ዘፀአት 30:1-38

  • የዕጣን መሠዊያ (1-10)

  • የሕዝብ ቆጠራና ለማስተሰረያ የሚሆን ገንዘብ (11-16)

  • ለመታጠቢያ የሚያገለግለው የመዳብ ገንዳ (17-21)

  • በብልሃት የተቀመመ የቅብዓት ዘይት (22-33)

  • የቅዱሱ ዕጣን አቀማመም (34-38)

30  “ዕጣን የሚጨስበት መሠዊያ ትሠራለህ፤+ ከግራር እንጨትም ትሠራዋለህ።+  ርዝመቱ አንድ ክንድ፣* ወርዱ አንድ ክንድ ሆኖ አራቱም ጎኖቹ እኩል ይሁኑ፤ ቁመቱ ደግሞ ሁለት ክንድ ይሁን። ቀንዶቹም ከዚያው ወጥ ሆነው የተሠሩ ይሆናሉ።+  ላዩን፣ ሁሉንም ጎኖቹን እንዲሁም ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ ዙሪያውንም የወርቅ ክፈፍ ትሠራለታለህ።  በተጨማሪም በሁለቱ ተቃራኒ ጎኖቹ ላይ ከክፈፉ በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ትሠራለታለህ፤ ቀለበቶቹም መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉት መሎጊያዎች የሚገቡባቸው ይሆናሉ።  መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው።  ራሴን ለአንተ ከምገልጥበት+ ከምሥክሩ ታቦት+ አጠገብ ካለው መጋረጃ በፊት ይኸውም ምሥክሩን ከሚጋርደው መከለያ በፊት ታስቀምጠዋለህ።  “አሮንም+ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን+ ያጨስበታል፤+ በየማለዳው መብራቶቹን+ በሚያዘገጃጅበት ጊዜም ዕጣኑ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርጋል።  በተጨማሪም አሮን አመሻሹ ላይ* መብራቶቹን በሚያበራበት ጊዜ ዕጣኑን ያጨሰዋል። ይህም በትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘወትር በይሖዋ ፊት የሚቀርብ የዕጣን መባ ነው።  በዚህ መሠዊያ ላይ ያልተፈቀደ ዕጣን+ ወይም የሚቃጠል መባ አሊያም የእህል መባ አታቅርቡ፤ እንዲሁም በላዩ ላይ የመጠጥ መባ አታፍስሱ። 10  አሮንም በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተሰረያ ያድርግ።+ ለማስተሰረያ ከቀረበው የኃጢአት መባ ላይ የተወሰነ ደም ወስዶ+ በዓመት አንድ ጊዜ ለመሠዊያው ማስተሰረያ ያደርጋል፤ ይህም በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይደረጋል። ይህ ለይሖዋ እጅግ የተቀደሰ ነው።” 11  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12  “የሕዝብ ቆጠራ በማካሄድ የእስራኤልን ልጆች በምትቆጥርበት+ ጊዜ ሁሉ እያንዳንዱ ሰው በቆጠራው ወቅት ለይሖዋ ስለ ሕይወቱ* ቤዛ መስጠት አለበት። ይህን የሚያደርጉት በሚመዘገቡበት ጊዜ መቅሰፍት እንዳይመጣባቸው ነው። 13  የተመዘገቡት ሁሉ የሚሰጡት ይህን ነው፦ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* መሠረት+ ግማሽ ሰቅል* ይሰጣሉ። አንድ ሰቅል ሃያ ጌራ* ነው። ለይሖዋ የሚሰጠው መዋጮ ግማሽ ሰቅል ነው።+ 14  ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተመዘገቡት ሁሉ ለይሖዋ መዋጮ ይሰጣሉ።+ 15  ለሕይወታችሁ* ማስተሰረያ እንዲሆን ለይሖዋ መዋጮ በምትሰጡበት ጊዜ ባለጸጋው ከግማሽ ሰቅል* አብልጦ፣ ችግረኛውም ከግማሽ ሰቅል አሳንሶ አይስጥ። 16  ለሕይወታችሁ* ማስተሰረያ በመሆን በይሖዋ ፊት ለእስራኤላውያን እንደ መታሰቢያ ሆኖ እንዲያገለግል ለማስተሰረያ የቀረበውን የብር ገንዘብ ከእስራኤላውያን ወስደህ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ለሚቀርበው አገልግሎት ትሰጠዋለህ።” 17  በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 18  “ለመታጠቢያ እንዲሆን ከመዳብ ገንዳና ማስቀመጫውን ሥራ፤+ በመገናኛ ድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠው፤ ውኃም ጨምርበት።+ 19  አሮንና ወንዶች ልጆቹም እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡበታል።+ 20  ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገቡበት ወይም ለማገልገልና በእሳት የሚቀርብ መባ ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ እንዳይሞቱ በውኃ ይታጠባሉ። 21  እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእሱና ለዘሮቹ በትውልዶቻቸው ሁሉ ዘላለማዊ ሥርዓት ሆኖ ያገልግል።”+ 22  ይሖዋም እንዲህ በማለት ሙሴን ማነጋገሩን ቀጠለ፦ 23  “አንተም ጥሩ መዓዛ ያላቸውን የሚከተሉትን ምርጥ ቅመሞች ውሰድ፦ 500 ሰቅል የረጋ ከርቤ፣ የዚህን ግማሽ ይኸውም 250 ሰቅል ጣፋጭ ቀረፋ፣ 250 ሰቅል ጥሩ መዓዛ ያለው ጠጅ ሣር፣ 24  እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* መሠረት+ 500 ሰቅል ብርጉድ* እንዲሁም አንድ ሂን* የወይራ ዘይት። 25  ከእነዚህም ቅዱስ የቅብዓት ዘይት አዘጋጅ፤ በብልሃት የተቀመመ መሆን ይኖርበታል።+ ይህም ቅዱስ የቅብዓት ዘይት ይሆናል። 26  “አንተም የመገናኛ ድንኳኑንና+ የምሥክሩን ታቦት 27  እንዲሁም ጠረጴዛውንና ዕቃዎቹን በሙሉ፣ መቅረዙንና ዕቃዎቹን፣ የዕጣን መሠዊያውን፣ 28  የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያና ዕቃዎቹን በሙሉ እንዲሁም የውኃ ገንዳውንና ማስቀመጫውን በዘይቱ ትቀባለህ። 29  እጅግ ቅዱስ እንዲሆኑም ቀድሳቸው።+ የሚነካቸው ማንኛውም ሰው ቅዱስ መሆን አለበት።+ 30  አንተም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ትቀባቸዋለህ፤+ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝም+ ትቀድሳቸዋለህ። 31  “አንተም ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ትነግራቸዋለህ፦ ‘በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ምንጊዜም ለእኔ ቅዱስ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።+ 32  ይህ ማንም ሰው ሰውነቱን የሚቀባው አይደለም፤ እንዲሁም በተመሳሳይ መንገድ በመቀመም እንዲህ ያለ ቅባት ማዘጋጀት የለባችሁም። ይህ የተቀደሰ ነገር ነው። ለእናንተም ምንጊዜም የተቀደሰ ይሆናል። 33  ይህን የመሰለ ቅባት የሚሠራና ያልተፈቀደለትን ሰው* የሚቀባ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።’”+ 34  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተም ጥሩ መዓዛ ካላቸው ቅመሞች+ ይኸውም ከሚንጠባጠብ ሙጫ፣ ከኦኒካ፣* ከሚሸት ሙጫ እንዲሁም ከንጹሕ ነጭ ዕጣን እኩል መጠን ውሰድ። 35  ከዚያም ዕጣን አድርገህ አዘጋጀው፤+ ይህም ዕጣን በብልሃት የተቀመመ፣ ጨው የተጨመረበት፣+ ንጹሕና ቅዱስ መሆን ይኖርበታል። 36  ከእሱም የተወሰነውን ወቅጠህ በማላም ራሴን ለአንተ በምገልጥበት በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ባለው ምሥክር ፊት ታስቀምጠዋለህ። ይህም ለእናንተ እጅግ ቅዱስ መሆን ይኖርበታል። 37  በተመሳሳይ መንገድ የተቀመመ ዕጣን ለራስህ ማዘጋጀት የለብህም።+ ለይሖዋ የተቀደሰ እንደሆነ አድርገህ ልትመለከተው ይገባል። 38  በመዓዛው ለመደሰት ሲል ይህን የመሰለ ዕጣን የሚያዘጋጅ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።”

የግርጌ ማስታወሻ

አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
ወይም “ነፍሱ።”
ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ጌራ 0.57 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ለነፍሳችሁ።”
ወይም “ለነፍሳችሁ።”
ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”
ከቀረፋ ዛፍ ጋር የሚዛመድ ዛፍ ነው።
አንድ ሂን 3.67 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ባዕዱን ሰው።” ከአሮን ወገን ያልሆነን ሰው ያመለክታል።
የዚህ ቅመም ምንነት በውል አይታወቅም። ከሚሸት ተክል ወይም ከዛጎል ውስጥ የሚገኝ ሊሆን ይችላል።