ዘፀአት 29:1-46

  • የካህናቱ ሹመት (1-37)

  • በየቀኑ የሚቀርብ መባ (38-46)

29  “ለእኔ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ እነሱን ለመቀደስ የምታደርገው ነገር ይህ ነው፦ እንከን የሌለበትን አንድ ወይፈንና እንከን የሌለባቸውን ሁለት አውራ በጎች ውሰድ፤+  እንዲሁም ቂጣ፣* በዘይት ከተለወሰ ሊጥ የተጋገረ የቀለበት ቅርጽ ያለው እርሾ ያልገባበት ዳቦና ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ውሰድ።+ እነዚህንም ከላመ የስንዴ ዱቄት ጋግረህ  በቅርጫት ውስጥ ታደርጋቸዋለህ፤ በቅርጫት ውስጥ አድርገህም+ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር ታቀርባቸዋለህ።  “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ+ ታቀርባቸዋለህ፤ በውኃም ታጥባቸዋለህ።+  ከዚያም ልብሶቹን+ ወስደህ ረጅሙን ቀሚስ፣ እጅጌ የሌለውን የኤፉዱን ቀሚስ፣ ኤፉዱንና የደረት ኪሱን አሮንን አልብሰው፤ በሽመና የተሠራውን የኤፉዱን መቀነትም ወገቡ ላይ ጠበቅ አድርገህ ታስርለታለህ።+  ጥምጥሙንም በራሱ ላይ ታደርግለታለህ፤ በጥምጥሙም ላይ ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየውን ቅዱስ ምልክት* ታደርጋለህ፤+  የቅብዓት ዘይቱንም+ ወስደህ በራሱ ላይ በማፍሰስ ትቀባዋለህ።+  “ከዚያም ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ ረጃጅሞቹን ቀሚሶች አልብሳቸው፤+  አሮንንና ወንዶች ልጆቹን መቀነቱን አስታጥቃቸው፤ የራስ ቆባቸውንም አድርግላቸው፤ ክህነቱም ዘላለማዊ ደንብ ሆኖ የእነሱ ይሆናል።+ በዚህም መንገድ አሮንና ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ትሾማቸዋለህ።*+ 10  “ከዚያም ወይፈኑን በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ።+ 11  ወይፈኑንም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በይሖዋ ፊት እረደው።+ 12  ከወይፈኑም ደም ላይ የተወሰነውን ወስደህ በጣትህ በመሠዊያው ቀንዶች+ ላይ አድርግ፤ የቀረውንም ደም በሙሉ መሠዊያው ሥር አፍስሰው።+ 13  ከዚያም አንጀቱን የሸፈነውን ስብ+ ሁሉ፣ በጉበቱ ላይ ያለውን ሞራ፣ ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ያለውን ስብ ውሰድ፤ በመሠዊያውም ላይ እንዲጨሱ አቃጥላቸው።+ 14  የወይፈኑን ሥጋ፣ ቆዳውንና ፈርሱን ግን ከሰፈሩ ውጭ አውጥተህ በእሳት ታቃጥለዋለህ። ይህ የኃጢአት መባ ነው። 15  “ከዚያም አንዱን አውራ በግ ውሰድ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ።+ 16  አንተም አውራውን በግ እረደው፤ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ እርጨው።+ 17  አውራውንም በግ በየብልቱ ቆራርጠው፤ ሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም እጠባቸው፤+ ከዚያም የተቆራረጡትን ብልቶች ከጭንቅላቱ ጋር አሰናድተህ አስቀምጣቸው። 18  አውራውንም በግ ሙሉ በሙሉ በማቃጠል በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ አድርገው። ይህም ለይሖዋ የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ይኸውም ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ+ ነው። ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነው። 19  “ከዚያም ሌላኛውን አውራ በግ ትወስዳለህ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭኑበታል።+ 20  አንተም አውራውን በግ እረደው፤ ከደሙም ወስደህ የአሮንን የቀኝ ጆሮ ጫፍና የወንዶች ልጆቹን የቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ቀባ፤ ደሙንም በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ እርጨው። 21  በመሠዊያው ላይ ካለው ደምና ከቅብዓት ዘይቱ+ ውሰድ፤ ከዚያም አሮንና ልብሶቹ እንዲሁም ወንዶች ልጆቹና ልብሶቻቸው ቅዱስ እንዲሆኑ በአሮንና በልብሶቹ እንዲሁም በወንዶች ልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ እርጨው።+ 22  “አውራው በግ የክህነት ሹመት ሥርዓት በሚካሄድበት ጊዜ የሚቀርብ+ ስለሆነ ከአውራው በግ ላይ ስቡን፣ ላቱን፣ አንጀቱን የሚሸፍነውን ስብ፣ የጉበቱን ሞራ፣ ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ያለውን ስብ+ እንዲሁም ቀኝ እግሩን ውሰድ። 23  በተጨማሪም በይሖዋ ፊት ካለው ቂጣ ከተቀመጠበት ቅርጫት ውስጥ ቂጣውን፣ በዘይት ከተለወሰ ሊጥ የተጋገረውን የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦና ስሱን ቂጣ ውሰድ። 24  ሁሉንም በአሮን እጅና በወንዶች ልጆቹ እጅ ላይ አስቀምጣቸው፤ ከዚያም በይሖዋ ፊት እንደሚወዘወዝ መባ ወዲያና ወዲህ ወዝውዛቸው። 25  በይሖዋም ፊት ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ እንዲሆን ከእጃቸው ላይ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ባለው በሚቃጠለው መባ ላይ ታቃጥላቸዋለህ። ይህ ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነው። 26  “ከዚያም ለአሮን የክህነት ሹመት ሥርዓት የሚቀርበውን አውራ በግ+ ፍርምባ ወስደህ በይሖዋ ፊት እንደሚወዘወዝ መባ ወዲያና ወዲህ ወዝውዘው፤ እሱም የአንተ ድርሻ ይሆናል። 27  ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የክህነት ሹመት ሥርዓት ከቀረበው አውራ በግ+ ተወስዶ ለሚወዘወዝ መባ የቀረበውን ፍርምባና የተቀደሰ ድርሻ እንዲሆን የተወዘወዘውን እግር ትቀድሳቸዋለህ። 28  ይህም የተቀደሰ ድርሻ ስለሆነ የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ይሆናል፤ ይህም እስራኤላውያን የሚፈጽሙት ዘላለማዊ ሥርዓት ነው፤ ይህ ድርሻ እስራኤላውያን የሚያቀርቡት የተቀደሰ ድርሻ ይሆናል።+ ከሚያቀርቧቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ላይ ለይሖዋ የሚሰጥ የተቀደሰ ድርሻቸው ነው።+ 29  “የአሮን ቅዱስ ልብሶችም+ ከእሱ በኋላ የሚመጡት ወንዶች ልጆቹ በሚቀቡበትና ካህናት ሆነው በሚሾሙበት ጊዜ ይገለገሉባቸዋል።+ 30  ከወንዶች ልጆቹ መካከል እሱን የሚተካውና በቅዱሱ ስፍራ ለማገልገል ወደ መገናኛ ድንኳኑ የሚገባው ካህን ለሰባት ቀን ይለብሳቸዋል።+ 31  “ለክህነት ሹመት ሥርዓት የሚቀርበውን አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ።+ 32  አሮንና ወንዶች ልጆቹ የአውራውን በግ ሥጋና በቅርጫቱ ውስጥ ያለውን ቂጣ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ይበሉታል።+ 33  እነሱን ካህናት አድርጎ ለመሾምና* ለመቀደስ ማስተሰረያ ሆነው የቀረቡትን ነገሮች ይበላሉ። ሆኖም እነዚህ ነገሮች የተቀደሱ ስለሆኑ ያልተፈቀደለት ሰው* ሊበላቸው አይችልም።+ 34  ለክህነት ሹመት ሥርዓቱ መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበው ሥጋና ቂጣ ተርፎ ያደረ ካለ የተረፈውን በእሳት አቃጥለው።+ የተቀደሰ ስለሆነ መበላት የለበትም። 35  “እኔ ባዘዝኩህ ሁሉ መሠረት ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ በዚሁ መንገድ ታደርግላቸዋለህ። እነሱን ካህናት አድርገህ ለመሾም* ሰባት ቀን ይፈጅብሃል።+ 36  ለማስተሰረያ እንዲሆን የኃጢአት መባ የሚሆነውን በሬ በየዕለቱ ታቀርባለህ፤ ለመሠዊያውም ማስተሰረያ በማቅረብ መሠዊያውን ከኃጢአት ታነጻዋለህ፤ መሠዊያውን ለመቀደስም ቀባው።+ 37  መሠዊያውን ለማስተሰረይ ሰባት ቀን ይፈጅብሃል፤ እጅግ ቅዱስ መሠዊያ እንዲሆንም ቀድሰው።+ መሠዊያውን የሚነካ ማንኛውም ሰው ቅዱስ መሆን አለበት። 38  “በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው እነዚህን ይሆናል፦ አንድ ዓመት የሆናቸው ሁለት የበግ ጠቦቶችን በየቀኑ ሳታቋርጥ ታቀርባለህ።+ 39  አንደኛውን የበግ ጠቦት ጠዋት ላይ ታቀርበዋለህ፤ ሌላኛውን የበግ ጠቦት ደግሞ አመሻሹ ላይ* ታቀርበዋለህ።+ 40  ተጨቅጭቆ በተጠለለ አንድ አራተኛ ሂን* ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ* አንድ አሥረኛ የላመ ዱቄትና ለመጠጥ መባ የሚሆን አንድ አራተኛ ሂን የወይን ጠጅ ከመጀመሪያው የበግ ጠቦት ጋር ይቅረብ። 41  ሁለተኛውንም የበግ ጠቦት ልክ ማለዳ ላይ ከምታቀርባቸው ጋር ተመሳሳይ ከሆኑ የእህልና የመጠጥ መባዎች ጋር አመሻሹ ላይ* ታቀርበዋለህ። ይህን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ይኸውም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርገህ ታቀርበዋለህ። 42  ይህም እኔ እናንተን ለማነጋገር ራሴን በምገልጥበት በመገናኛ ድንኳኑ+ መግቢያ ላይ በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ በይሖዋ ፊት ዘወትር የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ይሆናል። 43  “እኔም በዚያ ራሴን ለእስራኤላውያን እገልጣለሁ፤ ያም ስፍራ በክብሬ+ የተቀደሰ ይሆናል። 44  የመገናኛ ድንኳኑንና መሠዊያውን እቀድሰዋለሁ፤ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እቀድሳቸዋለሁ።+ 45  እኔም በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁ፤* አምላካቸውም እሆናለሁ።+ 46  እነሱም በመካከላቸው እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው እኔ አምላካቸው ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ።+ እኔ አምላካቸው ይሖዋ ነኝ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ቅዱሱን ዘውድ።”
ቃል በቃል “የአሮንን እጅና የወንዶች ልጆቹን እጅ ትሞላለህ።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ቃል በቃል “እጃቸውን ለመሙላትና።”
ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።” ከአሮን ወገን ያልሆነን ሰው ያመለክታል።
ቃል በቃል “እጃቸውን ለመሙላት።”
ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
አንድ ሂን 3.67 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ወይም “አድራለሁ።”