ዘፀአት 4:1-31

  • ሙሴ ሦስት ተአምራት እንዲፈጽም ተነገረው (1-9)

  • ሙሴ ብቁ እንዳልሆነ ተሰማው (10-17)

  • ሙሴ ወደ ግብፅ ተመለሰ (18-26)

  • ሙሴ በድጋሚ ከአሮን ጋር ተገናኘ (27-31)

4  ሆኖም ሙሴ “‘ይሖዋ አልተገለጠልህም’ ቢሉኝና ባያምኑኝስ? ቃሌንስ ባይሰሙ?”+ አለው።  ይሖዋም “በእጅህ የያዝከው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “በትር ነው” አለ።  እሱም “መሬት ላይ ጣለው” አለው። እሱም መሬት ላይ ጣለው፤ በትሩም እባብ ሆነ፤+ ሙሴም ከእባቡ ሸሸ።  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዘው” አለው። እሱም እጁን ዘርግቶ ያዘው፤ እባቡም በእጁ ላይ እንደገና በትር ሆነ።  ከዚያም አምላክ “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ይሖዋ+ እንደተገለጠልህ እንዲያምኑ ነው” አለው።+  ይሖዋም በድጋሚ “እባክህ እጅህን ወዳጣፋኸው ልብስ ውስጥ አስገባ” አለው። እሱም እጁን ወዳጣፋው ልብስ ውስጥ አስገባ። ባወጣውም ጊዜ እጁ በሥጋ ደዌ ተመቶ ልክ እንደ በረዶ ነጭ ሆኖ ነበር!+  ከዚያም “እጅህን ወዳጣፋኸው ልብስ ውስጥ መልሰህ አስገባው” አለው። እሱም እጁን መልሶ ልብሱ ውስጥ አስገባው። እጁንም ከልብሱ ውስጥ ባወጣው ጊዜ እጁ ተመልሶ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነ!  እሱም እንዲህ አለው፦ “ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ተአምራዊ ምልክት ችላ ቢሉ እንኳ የኋለኛውን ተአምራዊ ምልክት በእርግጥ አምነው ይቀበላሉ።+  እንደዛም ሆኖ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑና ቃልህን ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆኑ ከአባይ ወንዝ ውኃ ቀድተህ በደረቁ መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከአባይ የቀዳኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።”+ 10  ሙሴም ይሖዋን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እኔ ከዚህ በፊትም ሆነ አንተ አገልጋይህን ካነጋገርክበት ጊዜ ጀምሮ ፈጽሞ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ንግግር የማልችልና* ተብታባ ሰው ነኝ” አለው።+ 11  ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍ የፈጠረለት ማን ነው? ሰዎችን ዱዳ፣ ደንቆሮ ወይም ዕውር የሚያደርግ አሊያም ለሰዎች የዓይን ብርሃን የሚሰጥ ማን ነው? እኔ ይሖዋ አይደለሁም? 12  በል አሁን ሂድ፤ በምትናገርበት ጊዜ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤* የምትናገረውንም ነገር አስተምርሃለሁ።”+ 13  እሱ ግን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እባክህ መላክ የፈለግከውን ሌላ ማንኛውንም ሰው ላክ” አለው። 14  በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ እንዲህም አለው፦ “እሺ ሌዋዊው ወንድምህ አሮንስ?+ እሱ በደንብ መናገር እንደሚችል አውቃለሁ። ደግሞም አንተን ለማግኘት አሁን ወደዚህ እየመጣ ነው። በሚያይህም ጊዜ ልቡ በደስታ ይሞላል።+ 15  ስለሆነም እሱን አነጋግረው፤ ቃላቱንም በአንደበቱ አኑር፤+ በምትናገሩበትም ጊዜ ከአንተና ከእሱ ጋር እሆናለሁ፤+ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ። 16  እሱም አንተን ወክሎ ለሕዝቡ ይናገራል፤ እንደ ቃል አቀባይም ይሆንልሃል፤ አንተም ለእሱ እንደ አምላክ ትሆናለህ።*+ 17  ይህን በትር በእጅህ ይዘህ ትሄዳለህ፤ በእሱም ተአምራዊ ምልክቶቹን ትፈጽማለህ።”+ 18  ስለዚህ ሙሴ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር+ ተመልሶ በመሄድ “እስካሁን በሕይወት መኖር አለመኖራቸውን አይ ዘንድ እባክህ በግብፅ ወዳሉት ወንድሞቼ ተመልሼ ልሂድ” አለው። ዮቶርም ሙሴን “በሰላም ሂድ” አለው። 19  ከዚያ በኋላ ይሖዋ ሙሴን በምድያም ሳለ “ሂድ፤ ወደ ግብፅ ተመለስ፤ ነፍስህን ለማጥፋት የሚፈልጉት ሰዎች በሙሉ ሞተዋል” አለው።+ 20  ከዚያም ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ ግብፅ ምድር ለመመለስ ጉዞ ጀመረ። የእውነተኛውን አምላክ በትርም በእጁ ይዞ ነበር። 21  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ግብፅ ከተመለስክ በኋላ፣ በሰጠሁህ ኃይል የምታከናውናቸውን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ።+ እኔ ግን ልቡ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤+ እሱም ሕዝቡን አይለቅም።+ 22  ፈርዖንንም እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እስራኤል ልጄ ነው፤ አዎ፣ የበኩር ልጄ ነው።+ 23  እንግዲህ ‘እንዲያገለግለኝ ልጄን ልቀቅ’ ብዬሃለሁ። ለመልቀቅ ፈቃደኛ ካልሆንክ ግን ልጅህን፣ አዎ የበኩር ልጅህን እገድላለሁ።”’”+ 24  ይሖዋም+ በመንገድ ላይ ባለው የእንግዳ ማረፊያ ስፍራ አገኘው፤ እሱንም ሊገድለው ፈልጎ ነበር።+ 25  በመጨረሻም ሲፓራ+ ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ ሸለፈቱን እግሩን ካስነካች በኋላም “ይህ የሆነው አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ስለሆንክ ነው” አለች። 26  ስለሆነም እንዲሄድ ፈቀደለት። እሷም በዚህ ጊዜ በግርዛቱ የተነሳ “የደም ሙሽራ” አለች። 27  ይሖዋም አሮንን “ሙሴን ለማግኘት ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው።+ እሱም ሄደ፤ በእውነተኛውም አምላክ ተራራ+ ላይ አገኘው፤ ከዚያም ሳመው። 28  ሙሴም ይሖዋ እንዲናገር የላከውን ቃል ሁሉ+ እንዲሁም እንዲፈጽማቸው ያዘዘውን ተአምራዊ ምልክቶች ሁሉ+ ለአሮን ነገረው። 29  ከዚህ በኋላ ሙሴና አሮን ሄደው የእስራኤልን ሽማግሌዎች በሙሉ ሰበሰቡ።+ 30  አሮንም ይሖዋ ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ነገራቸው፤ እሱም በሕዝቡ ፊት ተአምራዊ ምልክቶቹን አደረገ።+ 31  በዚህ ጊዜ ሕዝቡ አመነ።+ ይሖዋ ፊቱን ወደ እስራኤላውያን እንደመለሰና+ ሥቃያቸውንም እንዳየ+ ሲሰሙ ተደፍተው ሰገዱ።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “አፈ ከባድና።”
ቃል በቃል “ከአፍህ ጋር እሆናለሁ።”
ወይም “ለእሱ የአምላክ ተወካይ ትሆንለታለህ።”