ዘፀአት 25:1-40

  • ለማደሪያ ድንኳኑ የሚሰጥ መዋጮ (1-9)

  • ታቦቱ (10-22)

  • ጠረጴዛው (23-30)

  • መቅረዙ (31-40)

25  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦  “ለእስራኤላውያን መዋጮ እንዲያመጡልኝ ንገራቸው፤ ለመስጠት ልቡ ካነሳሳው ከእያንዳንዱ ሰው መዋጮዬን ትቀበላላችሁ።+  ከእነሱ የምትቀበሉት መዋጮም ይህ ነው፦ ወርቅ፣+ ብር፣+ መዳብ፣+  ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣* ደማቅ ቀይ ማግ፣ ጥሩ በፍታ፣ የፍየል ፀጉር፣  ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፣ የአቆስጣ ቆዳ፣ የግራር እንጨት፣+  ለመብራት የሚሆን ዘይት፣+ ለቅብዓት ዘይትና+ ጥሩ መዓዛ ላለው ዕጣን+ የሚሆን በለሳን፣  ለኤፉዱ+ እንዲሁም ለደረት ኪሱ+ የሚሆኑ የኦኒክስ ድንጋዮችና ሌሎች ድንጋዮች።  ለእኔም መቅደስ ይሠሩልኛል፤ እኔም በመካከላቸው እኖራለሁ።*+  የማደሪያ ድንኳኑንም ሆነ በውስጡ የሚቀመጡትን ቁሳቁሶች ሁሉ እኔ በማሳይህ ንድፍ መሠረት ትሠሯቸዋላችሁ።+ 10  “ርዝመቱ ሁለት ክንድ* ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል እንዲሁም ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት* ከግራር እንጨት ይሠራሉ።+ 11  ከዚያም በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ።+ ውስጡንና ውጭውን ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ትሠራለታለህ።+ 12  አራት የወርቅ ቀለበቶች ትሠራለታለህ፤ ከዚያም ሁለቱን ቀለበቶች በአንዱ በኩል ሁለቱን ቀለበቶች ደግሞ በሌላው በኩል በማድረግ ከአራቱ እግሮቹ በላይ ታያይዛቸዋለህ። 13  ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ትሠራለህ፤ በወርቅም ትለብጣቸዋለህ።+ 14  ታቦቱን ለመሸከም እንዲያገለግሉ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ጎንና ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ ታስገባቸዋለህ። 15  መሎጊያዎቹ በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ እንዳሉ ይቀመጣሉ፤ ከዚያ መውጣት የለባቸውም።+ 16  የምሰጥህንም ምሥክር በታቦቱ ውስጥ ታስቀምጠዋለህ።+ 17  “እንዲሁም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ መክደኛ ከንጹሕ ወርቅ ትሠራለህ።+ 18  ሁለት የወርቅ ኪሩቦችን ትሠራለህ፤ ወርቁን በመጠፍጠፍም በመክደኛው ጫፍና ጫፍ ላይ ወጥ አድርገህ ትሠራቸዋለህ።+ 19  በሁለቱ የመክደኛው ጫፎች ላይ ኪሩቦቹን ሥራ፤ አንዱን ኪሩብ በዚህኛው ጫፍ፣ ሌላኛውን ኪሩብ ደግሞ በዚያኛው ጫፍ ላይ ሥራ። 20  ኪሩቦቹ ሁለቱን ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይከልሉታል፤+ እነሱም ትይዩ ይሆናሉ። የኪሩቦቹ ፊት ወደ መክደኛው ያጎነበሰ ይሆናል። 21  መክደኛውንም+ በታቦቱ ላይ ትገጥመዋለህ፤ የምሰጥህንም ምሥክር በታቦቱ ውስጥ ታስቀምጠዋለህ። 22  እኔም በዚያ እገለጥልሃለሁ፤ ከመክደኛውም በላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ።+ በምሥክሩ ታቦት ላይ በሚገኙት በሁለቱ ኪሩቦች መካከል ሆኜ እስራኤላውያንን በተመለከተ የማዝህንም ሁሉ አሳውቅሃለሁ። 23  “በተጨማሪም ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር እንጨት ትሠራለህ።+ 24  በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ትሠራለታለህ። 25  ዙሪያውንም አንድ ጋት* ስፋት ያለው ጠርዝ ታበጅለታለህ፤ በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ። 26  አራት የወርቅ ቀለበቶች ትሠራለታለህ፤ ከዚያም ቀለበቶቹን አራቱ እግሮቹ በሚገኙባቸው አራት ማዕዘኖች ላይ ታደርጋቸዋለህ። 27  ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች እንዲይዙ ቀለበቶቹ በጠርዙ አጠገብ ይሆናሉ። 28  መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ትለብጣቸዋለህ፤ ጠረጴዛውንም በእነሱ አማካኝነት ትሸከማለህ። 29  “ለመጠጥ መባ ማፍሰሻ የሚያገለግሉትን ሳህኖቹን፣ ጽዋዎቹን፣ ማንቆርቆሪያዎቹንና ጎድጓዳ ሳህኖቹን ትሠራለህ። ከንጹሕ ወርቅ ትሠራቸዋለህ።+ 30  ገጸ ኅብስቱን በጠረጴዛው ላይ ሁልጊዜ በፊቴ ታስቀምጣለህ።+ 31  “ከንጹሕ ወርቅ መቅረዝ+ ትሠራለህ። መቅረዙም ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፎ የተሠራ ይሁን። የመቅረዙ መቆሚያ፣ ግንድ፣ ቅርንጫፎች፣ አበባ አቃፊዎች፣ እንቡጦችና የፈኩት አበቦች ወጥ ሆነው የተሠሩ ይሆናሉ።+ 32  በመቅረዙ ጎንና ጎን ስድስት ቅርንጫፎች ይኖራሉ፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች ከአንዱ ጎን፣ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች ደግሞ ከሌላው ጎን የወጡ ይሆናሉ። 33  በአንዱ በኩል ባሉት ቅርንጫፎች በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ፤ በሌላኛው በኩል ባሉት ቅርንጫፎችም በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ። ስድስቱ ቅርንጫፎች ከመቅረዙ ግንድ የሚወጡት በዚህ መንገድ ይሆናል። 34  በግንዱ ላይም የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ አራት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ። 35  ከግንዱ በሚወጡት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ በቀጣዮቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥርም አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ በቀጣዮቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥርም እንዲሁ አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ ከግንዱ የሚወጡት ስድስቱም ቅርንጫፎች በዚሁ መንገድ ይሠራሉ። 36  እንቡጦቹና ቅርንጫፎቻቸው እንዲሁም የመቅረዙ ሁለመና ንጹሕ ከሆነ አንድ ወጥ ወርቅ ተጠፍጥፈው የተሠሩ ይሆናሉ።+ 37  ሰባት መብራቶች ትሠራለታለህ፤ መብራቶቹ በሚለኮሱበት ጊዜ ከፊት ለፊቱ ላለው አካባቢ ብርሃን ይሰጣሉ።+ 38  መቆንጠጫዎቹና መኮስተሪያዎቹ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ይሁኑ።+ 39  ቁሳቁሶቹ ሁሉ ከአንድ ታላንት* ንጹሕ ወርቅ ይሠሩ። 40  በተራራው ላይ ተገልጦልህ ባየኸው ንድፍ መሠረት ተጠንቅቀህ ሥራቸው።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ቀይ ሐምራዊ ቀለም የተነከረ ሱፍ።”
ወይም “በመካከላቸው አድራለሁ።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ሣጥን።”
አንድ ጋት 7.4 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።