ዘፀአት 36:1-38

  • ከሚያስፈልገው በላይ ተዋጣ (1-7)

  • የማደሪያ ድንኳኑ አሠራር (8-38)

36  “ባስልኤል ከኤልያብና ጥሩ ችሎታ* ካላቸው ወንዶች ሁሉ ጋር ይሠራል፤ እነዚህ ወንዶች ቅዱስ ከሆነው አገልግሎት ጋር የተያያዘው ሥራ በሙሉ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት እንዴት እንደሚከናወን ማወቅ ይችሉ ዘንድ ይሖዋ ጥበብና ማስተዋል የሰጣቸው ናቸው።”+  ከዚያም ሙሴ ባስልኤልንና ኤልያብን እንዲሁም ይሖዋ በልባቸው ጥበብን ያኖረላቸውን ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ወንዶች+ ሁሉ ይኸውም ሥራውን ለመሥራት በፈቃደኝነት ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ልባቸው ያነሳሳቸውን+ ሁሉ ጠራ።  እነሱም እስራኤላውያን ለቅዱሱ አገልግሎት ሥራ ያመጡትን መዋጮ+ በሙሉ ከሙሴ ወሰዱ። ሕዝቡ ግን በየማለዳው የፈቃደኝነት መባ ወደ እሱ ያመጣ ነበር።  ቅዱሱን ሥራ ከጀመሩም በኋላ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞች ሁሉ አንድ በአንድ ይመጡ ነበር፤  ሙሴንም “ሕዝቡ፣ ይሖዋ እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከሚፈለገው በላይ እያመጣ ነው” አሉት።  ስለዚህ ሙሴ በሰፈሩ ሁሉ እንዲህ የሚል ማስታወቂያ እንዲነገር አዘዘ፦ “ወንዶችም ሆናችሁ ሴቶች፣ ከእንግዲህ ለቅዱሱ መዋጮ የሚሆን ተጨማሪ ነገር አታምጡ።” በመሆኑም ሕዝቡ ምንም ነገር ከማምጣት ተገታ።  የመጣውም ነገር ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በቂ፣ እንዲያውም ከበቂ በላይ ነበር።  ጥሩ ችሎታ ያላቸውም ሰዎች+ ሁሉ በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ከተሠሩ አሥር የድንኳን ጨርቆች የማደሪያ ድንኳኑን ሠሩ፤+ እሱም* በጨርቆቹ ላይ ኪሩቦችን ጠለፈባቸው።+  የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 28 ክንድ* ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ነበር። ሁሉም የድንኳን ጨርቆች መጠናቸው እኩል ነበር። 10  ከዚያም አምስቱን የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ ቀጣጠላቸው፤ ሌሎቹን አምስት የድንኳን ጨርቆችም እንዲሁ አንድ ላይ ቀጣጠላቸው። 11  ከዚህ በኋላ አንደኛው የድንኳን ጨርቅ ከሌላኛው ጋር በሚጋጠምበት ጠርዝ ላይ ከሰማያዊ ክር ማቆላለፊያዎችን ሠራ። ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት በመጨረሻው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይም እንዲሁ አደረገ። 12  በአንደኛው የድንኳን ጨርቅ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ፤ ማቆላለፊያዎቹም ትይዩ እንዲሆኑ ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት የድንኳኑ ጨርቅ ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ። 13  በመጨረሻም 50 የወርቅ ማያያዣዎችን ሠርቶ የድንኳኑን ጨርቆች በማያያዣዎቹ አማካኝነት እርስ በርስ አጋጠማቸው፤ በዚህም መንገድ የማደሪያ ድንኳኑ አንድ ወጥ ሆነ። 14  ከዚያም ለማደሪያ ድንኳኑ ልባስ የሚሆኑ የድንኳን ጨርቆችን ከፍየል ፀጉር ሠራ። አሥራ አንድ የድንኳን ጨርቆችን ሠራ።+ 15  የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 30 ክንድ ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ነበር። አሥራ አንዱም የድንኳን ጨርቆች መጠናቸው እኩል ነበር። 16  ከዚያም አምስቱን የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ፣ ሌሎቹን ስድስት የድንኳን ጨርቆች ደግሞ አንድ ላይ ቀጣጠላቸው። 17  በመቀጠልም አንደኛው የድንኳን ጨርቅ ከሌላኛው ጋር በሚጋጠምበት በመጨረሻው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ፤ እንዲሁም ከዚህኛው ጋር በሚጋጠመው በሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ። 18  ከዚያም ድንኳኑን በማያያዝ አንድ ወጥ እንዲሆን ለማድረግ 50 የመዳብ ማያያዣዎችን ሠራ። 19  እሱም ቀይ ቀለም ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ለድንኳኑ መደረቢያ ሠራ፤ እንዲሁም ከአቆስጣ ቆዳ በላዩ ላይ የሚደረብ መደረቢያ ሠራ።+ 20  ከዚያም የግራር እንጨት+ ጣውላዎችን በማገጣጠም የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች ሠራ።+ 21  እያንዳንዱ ቋሚ ቁመቱ አሥር ክንድ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር። 22  እያንዳንዱ ቋሚም እርስ በርስ የተያያዙ ሁለት ጉጦች ነበሩት። ሁሉንም የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች የሠራው በዚህ መንገድ ነበር። 23  በመሆኑም በስተ ደቡብ በኩል ለሚገኘው፣ ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ላለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ቋሚዎችን ይኸውም 20 ቋሚዎችን ሠራ። 24  ከዚያም በ20ዎቹ ቋሚዎች ሥር የሚሆኑ 40 የብር መሰኪያዎችን ሠራ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ላሉት ሁለት ጉጦች የሚሆኑ ሁለት መሰኪያዎችን፣ ቀጥሎ ባለው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ላሉት ሁለት ጉጦች የሚሆኑ ሁለት መሰኪያዎችን አደረገ።+ 25  በስተ ሰሜን በኩል ላለው ለሌላኛውም የማደሪያ ድንኳኑ ጎን 20 ቋሚዎችን ሠራ፤ 26  እንዲሁም 40 የብር መሰኪያዎቻቸውን ሠራ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎችን፣ በተቀረው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎችን አደረገ። 27  በስተ ምዕራብ በኩል ለሚገኘው ለኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ስድስት ቋሚዎችን ሠራ።+ 28  በማደሪያ ድንኳኑ በስተ ኋላ በኩል ባሉት ሁለት ማዕዘኖች ላይ የማዕዘን ቋሚዎች የሚሆኑ ሁለት ቋሚዎችን ሠራ። 29  ቋሚዎቹም ከታች አንስቶ የመጀመሪያው ቀለበት እስከሚገኝበት እስከ ላይ ድረስ ድርብ ነበሩ። ሁለቱን የማዕዘን ቋሚዎች የሠራቸው በዚህ መንገድ ነበር። 30  በመሆኑም ስምንት ቋሚዎች የነበሩ ሲሆን እነሱም ከብር የተሠሩ 16 መሰኪያዎች ነበሯቸው፤ ይህም በእያንዳንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያ ማለት ነው። 31  ከዚያም ከግራር እንጨት አግዳሚ እንጨቶችን ሠራ፤ በአንዱ ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን፣+ 32  በሌላኛው ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች ደግሞ አምስት አግዳሚ እንጨቶችን እንዲሁም በስተ ምዕራብ በሚገኘው በኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ላሉት ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን ሠራ። 33  በቋሚዎቹ መሃል ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲዘልቅ መካከለኛውን አግዳሚ እንጨት ሠራ። 34  ቋሚዎቹንም በወርቅ ለበጣቸው፤ አግዳሚ እንጨቶቹን የሚሸከሙትን ቀለበቶችም ከወርቅ ሠራቸው። አግዳሚ እንጨቶቹንም በወርቅ ለበጣቸው።+ 35  ከዚያም ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር መጋረጃ ሠራ።+ በላዩም ላይ ኪሩቦች+ እንዲጠለፉበት አደረገ።+ 36  ከዚያም ለመጋረጃው ከግራር እንጨት አራት ዓምዶችን ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው፤ ማንጠልጠያዎቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ ለዓምዶቹም ከብር የተሠሩ አራት መሰኪያዎችን አዘጋጀ። 37  በመቀጠልም ለድንኳኑ መግቢያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር የተሸመነ መከለያ* ሠራ፤+ 38  እንዲሁም አምስቱን ዓምዶችና ማንጠልጠያዎቹን ሠራ። አናታቸውንና ማያያዣዎቻቸውንም* በወርቅ ለበጣቸው፤ አምስቱ መሰኪያዎቻቸው ግን ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ጥበበኛ ልብ።”
ባስልኤልን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉ “ቀለበቶቻቸውንም።”