ዘፀአት 27:1-21

  • የሚቃጠል መባ የሚቀርብበት መሠዊያ (1-8)

  • የማደሪያ ድንኳኑ ግቢ (9-19)

  • ለመብራት የሚሆን ዘይት (20, 21)

27  “ርዝመቱ አምስት ክንድ፣* ወርዱም አምስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር እንጨት ትሠራለህ።+ መሠዊያው አራቱም ጎኖቹ እኩል፣ ከፍታው ደግሞ ሦስት ክንድ መሆን አለበት።+  በአራቱ ማዕዘኖቹ ላይ ቀንዶች+ ትሠራለታለህ፤ ቀንዶቹም የመሠዊያው ክፍል ይሆናሉ፤ መሠዊያውንም በመዳብ ትለብጠዋለህ።+  አመዱን* ማስወገጃ ባልዲዎችን፣ አካፋዎችን፣ ሳህኖችን፣ ሹካዎችንና መኮስተሪያዎችን ትሠራለህ፤ ዕቃዎቹንም ሁሉ ከመዳብ ትሠራቸዋለህ።+  ለመሠዊያው እንደ መረብ አድርገህ የመዳብ ፍርግርግ ትሠራለታለህ፤ በፍርግርጉ በአራቱም ማዕዘኖቹ ላይ አራት የመዳብ ቀለበቶችን ትሠራለታለህ።  ፍርግርጉንም ከመሠዊያው ጠርዝ ወደ ታች ወረድ አድርገህ ታስቀምጠዋለህ፤ ፍርግርጉም መሠዊያው መሃል አካባቢ ይሆናል።  ለመሠዊያው የሚሆኑ መሎጊያዎችን ከግራር እንጨት ትሠራለህ፤ በመዳብም ትለብጣቸዋለህ።  መሎጊያዎቹም ቀለበቶቹ ውስጥ ይገባሉ፤ መሠዊያውን በምትሸከሙበትም ጊዜ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ጎኖቹ በኩል ይሆናሉ።+  መሠዊያውንም ባዶ ሣጥን አስመስለህ ከሳንቃ ትሠራዋለህ። ልክ ተራራው ላይ ባሳየህ መሠረት ይሠራ።+  “የማደሪያ ድንኳኑን ግቢ ትሠራለህ።+ በስተ ደቡብ በኩል የሚገኘው፣ ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ያለው የግቢው ጎን በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ይኖሩታል፤ የአንዱ ጎን ርዝመት 100 ክንድ ይሆናል።+ 10  ግቢው 20 ቋሚዎችና ከመዳብ የተሠሩ 20 መሰኪያዎች ይኖሩታል። በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ደግሞ ከብር የተሠሩ ይሆናሉ። 11  በስተ ሰሜን በኩል በሚገኘው ጎን ያሉት መጋረጃዎችም ርዝመታቸው 100 ክንድ ይሆናል፤ እንዲሁም 20 ቋሚዎችና ለቋሚዎቹ የሚሆኑ ከመዳብ የተሠሩ 20 መሰኪያዎች ይኖራሉ፤ በቋሚዎቹም ላይ ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎች* ይኖራሉ። 12  በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በግቢው ወርድ ልክ 50 ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይኖራሉ፤ አሥር ቋሚዎችና አሥር መሰኪያዎችም ይኖሯቸዋል። 13  በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ በፀሐይ መውጫ በኩል ያለው የግቢው ወርድ 50 ክንድ ነው። 14  በአንዱ በኩል 15 ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይኖራሉ፤ ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎችም ይኖሯቸዋል።+ 15  በሌላኛውም በኩል 15 ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይኖራሉ፤ ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎችም ይኖሯቸዋል። 16  “የግቢው መግቢያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር+ ተሸምኖ የተሠራ 20 ክንድ ርዝመት ያለው መከለያ* ይኑረው፤ አራት ቋሚዎችና ለቋሚዎቹ የሚሆኑ አራት መሰኪያዎችም ይኑሩት።+ 17  በግቢው ዙሪያ ያሉት ቋሚዎች በሙሉ ከብር የተሠሩ መቆንጠጫዎችና ከብር የተሠሩ ማንጠልጠያዎች ይኖሯቸዋል፤ መሰኪያዎቻቸው ግን ከመዳብ የተሠሩ ይሆናሉ።+ 18  ግቢው ርዝመቱ 100 ክንድ፣+ ወርዱ 50 ክንድ ሆኖ በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠሩ 5 ክንድ ከፍታ ያላቸው መጋረጃዎች ይኖሩታል፤ ከመዳብ የተሠሩ መሰኪያዎችም ይኑሩት። 19  በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ለሚቀርበው አገልግሎት የሚውሉት ቁሳቁሶችና ዕቃዎች በሙሉ እንዲሁም የድንኳኑ ካስማዎችና የግቢው ካስማዎች በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ይሆናሉ።+ 20  “አንተም መብራቶቹ ያለማቋረጥ እንዲበሩ ለመብራት የሚሆን ተጨቅጭቆ የተጠለለ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን ታዛቸዋለህ።+ 21  አሮንና ወንዶች ልጆቹ መብራቶቹ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ በምሥክሩ+ አጠገብ ካለው መጋረጃ ውጭ ከምሽት አንስቶ እስከ ጠዋት ድረስ በይሖዋ ፊት+ እንዲበሩ ያደርጋሉ። ይህ እስራኤላውያን በትውልዶቻቸው ሁሉ የሚፈጽሙት ዘላቂ ደንብ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻ

አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በስብ የራሰውን አመድ።” መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡት እንስሳት ስብ የራሰውን አመድ ያመለክታል።
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉ “ቀለበቶች።”
ወይም “መጋረጃ።”