሬዎችን የኅብረት መሥዋዕቶች+ አድርገው ለይሖዋ ሠዉ።  ሙሴም ከደሙ ግማሹን ወስዶ በሳህኖች ውስጥ አስቀመጠው፤ ግማሹን ደም ደግሞ በመሠዊያው ላይ ረጨው።  ከዚያም የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ድምፁን ከፍ በማድረግ ለሕዝቡ አነበበ።+ ሕዝቡም “ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ ለመፈጸምና ለመታዘዝ ፈቃደኞች ነን” አሉ።+  በመሆኑም ሙሴ ደሙን ወስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው፤+ እንዲህም አለ፦ “በእነዚህ ቃላት መሠረት ይሖዋ ከእናንተ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ደም ይህ ነው።”+  ሙሴ፣ አሮን፣ ናዳብ፣ አቢሁና 70ዎቹ የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ላይ ወጡ፤ 10  የእስራኤልንም አምላክ አዩ።+ ከእግሩም ሥር እንደ ሰማይ የጠራ የሰንፔር ንጣፍ የሚመስል ነገር ነበር።+ 11  እሱም በእስራኤል አለቆች+ ላይ ጉዳት አላደረሰባቸውም፤ እነሱም እውነተኛውን አምላክ በራእይ ተመለከቱ፤ በሉ፣ ጠጡም። 12  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣና በዚያ ቆይ። ለሕዝቡ መመሪያ እንዲሆን እኔ የጻፍኩትን ሕግና ትእዛዝ የያዙትን የድንጋይ ጽላቶች እሰጥሃለሁ።”+ 13  በመሆኑም ሙሴ ከአገልጋዩ ከኢያሱ+ ጋር ተነስቶ ወደ እውነተኛው አምላክ ተራራ ወጣ።+ 14  ሽማግሌዎቹን ግን እንዲህ አላቸው፦ “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ እዚሁ ጠብቁን።+ አሮንና ሁር+ አብረዋችሁ ናቸው። ሙግት ያለው ሰው ቢኖር እነሱ ፊት መቅረብ ይችላል።”+ 15  ሙሴም ወደ ተራራው ሲወጣ ደመናው ተራራውን ሸፍኖት ነበር።+ 16  የይሖዋም ክብር+ በሲና ተራራ ላይ እንዳረፈ ነበር፤+ ደመናውም ለስድስት ቀናት ተራራውን ሸፍኖት ነበር። በሰባተኛውም ቀን ከደመናው መሃል ሙሴን ጠራው። 17  ሁኔታውን ይከታተሉ ለነበሩት እስራኤላውያን የይሖዋ ክብር በተራራው አናት ላይ እንዳለ የሚባላ እሳት ሆኖ ታያቸው። 18  ከዚያም ሙሴ ወደ ደመናው ገባ፤ ወደ ተራራውም ወጣ።+ ሙሴም በተራራው ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆየ።+

የግርጌ ማስታወሻ