ዘፀአት 39:1-43

  • የካህናቱ አልባሳት አሠራር (1)

  • ኤፉዱ (2-7)

  • የደረት ኪሱ (8-21)

  • እጅጌ የሌለው ቀሚስ (22-26)

  • ሌሎቹ የካህናት አልባሳት (27-29)

  • ጥምጥሙ ላይ የሚደረገው ጠፍጣፋ ወርቅ (30, 31)

  • ሙሴ የማደሪያ ድንኳኑ በትክክል መሠራቱን ተመለከተ (32-43)

39  በቅዱሱ ስፍራ ለማገልገል የሚለበሱትን በጥሩ ሁኔታ የተሸመኑትን ልብሶች ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ሠሩ።+ ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረትም የአሮንን ቅዱስ ልብሶች ሠሩ።+  እሱም ኤፉዱን+ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው።  እነሱም ወርቁን በመቀጥቀጥ በስሱ ጠፈጠፉት፤ እሱም ከሰማያዊው ክር፣ ከሐምራዊው ሱፍ፣ ከደማቁ ቀይ ማግና ከጥሩው በፍታ ጋር አብሮ እንዲሠራው ወርቁን እንደ ክር በቀጫጭኑ ሰነጣጠቀው፤ ከዚያም በወርቁ ጥልፍ ጠለፈበት።  ለኤፉዱ በሁለቱ የላይኛው ጫፎቹ ላይ የተያያዙ ሁለት የትከሻ ጥብጣቦች ሠሩለት።  ኤፉዱ ወዲያ ወዲህ እንዳይንቀሳቀስ ለማሰር የሚያገለግለው ከኤፉዱ ጋር የተያያዘው በሽመና የተሠራው መቀነትም + ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት እንደ ኤፉዱ ሁሉ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ተሠራ።  ከዚያም የኦኒክስ ድንጋዮቹን በወርቅ አቃፊዎቹ ውስጥ አስቀመጧቸው፤ የእስራኤልን ወንዶች ልጆች ስሞችም ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ቀረጹባቸው።+  እሱም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች ሆነው እንዲያገለግሉ+ በኤፉዱ የትከሻ ጥብጣቦች ላይ አስቀመጣቸው።  ከዚያም የደረት ኪሱን+ የጥልፍ ባለሙያ እንደሚሠራው አድርጎ ልክ ኤፉዱ በተሠራበት መንገድ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው።+  ለሁለት በሚታጠፍበት ጊዜም አራቱም ጎኖቹ እኩል ነበሩ። ለሁለት በሚታጠፍበት ጊዜ ቁመቱም ሆነ ወርዱ አንድ ስንዝር* የሆነውን የደረት ኪስ ሠሩ። 10  በላዩም ላይ አራት ረድፍ ድንጋዮችን አደረጉበት። በመጀመሪያው ረድፍ ሩቢ፣ ቶጳዝዮንና መረግድ ተደረደረ። 11  በሁለተኛው ረድፍ ደግሞ በሉር፣ ሰንፔርና ኢያስጲድ ተደረደረ። 12  በሦስተኛው ረድፍ ለሼም፣ አካትምና አሜቴስጢኖስ ተደረደረ። 13  በአራተኛውም ረድፍ ክርስቲሎቤ፣ ኦኒክስና ጄድ ተደረደረ። በወርቅ አቃፊዎችም ውስጥ ተቀመጡ። 14  ድንጋዮቹም 12ቱን የእስራኤል ወንዶች ልጆች ስሞች የሚወክሉ ነበሩ፤ ስሞቹም ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ተቀረጹ፤ እያንዳንዱ ስም ከ12ቱ ነገዶች አንዱን የሚወክል ነበር። 15  ከዚያም በደረት ኪሱ ላይ እንደ ገመድ የተጎነጎነ ሰንሰለት ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ።+ 16  በመቀጠልም ሁለት የወርቅ አቃፊዎችንና ሁለት ቀለበቶችን ሠሩ፤ ሁለቱን ቀለበቶችም በደረት ኪሱ ሁለት ማዕዘኖች ላይ አያያዟቸው። 17  በኋላም ሁለቱን የወርቅ ገመዶች በደረት ኪሱ ማዕዘኖች ላይ በሚገኙት ሁለት ቀለበቶች ውስጥ አስገቧቸው። 18  ከዚያም የሁለቱን ገመዶች ሁለት ጫፎች በሁለቱ አቃፊዎች ውስጥ አስገቧቸው፤ በኤፉዱ በፊት በኩል በትከሻ ጥብጣቦቹ ላይ አያያዟቸው። 19  በመቀጠልም ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው በኤፉዱ በኩል በሚውለው በደረት ኪሱ ውስጠኛ ጠርዝ ሁለት ጫፎች ላይ አደረጓቸው።+ 20  ከዚያም ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው በኤፉዱ ላይ ከፊት በኩል ከሁለቱ የትከሻ ጥብጣቦች በታች፣ መጋጠሚያው አጠገብ፣ በሽመና ከተሠራው የኤፉዱ መቀነት በላይ አደረጓቸው። 21  በመጨረሻም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ላይ ሳይንቀሳቀስ፣ ተሸምኖ ከተሠራው መቀነት በላይ እንዲውል የደረት ኪሱን ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ገመድ አያያዟቸው። 22  ከዚያም እጅጌ የሌለውን የኤፉዱን ቀሚስ የሽመና ባለሙያ ሙሉ በሙሉ በሰማያዊ ክር ሸምኖ እንዲሠራው አደረገ።+ 23  የቀሚሱ አንገት ማስገቢያ ልክ እንደ ጥሩር አንገት ማስገቢያ መሃል ላይ ነበር። የአንገት ማስገቢያውም እንዳይቀደድ ዙሪያውን ተቀምቅሞ ነበር። 24  ከዚያም ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍና ደማቅ ቀይ ማግ አንድ ላይ በመግመድ በታችኛው የቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ዘርፍ የሚሆኑ ሮማኖችን ሠሩ። 25  በተጨማሪም ከንጹሕ ወርቅ ቃጭሎችን ሠሩ፤ ቃጭሎቹንም በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ በሮማኖቹ መሃል መሃል አደረጓቸው። 26  ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረትም ለአገልግሎት በሚውለው ቀሚስ የታችኛው ጠርዝ ዙሪያ ቃጭል ከዚያም ሮማን፣ ቃጭል ከዚያም ሮማን እያፈራረቁ አደረጉበት። 27  ከዚያም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ከጥሩ በፍታ ረጅም ቀሚስ በሽመና ባለሙያ አሠሩላቸው፤+ 28  በተጨማሪም ጥምጥሙን+ ከጥሩ በፍታ፣ ጌጠኛ የራስ ቆቦቹንም+ ከጥሩ በፍታ፣ የበፍታ ቁምጣውን+ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ 29  እንዲሁም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት መቀነቱን በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ሸምነው ሠሩት። 30  በመጨረሻም የሚያብረቀርቀውን ጠፍጣፋ ወርቅ ይኸውም ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየውን ቅዱስ ምልክት* ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ፤ አንድ ሰው ማኅተም በሚቀርጽበት መንገድ “ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚል ጽሑፍ በላዩ ላይ ቀረጹበት።+ 31  ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት በጥምጥሙ ላይ እንዲውል ለማድረግ ሰማያዊ ገመድ አሰሩበት። 32  የማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም የመገናኛ ድንኳኑ ሥራ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ እስራኤላውያን ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ነገር ሁሉ ሠሩ።+ ልክ እንደታዘዙትም አደረጉ። 33  እነሱም የማደሪያ ድንኳኑን+ ወደ ሙሴ አመጡ፤ ድንኳኑንና+ ዕቃዎቹን በሙሉ ማለትም ማያያዣዎቹን፣+ አራት ማዕዘን ቋሚዎቹን፣+ አግዳሚ እንጨቶቹን፣+ ዓምዶቹን፣ መሰኪያዎቹን፣+ 34  ለመደረቢያ የሚሆነውን ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳና+ ለመደረቢያ የሚሆነውን የአቆስጣ ቆዳ፣ ለመግቢያው መከለያ የሚሆነውን መጋረጃ፣+ 35  የምሥክሩን ታቦት እንዲሁም መሎጊያዎቹንና+ መክደኛውን፣+ 36  ጠረጴዛውን እንዲሁም ዕቃዎቹን+ በሙሉና ገጸ ኅብስቱን፣ 37  ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን መቅረዝ+ እንዲሁም በመደዳ የተደረደሩትን መብራቶቹንና ዕቃዎቹን+ በሙሉ፣ የመብራቱን ዘይት፣+ 38  የወርቅ መሠዊያውን፣+ የቅብዓት ዘይቱን፣+ ጥሩ መዓዛ ያለውን ዕጣን፣+ ለድንኳኑ መግቢያ የሚሆነውን መከለያ፣*+ 39  የመዳብ መሠዊያውንና+ የመዳብ ፍርግርጉን እንዲሁም መሎጊያዎቹንና+ ዕቃዎቹን+ በሙሉ፣ ገንዳውንና ማስቀመጫውን፣+ 40  የግቢውን መጋረጃዎች እንዲሁም ቋሚዎቹን፣ መሰኪያዎቹን፣+ ለግቢው መግቢያ የሚሆነውን መከለያ፣*+ የድንኳኑን ገመዶች፣ የድንኳኑን ካስማዎችና+ በማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ ለሚከናወነው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች በሙሉ፣ 41  በመቅደሱ ለማገልገል የሚለበሱትን በጥሩ ሁኔታ ተሸምነው የተሠሩትን ልብሶች፣ የካህኑን የአሮንን ቅዱስ ልብሶች+ እንዲሁም ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን ልብሶች አመጡ። 42  እስራኤላውያን ሥራውን በሙሉ ያከናወኑት ይሖዋ ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነበር።+ 43  ሙሴም ሥራቸውን በሙሉ ሲመለከት ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት እንደሠሩ አየ፤ ከዚያም ባረካቸው።

የግርጌ ማስታወሻ

አንድ ስንዝር 22.2 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቅዱሱን ዘውድ።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “መጋረጃ።”